>

አስገራሚው የአቶ ታዲዮስ ታንቱ ችሎት! (ሮሃ ቲቪ) 

አስገራሚው የአቶ ታዲዮስ ታንቱ ችሎት!

ሮሃ ቲቪ 


ፍ/ቤቱ የታሪክ ተመራማሪው ታዲዎስ ታንቱ የሰነድና የሰው ምስክሮቻቸውን እንዲያሰባስቡ ተጨማሪ ቀን ፈቀደ!

ታሕሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም

አሻራ ሚዲያ ፣

ጋዜጠኛና የታሪክ ምሁሩ ታዲዮስ ታንቱ ትናንት ልደታ ምድብ 3ኛ ጸረ ሽብርና ህገመንግስታዊ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ህዳር 20/2015 በሰጠው ትእዛዝ አቶ ታዲዎስ ታንቱ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ችሎቱ ብይን መስጠቱን ተከትሎ አቶ ታዲዎስ ያሏቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በዝርዝር እንዲያቀርቡ ለዛሬ መቀጠራቸው ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ታዲዎስ ያሏቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በርካታ እንደሆኑና እርሳቸውም በእስር ላይ የሚገኙ መሆናቸውን በማንሳት ፍርድ ቤቱ በማስረጃ አሰባሰቡ ላይ የትእዛዝ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

የታሪክ ምሁሩ በኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊ ባልሆኑ ጸሃፊያን የቀረቡ 10 የታሪክ መጽሃፍትን በሰነድ ማስረጃነት ያቀረቡ ሲሆን እነዚህ በሰነድ ማስረጃነት የተጠቀሱ መጽሃፍትም በሙሉ በኢትዮጵያ ትልቁ በሆነው ቤተምጽሃፍት /ወመዘክር/ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የተቀሩት 5 የሰነድ ማስረጃዎች ደግሞ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተይዘው የሚገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል አቶ ታዲዎስ፡፡

አቶ ታዲዎስ ያቀረቧቸው የሰው ምስክሮች ደግሞ 13 ሲሆኑ ከእነሱም መካከል ከፍተኛ የመንግስት ባልስልጣናት ይገኙበታል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ፣ ረዳት ፕሮፈሰር አበባው አያሌው ፣ ጀነራል አበባው ታደሰ ፣ የምርጫ ቦርድ ሃላፊ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ፣ ጦማሪ ተመስገን ደሳለኝ ፣ መምህርት መስከረም አበራ ፣ አቶ አቻምየለህ ታምሩ ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ እና ሌሎች አምስት ግለሰቦች አቶ ታዲዮስ ታንቱ  የቆጠሯቸው የሰው ምስክሮች ናቸው፡፡

በመሆኑም ከጠቀሷቸው ምስክሮች ውስጥ በውጭ ሃገር የሚኖሩ የታሪክ ጸሃፊዎች በስካይፒ ቃላቸውን እንዲሰጡ እንዲመቻችላቸውና ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ተይዘው የሚገኙ ማስረጃዎቻቸው ለችሎት እንዲቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

ሮሃ ያነጋገረችው የአቶ ታዲዎስ ጠበቃ አዲሱ ጌታነህም ፍርድ ቤቱ አቶ ታዲዎስ በወመዘክር የሚገኙ የሰነድ ማስረጃዎችን በቦታው በመሄድ እንዲያቀርቡና በውጭ አገር የሚገኙ ምስክሮቻቸውን አድራሻ እንዲፈልጉ ትእዛዝ እንደሰጠ ነግረውናል፡፡እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስ በእጁ ያሉትን የሰነድ ማስረጃዎች ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ በድጋሜ መታዘዙን ገልጸዋል፡፡በመሆኑም አቶ ታዲዎስ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ይዘው ለጥር 8/2015 እንዲቀርቡ ፍ/ቤቱ አዟል፡፡

Filed in: Amharic