መርገምት፤ ግንድ ግንዱን መገርሰስ
ያሬድ ሀይለማርያም
በዘመነ ወያኔ የጀመረው አገራዊ ክሽፈት በብዙ እጥፍ አቅሙንና ፍጥነቱን ጨምሮ ኢትዬጵያን ቁልቁል እየነዳት እንደሆነ የቅርቡ በእስልምና እምነት ላይ አነጣጥሮ የነበረው ደባና ክፍፍል ጋብ ሲል በሰሞኑ ቆብ ያጠለቁ ነውረኞች ድራማ መተካቱ ጥሩ ማሳያ ነው። ወያኔ ስልጣን ከያዘች ጀምሮ ካደረገችው በርካታ ኢትዮጵያን የማዳከም እኩይ ሥራዎች መካከል የአገሪቱን እድሜ ጠገብ ተቋማት ማፈራረስ፣ ሕዝቧን ያስተሳሰሩ ማህበራዊ መስተጋብሮችን መበጣጠስ፣ እድሜ ጠገብ አገራዊ ትውፊቶችን ማራከስ እና በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ክብርና ሞገስ ያላቸውን አውራዎች ማዋረድ፣ ማሸማቀቅ እና ሕዝብ እንዲንቃቸው ማድረግ ነበር። በወቅቱ ፕሮፌሰር መስፍን ወያኔ ግንድ ግንዱን እየገነደሰች ነው ብለው ነበር።
አንጋፋ የሙያ ማህበራትን አፍርሶ በተለጣፊ ካድሬዎች መተካት፣ አለም ያከበራቸው ምሁራንን በአደባባይ መዝለፍና ማዋረድ፣ ማሰርና ማዋከብ፣ የጏይማኖት ተቋማትን አናታቸውን ጨምድዶ በመያዝ የአፈናው መዋቅር አካል ማድረግና የፖለቲካ ምርኩዝ አድርጎ ምዕመናኑን ለማሸማቀቂያነት መጠቀም፣ ታሪክን በተዛባ ትርክት መቀየርና ጥራዝ ነጠቅ ትውልድ መፍጠር የተሳካው የወያኔ ትልም ነበር። አንጋፋውን የመምህራን ማህበር፣ የሠራተኞች ኮንፌደሬሽን፣ የነጻ ጋዜጠኞች ማህበር እና አከርካሪያቸው ተመቶ በካድሬዎችና በፖለቲካ ተሻሚዎች እጅ የወደቁትን የትምህርት ተቋማትና የጏይማኖት ቤቶችን ሁኔታ ልብ ይለዋል።
ይሄ ኢትዮጵያን ለማዋረድ፣ ታሪኳን ለማዛባት፣ ነጻና ጠንካራ ተቋም የሌላት ደካማ አገር እንድትሆን እና አዲስ የታሪክ ድርሳን ለመጻፍ በወያኔ የተጀመረው ግንድ ግንዱን የመደርመስ እኩይ ተግባር ዛሬም ወያኔ ባሰለጠነቻቸው መንደርተኛ ካድሬዎች አፍጦና አግጦ መምጣቱ፣ ምናልባትም እጅግ በከፋና አስፈሪ በሆነ መልኩ መከሰቱ ማንኛውንም ጤነኛና ቅን አሳቢ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንቅልፍ የነሳው ጉዳይ ይመስለኛል።
ወያኔ ከርክማና ኮትኩታ ያሰለጠነቻቸው የትላንት ጨቅላ ካድሬዎች፣ የዛሬ አገር መሪዎች በሰለጠኑበት መንገድ ኢትዮጵያን አውራ ግለስብ እና አውራ ተቋማት የማሳጣት የክሽፈት ምሪታቸውን ምንም ሳይሳቀቁና ያለ ምንም አፍረት ቀጥለውበታል። ኢትዮጵያ ዛሬ ማባሪያ በሌለው በመከራዎች ናዳ ከግራ ቀኝ እየተወገረች ነው።
ባሳለፍነው ሳምንት እንኳ አጣዬና አካባቢዋ በዘር ፖለቲካ በተመረዙ አክራሪዎች በእሳት ቶን ውስጥ ሲለበለቡና ጥይት ሲያጓራባቸው፤ በተመሳሳይ ቀናት የብዙ ዘመናት ታሪክ ያላትና የጽናት ተምሳሌት የሆነችው ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከጉያዋ በወጡ ባለቆብ ካድሬዎች ስትናጥ ከረመች። ለእኔ አጣዬ ለስንተኛ ጊዜ የተከሰተው በአክራሪ ታጣቂዎች ጥቃት ስር ውላ ለቀናት በእሳት መንደድና የቤተክርስቲያን በተመሳሳይ ጊዜ የተኩላ ለምድ በለበሱ ሰዎች በነገር እሳት መለብለብ ውላቸውም ሆነ ምንጫቸው አንድና አንድ ብቻ ነው። አገራዊ የፖለቲካ ክሽፈት ያስከተላቸው ችግሮች ናቸው። መዳረሻ ግባቸውም እንዲሁ አንድ ነው። አክተሮቹም ግብራቸው ቢለያይም፣ ውሏቸውና የተሰማሩበት ግንባር ቢራራቅም ከጀርባ ሆነው ነገሩን ለሚያቀነባብሩትና ለሚመሩት ሰዎች ግን አንድ ግብና አንድ መዳረሻ ነው ያላቸው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ግንድ ግንዱን የመገርሰስ ስልቶች አካል ናቸው። ባጭሩ ኢትዮጵያን አዳክሞ የዛሬ ክልሎችን የነገ ራስ ገዝ አገር የማድረግ ጭንጋፍ የሆነ የፖለቲካ ንድፍ ማሳለጫዎች ናቸው።
እስኪ በዚህ 30 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተዋከበ፣ ያልተዋረደ፣ ክብሩ ያልተገፈፈ፣ በካድሬዎች ጭንጋፍ እሳቤ ያልተጨናገፈ፣ ያልተዘረፈ ተቋም ጥሩልኝ? በጭንጋፍ እሳቤ አገር የማጨንገፉ እኩይ ሥራ በብዙ መልኩ ለመሳካቱ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ጥሩ ምስክር ነች። እስኪ እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር ያልከሸፍንበትን ጎናችንን ንገሩኝ? በትምህርት ጥራት መቀመቅ መውረዳችንን የትምህርት ሚኒስትሩ ትላንት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ውጤት ሲናገሩ አብረው አርድተውናል፣ የጏይማኖት ተቋማቶቻችን የጨነገፉ ካድሬዎች መፈንጫ ከሆኑ ዘመናት ተቆጥሯል፣ አንጋፋ የሚባሉ ተቋማትች ገሚሱ ፈርሰዋል፣ የተቀሩት ካለመኖር ባልተሻለ ሁኔታ ተዳክመዋል፣ ለአገር ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ምሁራን ከነመኖራቸው ተረስተዋል፣ ምሁራኖቹ ያደራጇቸው የትምህርት ተቋማት ከሳይንሳዊ ምርምር ይልቅ የብሔር ፖለቲካ ሰለባ ሆነዋል፣ የአገር ባለውለታ የሆኑ አውራዎች ለበጎ ሥራቸው የስድብና የጥላሸት ካባ በላያቸው ተደፍቶ እንዲሸማቀቁ ተደርጓል።
ዛሬ መከራው በብዙ እጥፍ ቢበረታም ቢያንስ ቁጭ ብለን የሃፍረት፣ የክሽፈት፣ የስጋትና የምሬት እንቆቋችንን እየተጎነጨን የምንቆዝምበት ምርጥ ምርጥ ፖርኮች ተሰርተውልናል። አንድነት በሌላት አገር ውስጥ በአንድነት ፖርክ ውስጥ ቁጭ ብለን ለምን አንድነት እንዳጣን ማሰላሰል እንችላለን።
ለማንኛውም አገርን አውራ በማሳጣትና ግንድ ግንዱን እየገነደሱ በደረቅ ጭራሮ አገርን ለማቆምና ለማጽናት እንደማይቻል የመጣንበት እረዥም እርቀት ጥሩ ማሳያ ነው። ጭራሮ ተሰብስቦ ቢታሰር እንኳ ችቦ ይሆናል እንጂ ግንድ ሊሆን አይችልም። አገር የሚጸናው በጠንካራ ተቋማት፣ በደፋርና እውነተኛ ምሁራን እና ቅን አሳቢና በጎ ራዕይ ባነገቡ የፖለቲካ ልሂቃን ነው። ፖለቲከኛውም፣ ቄሱም፣ ሼሁም፣ ምሁሩም፣ ተማሪውም እኩል በከሸፉበት አገር ግን አውራና ግንድ አይኖርም። ጭራሮ ብቻ እንጂ። አውራ ያጣ ሕዝብ ቀፎው ጠፍቶበት እንደተበተነ የንብ መንጋ ነው። ለራሱም ለሌላም ስጋት ነው። ወደ ቀልባችን ቶሎ ተመልሰን አውራዎቻችንን ከፊት ካላስቀደምን፣ አገር ጸንታ እንድትቆም ግንድ የሆኑንን ተቋማትና ግለሰቦች ጨርሰው ሳይጠፉ ካልደገፍናቸው እና ሁሉን ነገር ለጭራሮዎች ከተውን እንደ አገርም፣ እንደ ሕዝብም ተረት የምንሆንበት ዘመን እሩቅ አይሆንም።