>
5:26 pm - Tuesday September 15, 1536

“እንዳንሰደድ መንገድ ተዘግቶብናል፣ እንዳንኖር ቢላዋ ተስሎብናል ..” (በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

“እንዳንሰደድ መንገድ ተዘግቶብናል፣ እንዳንኖር ቢላዋ ተስሎብናል የጥይት ናዳ ይወርድብናል” የሀሮ አዲስ ዓለም ቀበሌ ነዋሪዎች እሮሮ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

“ለውጥ መጣ” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አራት ዓመታት አንዳንዴ በአሸባሪነት በተፈረጁ ድርጅቶች ስም አለፍ ሲልም በመንግሥት የጸጥታ አካላትና መዋቅር ተሳትፎ እና ሽፋን ሰጪነት  በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ በዓለም ላይ ተሰምቶም ሆነ ታይቶ የማይታወቅ ተከታታይና ስልታዊ በሆነ ዘዴ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እየተፈጸመ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከዚህ በፊት ሲፈጸሙ የነበሩ ጭፍጨፋዎችን በሽብር ድርጅቶች ሲያሳብብ የቆየው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጭንብሉን አውልቆ በይፋ ሕዝብን መጨፍጨፍ ጀምሯል።

በተለያዩ አካባቢዎች ይፈጸም የነበረውን ጭፍጨፋ ሸሽተው በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪረሙ ወረዳ፣ ሀሮ አዲስዓለም ቀበሌ በተሰበሰቡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ በአራቱም አቅጣጫ በዛሬው ዕለት ጥር 03 ቀን 2015 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡ 00 ሰዓት ጀምሮ በተለየዩ የቡድን መሣሪያዎች በመታገዝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በነዋሪዎች ላይ ከባድ ተኩስ መክፈቱንና በአሁኑ ሰዓት የአካባቢው ነዋሪዎች እየተገደሉ እና ቀሪዎችም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸውን ፓርቲያችን ከአካባቢው ምንጮች ለመረዳት ችሏል።

እስከአሁን እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፈ ማሰቆም ያልፈለገው፣ ለአንድም ቀን እንኳን በስህተት የሐዘን መግለጫም ሆነ እየተካሔደ ላለው እልቂት ይቅርታ ጠይቆ የማያውቀው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዲሁም ጉዳዩን ባልሰማ እያለፈ ያለው የፌደራል መንግሥቱ ይዋል ይደር እንጂ ከጠጠያቂነት አያመልጡም። በተኩስ እሩምታ እየተናጠ ያለው የአካባቢው ነዋሪ እንዳይሰደድ ዙሪያውን መንገድ እንደተዘጋበት፣ በቀየው ጸንቶ እንዳይኖር ቢላዋ እንደተሳለበት፣ የተኩስ ናዳ እየወረደበትና በዚህም ለተከታታይ ጊዜያት ያዝ ለቀቅ በሚያደርግ ጭፍጨፋ እልቂት ላይ እንደሆነ ይናገራል።

የዜጎቻችንን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት የተሸከመው መንግሥት

፩. በቀበሌው ነዋሪ ላይ የተከፈተውን ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያሰቆም፤

2. የመከላከያ ሰራዊት በአፋጣኝ ደርሶ ከጭፍጨፋው የተረፉትን ወገኖች እንዲታደጋቸው፤

3. የክልሉ መንግሥት ጩኸት በሚበረታበት ጊዜ ዝም ያለ እየመሰልና እያዘናጋ የሚፈጽመው ጭፍጨፋ ሀገርን የሚያፈርስ አደገኛ አካሔድ ስለሆነ መላው ሕዝባችን እንዲያወግዘው ብሎም እንዲታገለው፤

፬. በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠረው እልቂት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለይቶ የሚያስቀረው አንድም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ተረድተን ሁሉም ዜጋ ከተበደሉት ጎን እንዲቆም፤

5. ዜጎቻችን እየተጨፈጨፉ ያሉበት የኦሮሚያ ክልልን እያስተዳደርኩ ነው የሚለው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እየተፈጸመ ላለው ግፍ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን፣ በጉዳዩ በቀጥታ እጃቸው ያለበት አጥፊዎችም ለፍርድ እንዲቀርቡ በጥብቅ እናሳስባለን።

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

እናት ፓርቲ

ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

Filed in: Amharic