>

የጋዜጠኛ ተመስገን የፍርድ ቤት ውሎ...! (ታሪኩ ደሳለኝ)

የጋዜጠኛ ተመስገን የፍርድ ቤት ውሎ…!

ታሪኩ ደሳለኝ


ዛሬ 27/4/15 ዓ.ም በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የክስ መዝገብ ውሳኔ ለመስጠት የተሰየመው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የፀረ-ሽብር ችሎት፣ ለጥር 16/5/15 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት በ12/4/15 ዓ.ም መከላከያ ሚንስቴር ለጄነራል መኮንኖቹ ማዕረግ የሰጠበትን መስፈርት እና ቃለ-ጉባኤ እንዲያቀርብ የታዘዘ ቢሆንም፤ መከላከያ በዛሬው ቀን በ27/4/15 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ “ፍርድ ቤቱ የጠየቀኝ ሰነዶች ወታደራዊ ምስጢሮችን የያዙ ስለሆኑ ማቅረብ አልችልም” የሚል መልስ ሰጥቷል፡፡

የጋዜጠኛው ጠበቆች ሄኖክ አክሊሉ እና ቤተማሪያም አለማየሁ መከላከያ የሰጠው መልስ አጥጋቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል፡፡ ጠበቆቹ በችሎቱ እንዳወሱት፣ መከላከያ “ተበደልኩ” ብሎ ክስ ካቀረበ በኋላ፣ ለትክክለኛ ፍትሕ የሚጠቅም ሰነድ ሲጠይቅ ‹ምስጢር ነው” በሚል ፍቃደኛ አለመሆኑ፣ በአንድ በኩል ዐቃቢ ሕግ በክርክሩ ወቅት የተከሳሽን ጥፋተኛነት እንዳላስረዳ የሚያሳይ ሲሆን፤ በሌላ በኩል፣ እኛ ያቀረብነው ማስረጃን እውነተኛነት የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ፍርድ ቤቱ የጠየቀው ሰነድ ከማዕረግ እና ሽልማት አሰጣጥ ጋር ብቻ የሚያያዝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ማዕረጉ በተሰጠበት ሰሞንም ይህው ጉዳይ በመንግሥት ሚዲያዎች በስፋት ሲዘገብ የነበረ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ስለዚህም “ምስጢር ነው ሊባል አይችልም” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቢ ሕግ በበኩሉ አገሪቱ የምስጢር ሕግ እንደሌላት ጠቅሶ፣ ሆኖም መከላከያ ምስጢራዊ ጉዳዮችን በአሰራር እንደሚለይ አስረድቷል፡፡

በመጨረሻም፣ የመከላከያ የሕግ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዳይሪክተር ሻለቃ ኃይለማርያም ማሞ በችሎት ቀርበው የተጠየቁትን ሰነዶች ምስጢራዊነት እንዲያስረዱ ትእዛዝ ተሰጥቶ ለጥር 15 ተቀጥሯል፡፡

Filed in: Amharic