>

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ! (ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ)

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ!

ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ


በክርስቲያኖች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የዕርቅ መጀመሪያ ተደርጎ ይታሰባል። ከልደቱ በፊት በፈጣሪና በፍጡር፣ በሰማይና በምድር፣ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ታላቅ የጠብ ግድግዳ ተገንብቶ ለብዙ ዘመናት ቆይቷል። የልደት በዓል “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለው የፈጣሪ ቃል በተግባር መፈጸም የጀመረበት፤ በአምላክና በሰው ልጆች መካከል ዕርቅ የተወጠነባት ዕለት ናት።

ይህ በዓል መለያየት የጠፋበት፣ ኅብረትና አንድነት የጸናበት፤ መለኮትና ሥጋ፣ ህያውና ሟች፣ ዘላለማዊና ጊዜያዊ፣ ፈጣሪና ፍጡር፣ ሰማያዊና ምድራዊ፣ ምሉዕና ውሱን፣ በተዋሕዶ አንድ ሆነው አዲስ የምሥራች የተበሰረበት ነው። ክፉው በዘራው ዘር መለያየት ነግሦ፣ በሰማይና በምድር መካከል የማይሞላ ገደል ተፈጥሮ እንኖር ነበር። በጠብና በመለየት ምክንያት ኀዘንና ሰቆቃው በዝቶ በሰው ልጆች ታሪክ ጊዜው ዘመነ-ፍዳ ይሰኝ ነበር። የክርስቶስ መወለድ የራቀን አቅርቦ፣ የጠፋውን አግኝቶ፣ የፈረሰውን ገንብቶ፣ የፍዳውን ዘመን ወደ ምሕረት በመቀየር በዘላለማዊ ዕርቅ አንድ አደረገን።

የልደቱ ብሥራት እረኞችን ከሜዳ፣ ሰብአ ሰገልን ከሩቅ ከምሥራቅ ወደ አንድ አምጥቷል፤ ሰዎችን ከምድር ጠርቷል፤ መላእክትን ከሰማይ አውርዷል። ዕለቱ የሰማይና የምድር ፍጡራንን በደስታ ሞልቶ በቤተልሔም ከተማ በአንድነት እንዲዘምሩ አድርጓል። ተራርቀው የሚኖሩትን አሰባስቦ በአንድነት እንዲዘምሩ ያደረጋቸው ጉዳይ ከትናንት ለየቅል ታሪካቸው ይልቅ የነገ የጋራ ተስፋቸው ብሩህ ሆኖ ስለታያቸው ነው። እረኞችና ሰብአ ሰገል በትናንት ታሪካቸው የሚገናኙት በጥቂት ነው። ሰዎችና መላእክት በትናንት ሕይወታቸው የሚገናኙት በጥቂት ነው። የነገው ታሪካቸው ግን አዲስ፣ በደቦ የሚሠሩት፣ በጋራ የሚኖሩት፣ በአንድ የሚወርሱትና በሙላት የሚኖሩበት ነው። ለዚህ ነው ዛሬ የሁሉንም ታሪክ ከክርስቶስ ልደት ጋር አስተሣሥረን የምንተርከው።

ማን ነበርክ? ከሚለው ይልቅ ማን ለመሆን ትፈልጋለህ? የሚለው የአንድነታቸው መሠረት ነው። የነገውን በጋራ ከተጋሩት የትናንቱን በመተሳሰብ መቀበል አይቸግራቸውም። በነገው ላይ ከተግባቡ በትናንቱ ላይ መስማማት አይፈትናቸውም። በረቷ የክርስቶስ በረት፣ እረኞቹ የክርስቶስ እረኞች፣ ጠቢባኑ የክርስቶስ ጠቢባን፣ መላእክትም የክርስቶስ መላእክት፣ ቀኗም የክርስቶስ የልደት ቀን፣ ዘመኑም የክርስቶስ ዘመን ሆነዋል። ያኛው የጥንቱ የብሉይ፣ ይሄኛው ደግሞ አዲሱ የሐዲስ ኪዳንና ታሪክ ሆነ። የጥንቱ በአዲሱ ምክንያት ታወቀ፤ የቀድሞው በአሁኑ ምክንያት ከበረ፤ የትናንቱ በዛሬው ምክንያት ታደሰ።

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ መለያየት የመጣው እንዲሁ አይደለም። ሆን ተብሎ ተሠርቶበት ነው። ክፉው ሆን ብሎ የልዩነትን ዘር ዘርቶ፣ የልዩነትን እሾህ አብቅሎ፣ የጠላትነትን ፍሬ እንዲያፈራ አድርጓል። ልዩነቱም ከመለያየት አልፎ ወደ ጠላትነት እንዲሻገር ሠርቷል። ጠላትነቱም አዳምን ከገነት አፈናቅሏል። አቤልን በቃየል አስገድሏል። በምድር እሾህና አሜከላ አብቅሏል። የጥፋት ውኃን እልቂት አስከትሏል። ጦርነትና ግጭትን አትርፏል። በዚህ ሁሉ ጠላት እንጂ ማንም አልተጠቀመም።

አንድነትም የመጣው በብዙ ልፋትና መሥዕዋትነት እንጂ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም። ከቤተልሔም እስከ ቀራንዮ፣ ከልደት እስከ ስቅለት፣ ከበረት እስከ ዕርገት ዋጋ ተከፍሎበት ነው። ዛሬ የምናከብረው ልደት ያስፈለገውም መለያየት ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው ጠላትነት እንዲሰፍን የተሠራባቸውን ወገኖች አንድ ለማድረግ ነው። ይህን የወገኖች አንድነት ፍለጋ በሰማይ ያሉት ወደ ታች ወርደዋል። እነርሱ ይሄንን እንደ ውርደትም እንደ ውለታም አልቆጠሩትም። በምሥራቅ ያሉት ወደ ምዕራብ ሲመጡ እንደ ድካም አላዩትም። ሁሉም ሰጥቷል፤ ሁሉም ጎድሎበታል። ሁሉም አግኝቷል፤ ሁሉም ትቷል። ሁሉም ከፍ ብሏል፤ ሁሉም ዝቅ ብሏል። ሁሉንም በሁሉ ሆኖ የሞላውና ያሟላው የተወለደው ከሰማይ ወርዶ በግርግም የተወለደው ክርስቶስ ነው።

ኢትዮጵያውያን የነገዋን ኢትዮጵያ የተሻለች ለማድረግ ከዚህ የልደት ታሪክ ብዙ ትምህርት ብንወስድ ይጠቅመናል። ዛሬ እዚህም እዚያም የምናየው የመለያየትና የመጠፋፋት አባዜ የባህሪያችን አይደለም። የማናችንም ማንነት መገለጫ አይደለም። ይህ የተዘራብን ክፉ ዘር ውጤት ነው። የውስጥ የውጭ ባዳ አንድ ሆነው የዘሩብን ዘር ውጤት ነው። ያለንበት ዘመን ዘሩ የተዘራበት ጊዜ አይደለም።

አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ይመስላቸዋል። ይህ ወቅት ዘሩ ጎምርቶ አፍርቶ ያየንበት ወቅት ነው። የታኅሣሥ መከር የሚዘራው በሐምሌ ነው። አንዳንድ ሰዎች ትናንትኮ እንዲህ ያለ ነገር አልነበረም ይላሉ። ዘሩ ከምድር በታች በመብቀል ላይ ስለነበረ አላስተዋልነውም። ሰርዶው አድጎ እግር መጥለፍ ስላልጀመረ አልተቸገርንም። እንክርዳዱ በዝቶ ራስ ማዞር ስላልጀመረ አልታወቀንም። እሾሁ አፍጥጦ ሰውነት መቧጠጥ ስላልጀመረ አልለየነውም። አሜከላው በርክቶ እግር ለማድማት ስላልደረሰ ከቁብ አልቆጠርነውም። እንጂ ክፉው ዘርስ እየበቀለ ነበረ።

ወደ አዲሱ ዘመን፣ ወደ አዲሱ ብርሃን እንምጣ። ወደ አዲሱ ማንነት፣ ወደ አዲሱ ምእራፍ እንምጣ። አዲስ የጋራ ታሪክ ስንሠራ፤ የትናንቱ ታሪክ ያግባባናል። አዲስ መንገድ ስንጀምር የትናንቱ መንገድ አያጣላንም። አዲስ ዘመን ስንወጥን ያለፈው ዘመን አያለያየንም። አዲስ ዓላማ አንግበን ከተነሣን፣ የትናንቱ ዓላማ አያጨቃጭቀንም።

የአንዳችን ጠላት ሆኖ የሌላችን ወዳጅ ሊሆን የሚችል የለም። አንዳችን ታምመን ሌላችን ጤነኛ መሆን አይታሰብም። አንዳችን ጎድሎብን ሌላችን ሙሉ ልንሆን አንችልም። አንዳችን ተከፍተን ሌላችን ደስተኛነትን ማጣጣም አንችልም። የሰው ልጅ ከገነት መውጣቱ የመላእክትን ደስታ ነጥቋል። የእንስሳትን ምቾት አጉድሏል። የምድርንና የሰማይን ክብር ገፍፏል። ገነትን ያለ ሰው አስቀርቷል። የሰው ልጅ ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ለጊዜው በክፋቱ ስኬት በደስታ ፈንጥዟል። የሁላችንም ደስታ ሙሉ መሆን የቻለው ለሁሉም የሚሆነው ክርስቶስ ሲወለድ ነው።

የጠላታችን ዓላማ አንዳችንን ጠቅሞ ሌላችንን መጉዳት ሳይሆን ሁላችንንም ማጥፋት ነው። ዲያብሎስ መጀመሪያ አዳምና ሔዋንን አካሰሰ። ቀጥሎ ሰውን ከፈጣሪው ነጣጠለ። ከዚያ ሰውን ከመኖሪያው ከገነት አፈናቀለ። እሾህና አሜከላ እንዲበቅል አድርጎ ሰውንና ምድርን አቆራረጠ። ቃየልን በአቤል ላይ አስነስቶ አስገደለው። ጠላታችን አንዱን ሕዝብ ከሌላው በማጋጨት አይቆምም፤ አንዱንም ሕዝብ እርስ በርሱም ያባላዋል። ክልልን ከክልል፣ ዞንን ከዞን፣ ወረዳን ከወረዳ፣ ጎጥን ከጎጥ፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ባልን ከሚስት፣ ልጆችን ከወላጆች እያባላ ዓለምን ሁሉ የግጭትና የጠብ ዐውድማ ማድረግ ነው ምኞቱ።

ስለዚህ ቆም ብለን እናስብ። መንገዱ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ለሁላችንም በቅቶ የሚተርፍ፣ አዲስ ማንነትን ይዘን እንደገና መወለድ ነው። ታሪክ ማለፉ አይቀርም። ታሪክ መለወጡም አይቀርም። ቁም ነገሩ የታሪክ ተከሳሽና ተወቃሽ ወይንስ ተዘካሪና ተሞጋሽ እንሆናለን? የሚለው ነው። ከሩቅ መጥተው መሲኹን እንደተገናኙት ጠቢባን ሰብአ ሰገል ታሪክ እንሠራለን ወይስ እንደ ሄሮድስ ታሪክን ለማጥፋት በንጽሐን ላይ ሰይፍ እናነሣለን? የሚለው ነው። እንደ ቅዱሳን መላእክቱ ለአዲስ ታሪክ አዲስ የምሥራች እናበሥራለን ወይስ እንደ ዘመኑ የአይሁድ ልሂቃን ባለፈው ታሪክ ላይ ተተክለን የቀረበልንን ዕድል በንቀት እንገፋለን? የሚለው ነው።

የእነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት፣ ኢትዮጵያ በአዲስ ልደት መንገድ እየተጓዘች የጌታችንንና የመድኃኒታችንን ልደት እንድታከብር ባለ በቂ ምክንያት ያደርጋታል።

መልካም የልደት በዓል ይሁንልን!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ታህሳስ 28፣ 2015 ዓ.ም.

Filed in: Amharic