>

እየተሸረበ ያለውን መፈንቅለ ሲኖዶስ ፓርቲያችን ባልደራስ በፅናት ይቃወማል...! (ባልደራስ)

እየተሸረበ ያለውን መፈንቅለ ሲኖዶስ ፓርቲያችን ባልደራስ በፅናት ይቃወማል…!

ባልደራስ

ህውሓት እና ኦነግ ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ ሲያቀነቅኑ የነበሩት የ“አማራ (የአበሻ) ጭቆና” የቆመባቸው መሠረቶች አራት ናቸው ብለው በመሥራች ፅሑፎቻቸው ሳይቀር አስፍረዋል፡፡ እንደነዚህ ፅንፈኛ ብሔርተኞች አመለካከት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የትግራይንና የኦሮሚያ ሪፐብሊኮችን ለመመስረት 

1ኛ/ የአማርኛ ቋንቋ 

2ኛ/ የግዕዝ ፊደል

 3ኛ/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 

4ኛ/ ዘውድን ከኢትዮጵያ ህዝብ ስነልቦና መፋቅ ሲቻል ነው ብለው ያምናሉ፡፡  

ይህን አለመለካከታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በአማርኛ ቋንቋ ምትክ ኦሮምኛ ቋንቋን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሥራ ቋንቋ ማድረግ፣ የግዕዝ ፊደልን በላቲን ፊደል እንዲተካ ማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን በምእራብ ዓለም በሚደጎሙ ከፕሮቴስታንት አስተምህሮ ጋር በማይጣጣው እንደ የብልፅግና ወንጌል ባሉ ዘመን አመጣሽ አመለካካቶች እንዲቦረቦር አድርጎ እና ከፋፍሎ በማዳከም አንዲተካ ማድረግ፣ ዘውድን በተመለከተ ከሌሎች የኢትዮጵያ ዘውዳዊ መንግሥት ተቀናቃኞች ጋር ተባብሮ ማስወገድ የሚሉ አመለካከቶችን የሚሉ አስተሳሰቦች ይዞ፣ ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት የተጠነሰሰ አመለካከት ነው፡፡ የእንነዚህ ፅንፈኛ የነገድ ብሄርተኞች ወላጅ የሆነው እና የአመለካከት አንድነት ያለው ኦህዴድ ብልፅግና የአማራ ጪቆና መግለጫዎች ናቸው የሚላቸው ዘዉዱ ሲቀር ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱን የሚያጠቃልል ነው፡፡ የኦነግ የበኩር ልጅ የህወሓት የመንፈስ ልጅ የሆነው ኦህዴድ በኦህዴድ ብልፅግና ስም የመንግስት ስልጣንን በብቸኝነት በመቆጣጠሩ አሁን የአባቱን የኦነግን እና የመንፈስ አባቱን የህወሓትን ከአራት እና አምስት አስርት አመታት በፊት ይዘዋቸው የተነሱትን ፀረ-ኢትዮጵያ ዓለማዎች አንድ በአንድ በተግባር እየተረጎማቸዉ ነዉ፡፡

ዘውድ በሪፖብሊክ እስከ ተቀየረበት እስከ ደርግ ዘመነ መንግሥት ድረስ የኢትዮጵያ ስርዓተ መንግሥ የሚገለጥባቸው ሁለት አንጓዎች ዘውድና  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ነበሩ፡፡ የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትናም ሆነ የኢትዮጵያ እስልምና የኢትዮጵያ የአይሁድ እምነት የሃገራችን ልዩ መገለጫዎች ሁነው ለሺህ ዘመናት ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና፣ የኢትዮጵያ እስልምና እና የአይሁድ እምነቶች ከመካከለኛው ምስራቅ ወደ ኢትዮጵያ ፈልሰው በመጡ የሃይማኖት ሰባኪያን ኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋ ቢሆንም፣ እነዚህ አሃዳዊ (monotoistic) እምነቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ለሺህ ዘመናት በመቆየታቸው፣ የራሳቸውን ሃገራዊ ባህሪይ በመቅረፅ ከኢትዮጵያ ህዝብ ስነ ልቦና ጋር ተሰናስለው ጠንካራ 

የእምነት ተከታታይ እንዲሆን ከማድረጋቸው በላይ፣ በየእምነቱ ተከባብሮ፣ የሃገር አንድነትን ጠብቆ እና አፅንቶ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ወደር የሌለው አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

ኦህዴድ/ ብልፅግና የውጭ ምእራባውያን ፀረ- ኢትዮጵያ ሃይሎችን ተልእኮ ተሸካሚ ለመሆን በመምረጡ በሃገሪቱ መሠረታዊ እምነቶች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የማዳከም ደባውን ቀጥሎበታል፡፡ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ እስልምና እምነትን የመጀሊስ አመራር በነገድ መነፀር በማየት የኦህዴድ ብልፅግና ፓርቲ በመለመላቸው “መንፈሳዊ” ካድሬዎች አማካይነት መፈንቅለ መጅልስ ማድረጉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በነካ እጁ አሁን ደግሞ ደባው ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዙሯል፡፡ ለሺህ ዘመናት ሃገረ ተጠብቃ እና ተከብራ እንድትኖር ያደረጉ ሃገር በቀል እምነቶችን እየቦረበሩ፣ ከውጭ እየተደጎሙ በገቡ ዘመን አመጣሽ “እምነቶች” ለመተካት የሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች በገንዘብ እየደጎሙ የሚያስፈፅሙት ተልእኮ ነው፡፡ 

የራስን ልዩ መገለጫ እያቀለሉ የውጭ ተልእኮ አራማጅ መሆን ሃገርን ከማፍረስ ተነጥሎ የሚታይ ድርጊት አይደለም፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ለመታዘብ እንደተቻለው የኦህዴድ/ብልፅግና ፕሮፖጋንዳ እና ተግባራዊ ክንውን በተፃራሪ መንገድ የሚጓዝ ነው፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ እና ጊዜያዊ የፖለቲካ ተቀባይነት ለማግኜት ሲባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውስጡን እና የውጩን ሲኖዶስን ያስታረቅንበት ምክንያት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሃገር ናት ያሉበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እንደ ሌሎች በርካታ የተዘነጉ የጠቅላይ ሚኒስተሩ አባሎች ይህም አባባል አሁን ስልጣናችን ተደላድሏል ተብሎ በሚታመንበት ጊዜ የሃገር አንድነት ዋልታ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከቀኖናዋ እና ከህገ ቤተክርስቲያን ውጭ ፓትሪያሪክ እና ጳጳሳት በህይወት እያሉ ሌላ ፓትሪያሪክ፣ ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ በማስደረግ እየተገለፀ ነው፡፡  “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዳሚባለው የሃገራችን ብሄል ህገ ወጥ መፈንቅለ ሲኖዶስን በበላይነት የመራው የሶስት ጳጳሳት ሃሳዊ መሲህ ቡድን  ጥር 14/2015 በወሊሶ ከተማ በይፋ ተሰብስቦ አንድ አዲስ ፓትሪያሪክ፣ 26 ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሁም በርካታ ዲያቆናትን ያካተት አዲስ ሲኖዶስ መሥርተናል ሲል በይፋ አስታውቋል፡፡ ይህ ፍፁም ህገ ወጥ የሆነ እርምጃ ህግን በበላይነት ማስከበር ባለበት በኦህዴድ ብልፅግና መንግስት ቀጭን ትዕዛዝ በአጭር ካልተቀጨ፣ በምእመናን መከከል ልዩነት ተፈጥሮ ሃገር ወደ ብጥብጥ እና ትርምስ እንድታመራ መንገድ የሚጠርግ ድርጊት ነው፡፡

ይህን ይፋ የወጣን የመፈንቅለ ሲኖዶስ ድርጊት ፈፃሚ የሆነው ቡድን አሁን ድርጊቱ በይፋ ቢከሰትም፣ አቅዱ ሲብላላ የከረመና ይህ ሃሳዊ- መሲህ ቡድን እቅዱ ወደ ተግባር ሊተረጎም ስለሚችልበት ሁኔታ በመንግስት ውስጥ ካሉ የበላይ አስተባባሪዎች ጋር ለረዢም ጊዜ ሲመከርበት የከረመ ነው፡፡ ይህ የህገ ወጥ ቡድን ጉልበት እንዲያበጂ በማድረግ፣ ከለላ በመስጠት፣ በየሆቴሉ ስብሰባ እንዲጠራ በማድረግ የፌድራል መንግስቱን ሥልጣን የተቆጣጠረው የኦህዴድ/ብልፅግና ፓርቲ እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉለት እንደነበር የሚካድ አይደለም፡፡ 

እየተከናወነ ያለው መፈንቅለ ሲኖዶስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህጋዊ መብቷን የሚጥስ እንደመሆኑ፣ ትክክለኛ ህግ ካለ መፈንቅለ ሲኖዶሱ በህግ ሊታገድ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ህገ ወጥነትን የመከላከል ቀዳሚ ተልእኮም ሆነ ስልጣን ያለው ተቋም ደግሞ የፌደራል መንግሥቱን ስልጣን በበላይነት በሚቆጣጠረው በኦህዴድ/ብልፅግና እጅ ነው፡፡ መንግሥት እያለ በመንግስት ላይ ሌላ መንግስት መሰየም ለብጥብጥ እንደሚዳርግ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲን ቀኖና ህገ ቤተክርስቲያንን በጣሰ መልኩ ህጋዊ ፓትሪያሪኩም ሆነ ህጋዊ የሲኖዶስ አባላት መንበራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ወይም በሞት ሳይነተቁ ሌላ ፓትሪያሪክ እና ሌላ ሲኖዶስ ማቋቋሙ ታላቅ መንግሥታዊ ግድፈት እና የህግ የበላይነትን መጣስ ነው፡፡ በዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ምክንያት የሃገር ሰላም ቢደፈርስ የኦህዴድ ብልፅግና መንግሥት ብቸኛ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

የኦህዴድ/የብልፅግና መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲሰፍን በማድረግ ይህን አይን ያወጣ መፈንቅለ ሲኖዶስ ማቆም ሲችል፣ ህግን ለሚጥሱ ወገኖች ድጋፍ በመስጠት ተደራደሩ የሚል መግለጫ ማውጣት የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥትን  መንግሥት ያሰኜውን ተቀዳሚ ተግባሩን በገዛ ፈቃዱ መተውን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ህገ ወጥ የመፈንቅለ ሲኖዶስ ድርጊት የኦህዴድ/ብልፅግና መንግሥት በጉዳዩ እጁን በረዥሙ አስገብቶ በእጅ አዙር እየመራው መሆኑን የሚያስረግጥ ነው፡፡ 

በህወሓት ኢህአዴግ ዘመን አቡነ መርቆሪዮስ ሃገራቸውን እና መንበራቸውን ትተው እንዲሰደዱ በማድረግ እና በምትካቸው አቡነ ጳውሎእ መንበሩን እንዲረከቡ በማድረግ ረገድ የወቅትቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ታምራት ላይኔ ግፊቱ ከህወሓት እንደመጣ እና እሱ በህወሓት ታዛዥ በመሆኑ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንደነበረ በስደት ላይ ባለበት ሀገረ አሜሪካ ሆኖ ለሚዲያ በሰጠው ቃለ መጠይቅ አምኗል፡፡  

ይህ የሃገር እና የህዝብ ሰላምን የሚነሳ ድርጊት የተፈፀመው የዓለም ቅርስ የሆነው የጥምቀት በዓል አከባበር የሕዝብ አንድነትን ባጠነከረ ታላቅ ጨዋነትና ስነ ስርዓትን በተከተለ መልኩ የውጭ ቱሪስቶች በታላቅ አድናቆት በተመለከቱበት እና በተመሰጡበት ሁኔታ በተከናወነ በዋዜማው መፈፀሙ፣ ሃገርን ለማፍረስ ሲሰሩ የነበሩ ሃይሎች ተልእኳቸው እየከሸፈ መሆኑን ከመገንዘብ የመነጨ የቁጭት ድርጊት ይመስላል፡፡ 

በህወሓት የአገዛዝ ዘመን በፓትሪያክ አቡነ መርቆርዮስ ላይ በተፈፀመው የመንግሥታዊ ተፅእኖ በግድ ሃገር ለቀው እንዲሄዱ በመደረጉ ነባሩ ሲኖዶስ ከኢትዮጵያ ውጭ ሆኖ እንዲቀጥል፣ በዚያም ድርጊት ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሁለት እንድትከፈል መደረጉ ይታወቃል፡፡ ሲኖዶሱ በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገር እንዲከፈል ከተደረገ በኋላ መንግሥት በውጭ ሃገር ህግን ለማስከበር ስልጣን ስለሌለው የቤተክርስቲያኗ ክፍፍል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሊቆ ቻለ፡፡  አሁን ግን ክፍፍሉ የተፈጠረው በሃገር ውስጥ ስለሆነ፣ በሃገር ውስጥ ህግን የማስከበር ተቀዳሚ ተልእኮ ያለው በመንግስት እጅ መሆኑ እየታወቀ፣ ህገ ወጦችን ከህገ ወጥ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ሲቻል፣ ተደራድሩ የሚል መንግሥታዊ መግለጫ ማውጣት የብልፅግና መንግሥት ለህገ ወጥ ቡድኑ ድጋፍ ሰጭ መሆኑን በግልፅ ያመለክታል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የሃራችን ጌጥ በሆነችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት አጥብቆ ይቃወማል፡፡ በብፁ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብቸኛ ህጋዊ ፓትሪያርክ መሆናቸውን፣ የሚመሩት ሲኖዶስም ብቸኛ ህጋዊ ሲኖዶስ መሆኑን ፓርቲያችን ባልደራስ በጥብቅ ያስገነዝባል፡፡  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ  እምነት ተከታዮች ኢትዮጵያውን ቤተ-እምነቱ በሚደነግገው መሰረት ከህጋዊ እና ብቸኛ ፓትሪያርካቸው ከብፁ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ከሚመሩት ህጋዊ እና ብቸኛ ሲኖዶስ ጀርባ በአንድነት በመቆም በሃሳዊ መሲህ “ፓትሪያሪክ ነኝ” ባይና በሱም እንዲመራ ተቋቋመ ለተባለው ህገ ወጥ ሲኖዶስ እውቅና በመንፈግ የተጠነሰሰውን ፀረ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና ፀረ – ኢትዮጵያዊነት ተግባር እንዲያከሽፉ ፓርቲያችን ባልደራስ በአፅንኦት ጥሪውን ያቀርባል፡፡ 

የባልደራስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ቀን 17/2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Filed in: Amharic