>
5:21 pm - Tuesday July 20, 7294

ባለቤት አልባው መግለጫ፤ በማዘናጊያነት የቀረበ ያሸበረቀ የቃላት ኳኳታ ወይስ …? (ከይኄይስ እውነቱ)

ባለቤት አልባው መግለጫ፤ በማዘናጊያነት 

የቀረበ ያሸበረቀ የቃላት ኳኳታ ወይስ …?

ከይኄይስ እውነቱ

የሰሞኑ ዐቢይ አጀንዳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ የአምሐራ ሕዝብ በተለይ ቀንደኛ ጠላት፣ ኢሕአዴግ የሚባለው የአጋንንት ቡድን ዘላለማዊው አሽከር የሆነው የምውታን ስብስብ የሆነው ብአዴን ‹በጓዳ› ሰጠ የተባለው መግለጫ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ቡድኑ የኔ መግለጫ ነው በሚል በይፋ አልተናገረም፡፡ ከመግለጫው ይዘት በመነሣትና የክልሉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን  ቢሮ በድረ ገጹ ስለለጠፈው ነው የብአዴን የ‹ጓዳ› መግለጫ ያልሁት፡፡ ስለዚህ በድን ቡድን አገራዊ የጥፋት መሣሪያነት ብዙ ብዬአለሁ፤ ብዙም ተብሏል፡፡ በመሆኑም እስካሁን ካለው የኋላ ቆሻሻ ታሪክ በመነሣት እንደማናቸውም ኢሕአዴግ የሚባል የአጋንንት ስብስብ አባል ወሬውንም ሆነ መግለጫውን (ባለቤት አልባ ከመሆኑ አንፃር) ካለማመን መነሣቴ ተገቢና የማምንበትም አቋሜ ነው፡፡ አንድ ሰው ወይም ድርጅት አቋሜ ነው ለሚለው ሐሳብ በባለቤትነት ኃላፊነት ሳይወስድ ባደባባይ ጥሎ መጥፋቱ በራሱ የማይተማመን፣ ወራዳና ቦቅቧቃ መሆኑን ከሚያመለክት በቀር በሕዝብ የፍርድ ዐደባባይ ሞገስንና ዕውቅናን የሚያስገኝ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ተአማኒነትን የሚያሳጣና ከሕዝብ እንዲተፋ የሚያደርግ ተቃራኒ ውጤት የሚያመጣ ነው፡፡

ወገን! በስንቱ ድኩማን እየታለልን እንኖራለን፡፡ ምንም እንኳን ባሁኑ ጊዜ  ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እየሠሩ ካሉ ከሀዲዎችና ዘረኛ ቅጥረኞች ሕዝብን አስተባብሮ ለመታደግ የሚችል የፖለቲካ ድርጅት ባይኖርም፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰው በላ ስለሆነው የዘረኞች ሥርዓት ምንነትና ማንነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተረድቷል፡፡ ይሁን እንጂ ባገዛዙ ላይ የሚያደርገው ትግል ዝርውና ያልተቀናጀ እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ ባንፃሩም የአምሐራውን ሕዝብ የህልውና ተጋድሎ ብሎም የኢትዮጵያን ሉዐላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የተቋቋሙ በርካታ ሲቪል ማኅበራት እንዳሉ ብንሰማም ከጊዜያዊና አስቸኳይ ድጋፍ ባለፈ ዐቅምና ኃይላቸውን አስተባብረው – የጋራ አጀንዳ ቀርፀው፣ የጋራ ፕሮግራምና ስትራቴጂ አዘጋጅተው – የሕዝብን ትግል በተቀናጀ ሁናቴ ለመምራት በኅቡዕም ሆነ በገሃድ ሲንቀሳቀሱ እየታዩ አይደለም፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የዘረኛውን አገዛዝ በቃኝ ያለ፣ እየፈጸመ ባለውም ግፍና በደል በእጅጉ የተንገፈገፈና እስከ መጨረሻው ጠርዝ የተገፋ ሕዝብ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዝናት ይገኛል፡፡ ይህንን በሠራዊት ብዛትና በመሣሪያ ጋጋታ የማይበገር ታላቅ ኃይል ባግባቡ በመምራት አገራዊ ህልውናን እና የሕዝብን አንድነት መታደግ ይቻላል፡፡ የተጠቀሱት ማኅበራት የዓላማ አንድነት እስካላቸው ድረስ የመኖር ህልውናው በእጅጉ ፈተና ላይ የወደቀውን የአምሐራ ሕዝብ ማዕከል አድርገው ሁሉንም የተገፋ ኢትዮጵያዊ በማስተባበር አገራችንን ከአጥፊዎቿ መታደግ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ 

በዚህ ረገድ ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያዊ ምሁራን ከሚያስደነግጥ ዝምታችሁ ወጥታችሁ ኢትዮጵያ-ጠል ከሆነውና ሳያጠፋት ከማይተኛው ሰይጣናዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል እንችል ዘንድ ባንድ ዓላማ የተሰባሰቡ ማኅበራትን በዕውቀት በመደገፍና ትግሉን ፈር በማስያዝ የበኩላችሁን እንድትወጡ በዚሁ አጋጣሚ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ይህን በመንደርደሪያነት ማንሣቴ የኢትዮጵያ ታዳጊዋ ኢሕአዴግ ከሚባለው አጋንንታዊ ቡድን ውጭ መሆኑን በሚገባ ዐውቀን አሁን ባገራችን ካለው ነባራዊ ሁናቴ ለዚህ ዓላማ የሚጠቅመንና እንደ መልካም ዕድል ልናየው የምንችለው ነባራዊ ሁኔታ ካለ ለመፈተሽ ነው፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ምድር ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

 • የጐሠኞቹ አገዛዝ አገሩን መምራት የማይችልበት ደረጃ ደርሷል፤
 • በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር ለማምጣት ዐቅሙም፣ ፍላጎቱም ሆነ ተፈጥሮው (ጐሠኛነት) ስለማይፈቅደለት ቀውስ፣ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር የአገዛዙ ዓይነተኛ መገለጫ ሆኗል፤
 • በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ሰላምና ጸጥታ የለም፤
 • ከሁሉም በላይ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በረሃብና ጠኔ ከሞት ጋር ተፋጥጠው ይገኛሉ፤ ከ10 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የዕርዳት እጆችን እየጠበቁ ይገኛሉ፤
 • አገዛዙ አለኝ የሚለውን የፖለቲካ ካፒታል ሁሉ አጥቷል፤ በሕዝብ ተተፍቷል፤በተለይም የማትነካዋን የኢኦተቤክ ከደፈረ በኋላ ማንነቱ ተጋልጦ ተቀባይነትን አጥቷል፤
 • አገዛዙ በፍርኀት ቆፈን ውስጥ ሆኖ በጐሣና በዓላማ ለሚመሳሰሉት ዘረኞች ድጋፍ ፍለጋ በመሯሯጥ ላይ ይገኛል፤
 • ኢኮኖሚው በአመዛኙ አገዛዝ-ወለድ በሆኑ ችግሮች ተንኮታኩቶ የኑሮ ውድነቱን ኅብረተሰቡ የማይሸከምበት ደረጃ ላይ ከደረሰ ውሎ አድሯል፤
 • መንግሥታዊ ተቋማትና የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ የአገር ሀብት የሚባክንባቸው የአድልዎና የንቅዘት ማዕከላት ከመሆን አልፈው እንደ ጸጥታው፣ ፖሊስና መከላከያው መ/ቤቶች የሰብአዊ መብቶች ማፈኛ ማዕከላት ሆነዋል፤
 • ባገዛዙ ዳተኝነት ብቻ ሳይሆን ሆን ተብሎ በሚደረግም ደባ ዳር ድንበራችን በሰሜን ምዕራብና በደቡብ ምዕራብ በሁለቱ ሱዳኖች ከተያዘ ውሎ ማደር ብቻ ሳይሆን ዜጎች ታዳጊ አጥተው አንድ ኢትዮጵያዊ ጐሣ ማንነቱ ሙሉ ለሙሉ ለመጥፋት ተቃርቧል፤
 • አዲስ አበባ የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ማዕከል መሆኗ ቀርቶ አገዛዙና ምንደኛ አስተዳደሩ የግላቸው መንደር ለማድረግ ግዛቷን ከመቀራመት ጀምሮ በነዋሪዎቿ ላይ ሁለገብ ጥቃትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ በዚህም ባቀናት ባለማት ከተማ ባይተዋር ሆኖ የበዪ ተመልካች ብቻ ሳይሆን ከቤት ንብረቱ በገፍ እየተፈናቀለ መድረሻ አልባ ሆኖ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የምትገኝ ከተማ ሆናለች፤
 • ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊው በነገድና በሃይማኖት ተለይቶ በሕግና በመዋቅር የተደገፈ ጥቃት እየተፈጸመበት፤ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ሥርዓተ አልበኝነት ነግሧል፤

የሕዝብን ብሶትና ተቃውሞ በተደራጀ መልኩ ለመምራት ከተቻለ እነዚህ ለአብነት የተጠቀሱት ምድር ላይ የሚታዩ እውነታዎች የኢትዮጵያን ህልውና ከአጥፊዎቿ ለመታደግ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

ባለቤት አልባ ከሆነው መግለጫ የሚጠበቅ ነገር አለ ወይ? ከኵርንችት በለስ እንጠብቅ?

የመግለጫው ይዘት ባጭር ቃል ሲጠቃለል ‹‹ኢትዮጵያ ሱሴ፤ ስንኖር ኢትዮጵያዊ÷ ስንሞት ኢትዮጵያ›› የሚለውን የቅጥፈት አባቶችን ቃል ባሸበረቁ ቃሎች ለመግለጽ የሞከረ ነው፡፡  ደጋግመን እንደገለጽነው ብአዴን ወያኔ ትግሬ የአምሐራን ሕዝብ ለማጥፋት ጠፍጥፎ የሠራው ባሪያ ነው፡፡ ይህንን ነውረኛ ተግባሩን ባለፉት 27 ዓመታት ወለም ዘለም ሳይል እንደፈጸመ ሁሉ፤ ታማኝነቱን በ5ቱ የሰቈቃ ዓመታት ለአዲሱ ጌታውም በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ብአዴን በኢትዮጵያ ስንክሳር ውስጥ ያስመዘገበውና የሚያስመዘግበው ጉዳይ ቢኖር ፍጹም ነውረኛነት ብቻ ነው፡፡ በጎ ሥራ ያለው ይመስል ‹‹ለጋ ውጤቶቻችንን በማዝለቅ›› የሚለው የመግለጫው ክፍል እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ 

አገዛዙና አመራሮቹ ውሸትና ቅጥፈት የባሕርያቸው ስለሆነ፣ ሎሌው ብአዴንም የዚሁ በንጹሐን ደም የተጨማለቀ ሥርዓት አካል በመሆኑ መግለጫው በአሳዳሪው የተሰጠው ሌላው ሕዝብን ማደናገሪያ ስልት፣ የተዋሕዶ  ልጆች ከቤተክርስቲያናችን ላይ ዓይናችንን እንድናነሳና አድብተውና አድፍጠው ሊፈጽሙ ከሚፈልጉት ከጥፋት ተልእኮአቸው ማዘናጊያ አጀንዳ መስጠት ይመስላል፡፡ አንዳንድ ዥዋዥዌ መጫወት የለመዱ አድርባዮች ለመሣል እንደሚሞክሩት ይህ አከርካሪ አልባ ስብስብ ከራሱ አንቅቶ የተናገረውና ሊተገብረው የሚፈልገው ሐሳብ አለመሆኑን እና ቡድኑም ሕይወት የመዝራት ምልክት አሳይቶ አለመሆኑን ልንረዳ ይገባል፡፡ ከመግለጫው ተነሥቶ ቡድኑን ለማመን ዳር ዳር የሚል ካለ በተለይም በወንዜ ልጅ ስሜት ጭፍን አጋርነትን የሚያሳይ ካለ እሱም የበደነ ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ ብአዴን የሚባለው ቡድን ከአምሐራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና በተቃራኒው አውራጃ፣ ወረዳና መንደር ድረስ የሚቈጥር የለየለት ዘረኛ ቡድን ነው፡፡ ይህንን በተግባር ለማረጋገጥ የሚፈልግ ባሕር ዳር ብቅ ብሎ ከላይ እስከታች ባሉ መንግሥታዊ ተቋማት እና በሚያቋቁማቸው ተቋማት ባንኩን ጨምሮ በገሃድ የሚታይ ነው፡፡ ጐሠኛነትን እንደ ርእዮት እና ይህንኑ ያፀደቀውን ‹የደደቢት ሰነድ› ከተቀበለ ነውረኛ  ድርጅት የሚጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም ብአዴን የራሱን አጀንዳ ይዞ እንደመጣና ዐቅሙን አፈርጥሞ ለመገዳደር የሚያስችለው አቋም የመያዙ ምልክት ሊሆን አይችልም፡፡ አይደለምም፡፡ ባጭሩ የመግለጫው ደራሲ ማን እንደሆነና መልእክቱም ለማን እንደሆነ ከይዘቱ በትርጕም የሚደረስበት ካልሆነ በቀር በኦፊሴል ደረጃ ዕውቅና ያልተሰጠውና ፓርቲያችን በሚሉት ‹በብል/ጽ/ግና› ደረጃ ምንም ዓይነት አስተያየት ያልተሰጠበት ነው፡፡ ስለሆነም ይፋዊ በሆነ መልኩ መግለጫው  ባለቤት አልባ ነው፡፡

በሌላ በኩል ይህ በድን ድርጅት መግለጫውን የጻፍሑት ከራሴ አንቅቼ ነው ካለና ኃላፊነቱን በይፋ ከወሰደ፤ ለተግባራዊነቱ የያዘውን ሥልጣንና መዋቅር ተጠቅሞ ለሕዝብ ጥሪ ያደረገበትን ትግል አግዛለሁ ካለ፣ ቢያንስ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ ሊያሳየን ይገባል፡፡ አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን ቀደም ሲል በተለያዩ ወንድሞች ሲነሱ አድምጬአለሁ፡፡

1ኛ/ የእውነተኛ ተነሣሒ አንዱ መገለጫ በይፋ የፈጸመውን ኀጢአት/ወንጀል ንቅስ አድርጎ ዘርዝሮ ባደባባይ አምኖና ተፀፅቶ የበደለውን ሕዝብ ይቅርታ ለመጠየቅና ለመካሥ፤ ለፍርድ ቀርቦ ተገቢውን ዳኝነት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ፤

2ኛ/ ላገራዊው ምስቅልቅል ከዳረጉን ዐበይት ችግሮች አንዱ ወያኔ ትግሬ የተከለው የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› መሆኑን በይፋ ማመን፤

3ኛ/ አስተዳድረዋለሁ በሚለው ‹ክልል› በእስር የሚያንገላታቸውን በዐሥር ሺዎች የሚቈጠሩ የፋኖ አባላትንና ሌሎች የሕሊና እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፤

4ኛ/ አገዛዙ የራሱን ሕግ ተቃርኖ በኢኦተቤክ እና በኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ጉባኤ የውስጥ ጉዳይ ቀጥታ ጣልቃ መግባቱን እና ተቋማዊ አንድነትና ልዕልናቸውን መዳፈሩን፣ ጥፋት መድረሱን፣ በዚህም አገራዊ ሰላም መደፍረሱን በድጋሚ በይፋ ማውገዝ፤

5ኛ/ በወለጋ፣ በጎጃሙ መተከል፣ በሰሜን ሸዋ በተለይም አጣዬ፣ ኦሮሚያ በሚባለው የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ኦሮሞ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን በተለይም እገዛዋለሁ በሚለው የአምሐራ ሕዝብ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን አረመኔያዊ ፍጅትና በዐሥር ሚሊዮኖች የሚቈጠር ሕዝብ የደረሰበትን መፈናቀል በይፋ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ከእንግዲህ ወዲህ ተመሳሳይ ድርጊት ከተፈጸመ በሚያስተዳድረው ክፍለ ሀገር ያሉትን ታጣቂና ሕዝባዊ ኃይሎች አስተባብሮ በየትኛውም ቦታ የሚገኘውን የአምሐራ ሕዝብ ለመጠበቅ፣ ለመከላከል ያለውን ቊርጠኝነት በይፋ ማሳወቅ፤

6ኛ/ ወያኔ አምሐራ ብሎ ከሰየመው አካባቢ በአውቶቡስ ተጓጉዘው በተለይም ወደ ርእሰ ከተማዪቱ አ.አ. የሚመጡ መንገደኞች ላይ በአገዛዙ ወይም ከአገዛዙ ጋር የዓላማ አንድነት ያላቸው አሸባሪ ቡድኖች የሚፈጽሙትን ግድያ፣ ወደ አ.አ. እንዳይገቡ የሚያደርጉትን ክልከላና እንግልት ከማውገዝ ባለፈ ከእንግዲህ ወዲያ ተመሳሳይ የሽብር ድርጊት የሚፈጸም ከሆነ በኃይል ጭምር ርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንና መንገደኞች ያለምንም መሳቀቅ ወደ ፈለጉበት የአገራችን ክፍል የመዘዋወር መብታቸውን እንደሚያስጠብቅ በይፋ ማሳወቅ፤

7ኛ/ የአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያና የአፍሪቃ ኅብረት መዲናነቷ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በየትኛውም ‹ክልል› በባለቤትነት ያልተያዘች የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ከተማ እና የነዋሪዎቿ መብት ተከብሮ በነዋሪዎቿ አዲሳቤዎች መመራትና መተዳደር ያለባት ራሷን የቻለች ከተማ መሆኗን በቊርጠኝነት በይፋ መግለጽ፤ እንዲሁም የድሬደዋ ከተማ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ከተማ እና በነዋሪዎቿ ድሬዎች መመራትና መተዳደር ያለባት ራሷን የቻለች ከተማ መሆኗን እና የትኛውም ‹ክልል› 40/40/20 በሚል አፓርታይዳዊ (የመድሎ ሥርዓት) የማይቃረጣት ከተማ መሆኗን በቊርጠኝነት በይፋ መግለጽ፤

8ኛ/ ወያኔ/ሕወሓት ከፋፋይ፣ የአገርና የሕዝብን አንድነትን ከመሠረቱ የሚንድ የጐሠኛነትን ሥርዓት በሕግና በመዋቅር በመትከል የኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ በተለይ የትግራይ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላትና አሸባሪ ድርጅት መሆኑን በይፋ መግለጽ፤

9ኛ/ ከፌዴራል እና ኦሮሚያ ከሚባለው ግዛት የመጡ ማናቸውም ታጣቂ ኃይሎችን ብአዴን አስተዳድረዋለሁ ከሚለው ‹ክልል› ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማስወጣት፤ በሕግ ከተፈቀደው ውጭ የትኛውም ክልል በተለይም ኦሮሚያ የሚባለው ‹ክልል› ባለሥልጣናት አምሐራ በሚባለው ‹ክልል› ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ ማድረግ፤ ኦሮሚያ የሚባለውን ክልል ከሚመሩ ኃላፊዎች ጋር የአቻ እንጂ የአዛዥና ታዛዥነት ግንኙነት አለመኖሩን በተግባር ማሳየት፤ 

እነዚህንና ሌሎች አስፈላጊ የሚባሉ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን ከፈጸመ፣ የድርጀቱ አቋም በሕዝብ የፍርድ ዐደባባይ የሚበየን ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የራሱን አመራሮች ለመምረጥ ያልቻለ አከርካሪ አልባ ድርጅት ዓሣማ ክንፍ አውጥቶ ሲበር ካልሆነ በቀር ራሱን ነፃ አውጥቶ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ሊፈጽም አይችልም፡፡

ለማጠቃለል ኢሕአዴግ ከሚባለው አጋንንታዊ ቡድን በኢትዮጵያዊነት ስም በሚመጣ አጀንዳ ዳግም የሚታለል ሕዝብ የለም፡፡ ይህንን አስተያየት ለመስጠት የተገደድሁት ሕዝብን ከአጀንዳ ወደ አጀንዳ እያሸጋገሩ ፋታ ለመንሣትና የትኩረት አቅጣጫን ለማሳት፣ ውስጥ ውስጡን አፍራሽ ተልእኮአቸውን ለመፈጸም በማዘናጊያነት የቀረበ አጀንዳ እንደሆነ ለማሳወቅ እንጂ ከኵርንችት የበለስ ፍሬ ይለቀማል በሚል አይደለም፡፡

Filed in: Amharic