>
5:13 pm - Thursday April 19, 5179

እናንተማ ምናለባችሁ ዱሮም ገበታችሁ ሙሉ ነው፤ ዛሬም ይህው...! (ያሬድ ሀይለማርያም)

እናንተማ ምናለባችሁ ዱሮም ገበታችሁ ሙሉ ነው፤ ዛሬም ይህው…!

ያሬድ ሀይለማርያም


– ይብላኝ በጨነገፈ የፖለቲካ እሳቢያችሁ ቀየው በቦንብ ለጋየበት ድሀው ያገሬ ሰው፣

– ይብላኝ እድሜውን ሙሉ ያጠራቀመው ሀብቱ በቦንብና በድሮን ለጋየበት ድሀው ያገሬ ሰው፣

– ይብላኝ አንጡራ ሀብቱ ለተዘረፈበት ድሀው ያገሬ ሰው፣

– ይብላኝ ሚስቱ እና ሴት ልጁ በደቦ ለተደፈሩበት ድሀው ያገሬ ሰው፣

– ይብላኝ ቀየው ለወደመበት፣ በአናቱ ላይ የሚያጓራውን መድፍ እና ታንክ ሸሽቶ ከመንደሩ ተሰዶ በየጥሻው ለወደቀው ድሀው ያገሬ ሰው፣

– ይብላኝ ከጦርነቱ  ሸሽቶ በየሰፈራ ጣቢያው እርሀብ ለሚያዳፋው፣ ህክምና ተነፍጎት ነፍሱ ለተሰቀፈችው ድሀው ያገሬ ሰው፣

– ይብላኝ በእናንተ የሥልጣን ጸብ ሀዘን ለወረሰው፣ ልጆቹን ላጣው፣ ሰማይ ለተደፋት፣ ጠኔ ለወረሰው፣ ማቅ ለለበሰው፣ ሀገር አልባ ለተደረገው ድሀው ያገሬ ሰው።

እናንተማ ትላንትም (በዘመነ ወያኔ ጊዜ) አብራችሁ ብርጭቆ ታጋጩ ነበር፤ ሕዝብንም እንደዛው ትገጩት ነበር። መራራውን እውነት እንደ እንቆቆ እየተጋትን ለሰላም ሲባል መጨባበጣችሁን ወደድን።

አዎ ለአገር ሰላም ሲባል፣ የሕዝብ እልቂትን ለማስቆም ሲባል መተቃቀፋችሁን እያቅለሸለሸንም ቢሆን ተቀበልን።

አንድ ቀን ሁላችሁም በፍርድ አደባባይ ቆማችሁ በግራም፣ በቀኝም ላለቀው ሕዝብ ተጠያቂ የምትሆኑበት የፍርድ ቀን ይመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተሳክቶ ለማየት እጓጓለሁ። የራሴንም ድርሻ እወጣለሁ። እናንተም ለፍርድ የምትቀርቡበት ቀን እንዲቀርብ የሙያዬን እወጣለሁ።

ሰላም ለኢትዬጵያ!!

Filed in: Amharic