>
5:08 pm - Tuesday February 22, 4648

በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት ያለች ሀገር ኢትዮጵያ (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)


ደወል 1 ዘኢትዮጵያ

በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት ያለች ሀገር ኢትዮጵያ

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

ይቅርታ፥ እርቅ፥ ምክክር፥ መግባባት። የማንለው የለም። ግን የሚደረግ ነገር የለም። ለምን? አንድ ነገር ለማድረግ ቀርቶ፥ ለመነጋገርም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ነን። ማስረጃ ቢባል በሦስት ረድፍ ላስረዳ። አንደኛ ንግግር መጀመር አይቻልም። ሁለተኛ ንግግር ቢጀመር እንኳን መቀጠል አይቻልም። ሦስተኛ ንግግር መቀጠል እንኳን ቢቻል፥ መጨረስ አይቻልም። በዚህ ዓይነት የመፍትኤ ሀሳብ እንዳይወለድ (እንዳይሰማ) በሦስት ደረጃዎች መላን የሚያጨናግፍ ብዙ ጩኸቶች አሉ።  

 1ኛ/ ንግግር እንዳይጀመር ፈንጂ ተጠመደ

የተቀበረ ፈንጂ ስለማይታይ ሰላም ነው ብሎ በመሬት ላይ የሚራመድ ሰው ሁሉ ላይ አደጋ ያደርስበታል።  ዛሬ ላይ የፈውስ ሀሳብን ማንሳት እጅግ የሚያስቸግርበት ሁኔታ እየሆነ ነው።  የተናጋሪው ስም እንደ ታፔላ (ፈንጂ) ይሆናል።  የሰው አስተሳሰቡ በራሱ እንዳይመዘን በማድረግ፥ የተናጋሪውን አስተሳሰብ እንዲመክን ይደረጋል።  አንዱ የሚናገረው ነገር ጆሮ ለመክፈት እንዳይችል ፈንጅ እንቅፋት ነው። ገና ከመነሻው ሥር እንዳይዝ የሀሳብ ፍሰት ማጥለያ (filter) ይደነቀርበታል።  ደግሞ የተወሰኑ ኮድ ቃላቶች እንደ ፈንጂ ያገለግላሉ።  በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተናጋሪው ሀሳቡን ሊያብራራ ይቅርና የሀሳቡን ርዕስ እንኳን ለመግለፅ እንዳይችል ያደርጋሉ። አንዳንዶቻችን ከነገሩ ጦም እደሩ ብለን በግል ሕይወታችን ላይ ብቻ እንድናተኩር ተገደናል።  

2ኛ/ ንግግር እንዳይቀጥል ቋንቋ ተደበላለቀ

በባቢሎን ከተማ ሰዎች ሰማይ የሚደርስ ሐውልት ሊሰሩ ተነሱ።  ፈጣሪ ከዓላማው ጋር የሚሄድ ራዕይ ስላልሆነ ቋንቋቸውን ደባለቀ።  አንድ ልብ ሆነው እንዳይሰሩ፥ ቋንቋ ተደበላልቆ መግባባት እንዳይችሉ አደረጋቸው።  ከዚያ ሁሉን ትተው በዓለም ዙሪያ ተበተኑ። ይህ ታሪክ በእኛ ተደገመ፥ በፈጣሪ ሳይሆን በክፉው።

ኢትዮጵያ በአብሮነት እንድንትገነባ በጎ ፍቃደኝነት እና ቅን ልቦና በኢትዮጵያ ልጆች ላይ አለ።  ሁሉም የሀገሩ ነገር እንቅልፍ አሳጥቶት የሚታትርና የሚጥር እንደሆነ ይታወቃል።  ግን ሁሉም የሚያውቀው ብዙ ዘርቶ ትንሽ ማጨዱን፥ ብዙ እየለፋ የሚታፈስ ነገር ግን ማጣቱን ነው። ኢትዮጵያን ለማዳን ላይ ታች በማለት በተስፋ ብንጠመድም፥ ትርፍ ሳይሆን ከዕለት ዕለት ኪሳራ ሆነብን።  በዚህ ውስጥ አንዱ ንግግር መጀመር ከቻለ፥ የሚቀጥለው ፈተናው ደግሞ ንግግሩን መቀጠል ነው።  ምክንያቱም ቋንቋ ስለተደበላለቀ ንግግሩን ያቆመዋል።  አማርኛ እየተናገርን የምንለው ግን የተለያየ ሲሆን ቋንቋችን ይደበላለቃል።  አፋን ኦሮሞ እየተናገርን የምንለው ግን የተለያየ ሲሆን ቋንቋችን ይደበላለቃል። ሌላውም እንደዚሁ።  ቃላቶች ትርጉማቸውን ከደበላለቁብን፥ እንደ ባቢሎን ዘመን አልሆንምን?

3ኛ/ ንግግር እንዳይጨረስ ሰበር ዜና ሰባበረን

የቁም ነገር ንግግርና ሚዛን የሚደፋ ሀሳብ የሚሰማ ጆሮ ብቻ ሳይሆን የሚያስተውል አዕምሮ ይፈልጋል።  ለማስተዋል ሰከን ብሎ ማዳመጥና አውጥቶ አውርዶ ውሳኔ ለመወሰን ጊዜ መውሰድን ይጠይቃል።  ታዲይ ሰብር ዜና ለዚህ ፋታ አይሰጥም።  ከአንዱ ሰበር ዜና ወደ ሌላኛው እየተቀባበለ ለማሰብ ፋታ እንዳይኖረን ያደርጋል።  እንደ ጉም በየጊዜው እየተነነ በማይጨበጥ ነገር እያደናገረን ጊዜያችንን ብቻ ሳይሆን እኛን ራሳችንን እየመዘመዘ ይበላናል።  ሁልጊዜ እሳት ላይ እንደተጣድን ነው።  እፎይታ የለም፥ ለማሰብ ፋታ የለም።  ሰብር ዜና እኛን የሚሰባብር ዜና ቢባል ጥሩ ነበር።

የነገሩ ፍፃሜ ምንድነው?

የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን አሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፥ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው።  እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈፅሞ አንችልም ማለት ነው። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፥ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን፥ ወደ ሞት ይወስደናል ማለት ነው። ታዲያ ምን ይሻላል? በተከታታይ እንመለከታለን፥ በደወል 2 ዘኢትዮጵያ እንገናኝ። 

ፀሐፊውን ለማግኘት: www.myETHIOPIA.com 

Filed in: Amharic