>

ቤተክርስቲያን ምድሩም፣ ባሕሩም እንዳይገዛ ብታወግዝ ይህ አረመኔያዊ አገዛዝ በአንድ ቀን ታሪክ በሆነ. ነበር...! (አቻምየለህ ታምሩ)

ቤተክርስቲያን ምድሩም፣ ባሕሩም  እንዳይገዛ  ብታወግዝ  ይህ አረመኔያዊ አገዛዝ በአንድ ቀን ታሪክ በሆነ. ነበር…!

አቻምየለህ ታምሩ

ከሁሉ በላይ አቅም እያላት እንደ አቡነ ጴጥሮስና አቡና ሚካኤል ያሉ ምድራዊ ሞትን የናቁ አባቶች በማጣቷ የአረመኔ መጫዎቻ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን !

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአገዛዙ በእጅጉ የላቀ አቅምና ኃይል ያላት ተቋም መሆኗን የተረዳች አትመስል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአንድ አካል የሚመራ መዋቅር፣ ለሃይማኖቱና ለቤተ ክርስቲያኑ  ሰማዕትነትን ለመቀበል የቆረጠና መጠቃት ያብሰከሰከው ሕዝብ አላት። ይህ ሕዝብ  የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ  ግማሽ የሚያህል ነው።

እንደዚህ  አይነት ድርጅታዊ ጥንካሬ ያለው ምድራዊ ኃይል በኢትዮጵያ ውስጥ የለም።  በመንግሥትነት የተሰየመው የኦሮሙማ የአፓርታይድ አገዛዝ ጠመንጃና በገንዘብ የገዛው  ካድሬ እንጂ ሕይወቱን የሚሰጥ ታማኝ የሆነ መዋቅር የለውም። በመዋቅር ስናየው  አገዛዙ ልዩ ልዩ ክፍሎች ከላይ እስከ ታች ለየራሳቸው የሚፈለጉትን የሚያስፈጽሙ አምበሎች እንጂ መዋቅራዊ የበላይነት ያለው መሪ የላቸውም። የአገዛዙ አንዱ ክፍል ትዕዛዝ ሲሰጥ ሌላው አንተ ማነህ ነው ብሎ 

ይጠይቀዋል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አይነት ተዋረድ ለመፍጠር ሺህ ዓመታትን ይፈጃል። እንዲህ አይነት ተቋማዊ ተዋረድ በድንገት ሊፈጥሩት አይቻልምም።ባጭሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተርስቲያን የሰጠችው መመሪያ በመዋቅሩባ በምዕመዙ ዘንድ ያለ ይፈጸማል። ይህ ተቋማዊ  ኃይል ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጦር ማንሳት ሳያስፈልጋት በመንግሥትነት በተሰየመው አረመኔያዊ አገዛዝ መዋቅር ስር በአገዛዙ ልዩ ልዩ ክፍሎች በተለይም በጦር ኃይሉ፣ በፖሊስ ሠራዊትና በሕዝብ ደኅንነት መዋቅሩ ውስጥ የሚያገለግሉ  የቤተ ክርስቲያኗን ልጆች ከአሁን በኋላ ቤተ ክርስቲያናችኹን እያጠፋ ከሚገኘው አረመኔ አገዛዝ ጋር አትተባብሩ ብትል አረመኔው አገዛዝ በነጋታው ይወድቃል። 

ከቤንቶ ሙሶሊኒ አስር እጅ የከፋ ዘግናኝ ጥፋት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ላደረሰው ለአረመኔው ዐቢይ አሕመድ  የጭካኔ አገዛዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምድሩም፣ ባሕሩም እንዳይገዛ ቤተ ክርስቲያኗ በታወግዝ ደግሞ የዐቢይ አሕመድ አረመኔያዊ አገዛዝ በአንድ ቀን ይወገዳል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ያህል አቅም ቢኖራትም ከሷ ብዙ እጅ ያነሰ አቅም ያለው አረመኔያዊ አገዛዝ እንዲያጠፋት በመፍቀድ በጸሎት ብቻ የመጣባትን መከራ ለመከላከል እየሞከረች ትገኛለች። ከምንም በላይ አስቂው ነገር ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ በምታወጣቸው መግለጫዎች እያጠፋት ያለው አረመኔ አገዛዝ ይጠብቃት ዘንድ ጥሪ ማስተላለፏ ነው። ይህ በእውነቱ በጎችን ተኩላ ይጠብቃቸው ዘንድ ከመጠየቅ አይተናነስም። 

ለሺ አመታት የቆየችውን ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዐቢይ አሕመድ አረመኔያዊ አገዛዝ ጥፋት መታደግ የሚቻለው ሊያጠፋት ቆርጦ ከተነሳው ጠላቷ ከዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ተፈጥሮ ጋር የተመጣጠነ የኅልውና ተጋድሎ ስታደርግ ብቻ ነው።    

የዐቢይ አሕመድ አረመኔያዊ የኦሮሙማ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ተራ አምባገነን አይደለም። በመንግሥትነት የተሰየመው የኦሮሙማ አረመኔ የአፓርታይድ አገዛዝ ከግራኝ አሕመድና ከፋሽስት ጥሊያን በላይ የከፋ፤ ክፋትና ጭካኔ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ላይ ለመፈጸም የአቅም ማነስ ከሚገታው በቀር ሌላ መግቻ የሌለው አረመኔ ቡድን መሆኑን ቤተ ክርስቲያኗ ያወቀች አይመስልም። 

ይህን መገንዘብ ቤተ ክርስቲያኗ ሊያጠፋት ከተነሳው  ከአረመኔው የዐቢይ አሕመድ የኦሮሙማ አገዛዝ ራሷን ለመታደግ የምታደርገው ትግል  በጠላቷ የክፋት መጠን እንዲሆን ይረዳታል። በጸሎት፣ በምህላ፣ በፈሪሀ እንግዚያብሔር፣ በይሉኝታና በኅሊና ልጓም ተወስኖ አረመኔው  የዐቢይ አሕመድ አፓርታይድ አገዛዝ ቤተ ክርስቲያኗን ከጥፋት ይታደጋል ብሎ ማሰብ «በግ ካራጁ ኋላ እንደሚጎተት» እየተጎተቱ  ሞትን እያነገሡ አጥፊዎችን አበጃችሁ እንደማለት አይነት ጅልነት ነው። 

በእውነቱ የጣሊያን ጠቅላሚኒስትርና የፋሽት ፓርቲ መሪ የነበረው ቤኒቶ ሙሶሊኒ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጥፋት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየመውና የኦሮሙማ ዋና ስራ አስፈጻሚው ዐቢይ አሕመድ  በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሰራው ጥፋት አንድ አስረኛ አይሆንም። 

ኢትዮጵያ እውነተኛ የሃይማኖት አባት ቢኖራት ኖሮ ከቤንቶ ሙሶሊኒ አስር እጅ የከፋ ዘግናኝ ጥፋት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለው አረመኔው ዐቢይ አሕመድ  ቤተ ክርስቲያኗን ከኦሮምያቸው  ፈጽሜ አጠፋታለኹ እያለ እየፎከረ ያለው እንደ አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምድሩም፣ ባሕሩም ለአረመኔው ዐቢይ አሕመድ እንዳይገዛ በማውገዝ ቤተ ክርስቲያኗን የሚታደግ አባት በመጥፋቱ ነው።  ቤተ ክርስቲያኗ ማንም የሌለውን አቅም ተጠቅማ  ከጠላቷ ተፈጥሮ ጋር የተመጣጠነ እንቅስቃሴ እስካላደረገች ድረስ  ታሪክ መሆኗና የአረመኔ መጫወቻ ሆና መቅረቷ አይቀሬ ጉዳይ ነው።

Filed in: Amharic