>

ይዘገያል እንጂ በሕዝባችን ላይ እልቂትን ያደረሱ ሁሉ ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም! (ክርስቲያን ታደለ)

ይዘገያል እንጂ በሕዝባችን ላይ እልቂትን ያደረሱ ሁሉ ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም! –

 ክርስቲያን ታደለ

*

በአጣዬ ለ10ኛ ጊዜ እየደረሰ ባለው ኹሉንአቀፍ ጥቃት እጅጉን አዝናለሁ። 

እንደዓውደ ዓመት እየተደጋገመ የሚመጣ፣ መንስዔው ታውቆ ያደረ፣ የእልቂት ተዋናዮች በውል የሚታወቁ እና ግቡም ቢሆን ለሁሉም የታወቀ ነው። የጥቃቱ የትክተት ነጥብ አጣዬ ትሁን እንጂ ሰንሰለቱ ግን እጅግ ብዙ ነው። የእዝ ማዕከሉም ቢሆን ለግምት የቸገረ አይደለም። 

እንዲያው በተለምዶ የኦነግ ሸኔ የሽብር ጥቃት ነው የሚባለውም በእኔ እምነት በቂ አይደለም። ይልቁንም መንግስታዊ መዋቅሩ አመራር እየሰጠበት የሚፈፀም የግዛት መስፋፋትን ግቡ ያደረገ በዘመቻ የሚፈፀም ጥቃት ነው የሚለው ገላጭ ነው። በመንግስታዊ መዋቅር በሚዘወረው ዘመቻ ሸኔን ጨምሮ የጋራ የፖለቲካ ግብ ያነገቡ የየራሳቸውን የተጠና ሚና የሚጫወቱ አካላት ሊኖሩ ቢችሉም ዋናዎቹ አዝማቾች ግን በመንግስታዊ መዋቅር የሚገኙ ናቸው። 

ሕዝባችን እነዚህን ቀንደኛ አንቃሳቃሾች በመለየት ታግሎ ለፍርድ በማቅረብ መሰል ስውር እጆች ዳግመኛ እንዳነሱ የሚያደርግ ቅጣት ካላገኙ በስተቀር እልቂቱ የመቆም እድሉ የሰለለ ነው። 

በእሳት እየነደደ ላለ ወገን ስለችግር ምንጭ ማብራራት እፎይታን ባይሰጥም የችግሩን ምንጭ አውቆ ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀ በስተቀር ዛሬ 10 ያልነው የዘመቻ ጥቃት በየዓመቱ ወርኅ እየጠበቀ የመደገም እድሉ ሰፊ ይሆናል። 

ይዘገያል እንጂ በሕዝባችን ላይ እልቂትን ያደረሱ ሁሉ ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም!

Filed in: Amharic