የአምሓራ ህዝብ አንድ እርምጃ ወደ ፊት – እንዴት ይራመድ?
ብርሃኑ ድንቁ
የአምሓራ ህዝብ – መልክዓ-ምድራዊ አሰፋፈሩ ኢትዮጵያ እምብርት ላይ ስላዋለው፣ መግባብያ ቋንቋው አማርኛ መሆኑ፣ ባህሉ አቃፊና እንግዳ ተቀባይ ስላደረገው በተለይም ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ ከአብራኩ የወጡ ልጆቹ አጼ ሆነው ኢትዮጵያን መግዛታቸው – የመሳሰሉት ምስጢሮችና አጋጣሚዎች የባላንጣዎቹን ዓይን ደም አልብሷል፣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ክፉ መንፈስ እንደወረወረባቸው አሳሞችም አቅበዝብዟቸዋል። አሁን ላይ እንደውም ከግራም ከቀኝም፣ ከውስጥም ከውጭም አጀብ ሠርተው ይኽንኑ የፈረደበት አምሓራ ከምድር-ገጽ ለማጥፋት ቀን-ሌት እየዳከሩ ነው።
ምክንያተ-ቢስ ጠላቶቹ፣ የአምሓራ ህዝብ ኢትዮጵያ እስካሁን እንደ ሀገር እንድትቆይ ያደረገውን አስተዋጽዎና ተጋድሎ ዘንግተዋል አለያም ማስታወስ አይፈልጉም። የአምሓራ ህዝብ ግራኝ አህመድ ያደረሰበትን ሰቆቃና ሃይማኖቱን እንዲቀይር የተፈጸሙበትን የማስገደድ ድርጊት ልበቀል ብሎ አልተነሳም ይልቁንም እንደ ጀግና ቆጥሮት እሱ የረገጠውን ቦታ ሁሉ እስካሁን በስሙ ይጠራዋል። የአምሓራ ህዝብ የኦሮሞ ተስፋፊዎች ያደረሱበትን የብልት ሰለባ፣ አዲስ አሰፋፈር እንዲሁም የቦታ ስም ለውጥ ተቀብሎ አስተናገደው እንጂ ለበቀል፣ ለአምባጓሮ ወይንም የቦታ ስሙን ወደነበረበት ለመመለስ ሙከራ አላደረገም። አምሓራ ባለፉት ዘመናት የሆነውን ሁሉ ይሁን ብሎ ተቀብሎ አድራጊዎቹን እንደ ጀግና ቆጥሮ ሁሉን በዝምታ አልፏል።
የአምሓራ ህዝብ ምርኮኞቹን የኢጣሊያ ፋሽስቶችን አልተበቀላቸውም እንደውም “ለእንግሊዞች አሳልፋችሁ አትስጡን” ያሉትን ሸሽጎ ወደ አገራቸው ሲሸኛቸው የፈለጉትን ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ አቆይቶ ዕድል ሠጥቷቸዋል። የአምሓራ ህዝብ ወያኔዎችን እንደ ኢትዮጵያውያን ተመልክቶ ደርግን አብሯቸው ተፋልሞ እስልጣኑ ማማ ሚኒልክ ቤተ መንግሥት አድርሷቸዋል። የአምሓራ ህዝብ ኮሎኔል አብይን እንደ ጻድቅ ቆጥሮ “ለዘለዓለም ምራን” ብሎ መልካም ምኞቱን ገልጾለት መርቆታል። ታዲያ ብዙ መከራን ያስተናገደውና መልካም ያደረገው ደግ ህዝብ ምንድነው ያተረፈው? አምሓራ መፈናቀል፣ ስቃይ፣ ስደት፣ የዘር ፍጅት፣ ወዘተ፣ ይገባው ነበር?
የአምሓራ ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲቀጥልና ኢትዮጵያን መታደግ ከፈለገ አሁን ካለበት “ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚል አባዜ ወጥቶ “መጀመሪያ እራሴን እንዴት ነው የምከላከለው” ሲቀጥልም “እራሴን ካዳንኩ በኃላ ኢትዮጵያን እንዴት እታደጋለሁ” ብሎ ማሰብ አለበት ። የአምሓራ ሕዝብ እኚህን ሃሳቦች ወደ ዓዕምሮው አስገብቶ ማሰላሰል ከጀመረ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ተራመደ ማለት ነው።
እነሆ ዋናው ጥያቄና መልስ ማግኘት ያለበት ጉዳይ “አምሓራ እራሱን እንዴት ያድን ? የሚለው ነው።
ለዚህ ቁልፍ ጥያቄ መልስ ይሆን ዘንድ፣ በመጠኑም ቢሆን በቅደም ተከተል የተዘረዘሩትን፣ የሚከተሉትን ሃሳቦች ማቅረብ ይቻላል።
1/ እያንዳንዱ የአምሓራ ተወላጅ ቆም ብሎ ሁኔታዎችን መመርመር አለበት። ይህ ሁሉ ዘግናኝ እልቂት በምን ምክንያት ተፈጸመብኝ? ከአሁን በኋላስ እንዴት መመከት እችላለሁ? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት።
2/ የአምሓራ ሕዝብ ጠላቶቹን በሚገባ ማወቅ አለበት። ገዳዮቼ፣ አፈናቃዮቼ፣ የዘር ጥቃት አድራሾቹ፣ ወዘተ፣ እነማን ናቸው? ብሎ ሊያሰላስል ይገባል።
3/ የአምሓራ ሕዝብ መደራጀት አለበት።
4/ የአምሓራ ሕዝብ በጋራ መስራት አለበት።
እነዚህን ጽንሠ ሃሳቦች እስኪ ዘርዘር አድርገን እንመልከታቸው።
1/ “ሁኔታዎችን መመርመር አለበት” ሲባል ምን ማለት ነው? ይህ ሁሉ ዘግናኝ እልቂት በምን ምክንያት ነው የተደረገብኝ? ከአሁን በኋላስ ጥቃቱን እንዴት መመከት እችላለሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ ሁኔታዎችን መመርመር ነው።
በአምሓራ ህዝብ ላይ የመጣውን ሰቆቃና እየደረሰ ያለውን እልቂት ብዙ ሰው የተረዳው አይመስልም። ብዙውን ጊዜ በዋል ፈሰስ የሆነ ዓዕምሮ ለምርምር አይዘጋጅም ወይም የጥቃቱን ምክንያትና እንቅስቃሴ አይመረምርም። የዋህ ሰዎች “እዚያ ማዶ ያለ እሳት እኔ ዘንድ አይደርስም” ብለው ይዘናጋሉ።
ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ እሥልጣኑ ወንበር ያደረሰውን የአምሓራን ህዝብ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ያልሞከረው፣ ያልቆፈረውና ያልፈጸመው ግፍ የለም። የአምሓራ ህዝብ ከነህይወቱ ገደል ሲወረወር፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲጨፈጨፍ፣ እንደ ፍጡር ሳይቆጠር በየክልሉ መብት ሲያጣ፣ ከየመንግስት መስሪያ ቤቱ ሲባረርና የትም እንዳይቀጠር ሲደረግ፣ ርስቱ ወደ ሌላ ሲካለል፣ ህክምና እንዲነፈግ ሲደረግ፣ ለረሀብ ሲዳረግ፣ በዚህም በዚያም የትምህርት እድል እንዳያገኝ ሲሻጠርበት፣ ወዘተ፣ ቁጭ ብለን አይተናል።
ይሄ አልበቃ ብሎ በዚህ አምስት አመት ውስጥ የአምሓራ ህዝብ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ሲጨፈጨፍና ንብረቱ ሲወድም፣ ሲቃጠል በቪዲዮ አሳይተውናል፣ በድምጽም ቀድተው አሰምተውናል። ይህ ሁሉ – ዘርን የማጥፋት ድርጊት – እንደሆነ እንደምን ማወቅ ተሳነን? ወይንስ ደግሞ “እኔ ላይ ካልደረሰ ምን አገባኝ” እያልን ነው? ምንም ሆነ ምንም – ብቻ ግን ጥቃቱና አግጦ የመጣው ዘርን የማጥፋት ፍጅት ማንኛችንንም አይምርምና – እንዴት ነው መመከት የሚቻለው? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል። ጥያቄው በራሱ 50 በመቶ መልስ ነውና ይሄን ማሰላሰል ከጀመርን ከዚህ ቀጥሎ ወደማነሳው ሌላ ሃሳብ መሸጋገር እንችላለን። ለመሆኑ ማነው ይሄን ሁሉ ጥቃት ካለአንዳች ከልካይ የሚፈጽመው? ማነው ጠላቴ?
2/ የአምሓራ ሕዝብ ጠላቶቹን ማወቅ አለበት
የአምሓራ ህዝብ ጠላቶች ዘርፈ ብዙ ናቸው። ዋናውና በቅድሚያ ሊታወቅ የሚገባው በአብይና በኦነግ የሚመራው ኦሮሙማ ቡድን ነው። ይሄ ቡድን “ታላቂቷን ኦሮሚያ” የመመስረት ቅዠት ቢላበስም ቅሉ ነገር ግን ይሄ ቅዠቱ አምሓራ እስካለ ድረስ ቅዠት እንጂ እውን እንደማይሆን ስለተገነዘበ፣ የአምሓራን ህዝብ ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት አለያም አስፈላጊውን ሁሉ አድርጎ አምሓራ በአምሓራነት እንዳይደራጅና ተገዳዳሪ እንዳይሆንበት በግልጽና በስውር ይሠራል። እውነት አልባው ኦሮሙማ – ርዕዮት ወይንም ጥልቅ ሃሳብ ስለሌለው መስፈንጠርያው “ማሳመን ወይንም ማወናበድ” የተባለው ከንቱ ወግ ነው።
ሌላኛው የአምሓራ ሕዝብ ጠላት ወያኔ ነው። ወያኔ አምሓራን አዳክሞ ኦነግን ለዚህ ያበቃ የአረመነኔት ሁሉ ጫፍ ነው። ወያኔ ልክ እንደ ኦሮሙማው ቡድን ታላቅዋን ትግራይን ለመመስረት ካሰበ ዘመናት አልፈዋል። ወያኔ አጋጣሚ ሆኖበት የአምሓራ ህዝብ ጎረቤት በመሆኑ ሕልሙ ከቶ ሊሳካለት አልቻለም። በማንኛውም አጋጣሚ ወያኔ የአምሃራውን ይዞታ ራያንና ወልቃይትን ወስዶ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እንቅፋት የሆነበትን አምሓራንም ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት ቀን ከሌሊት ይጥራል።
ሶስተኛው የአምሓራ ሕዝብ ጠላት በሆዱ ምክንያት አሽርጋጅ የሆነውና በአስተሳሰብ ድህነት የላሸቀው “የአምሓራ ብልጽግና” ተብዬው ስብስብ ነው። ይሄ ስብስብ አምሓራ በአምሓራነቱ እንዳይደራጅ ዕለት ለዕለት የሚዳክሩ ከሃዲዎችን ያቀፈ ከመሆኑም በላይ አድፍጦ ብቅ ያሉትን ጀግና የአምሓራ ልጆች የሚገድል፣ አስሮ የሚያሰቃይ ወይም አሳልፎ ለወዳጁ ለኦሮሙማው ቡድን የሚያስረክብ አጎንባሽ ድርጅት ነው። ይሄ መዥገር ቡድን እውስጣችን ስለተጣበቀ በጥንቃቄ ነው መነቀል ያለበት።
ሌሎቹ የአምሓራ ጠላቶች “ኢትዮጵያዊ ነኝ – በአምሓራነት መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን ያፈርሳል” ብለው የሚለፍፉት ተላላ እና ተመጻዳቂ ቡድኖች ናቸው። ተላሎቹ የዚህ ቡድን ስብስቦች በአምሓራነት የተደራጁትን እየነቀፉ በሌላ በኩል ግን በፀረ አምሓራነት ለተደራጁት እውቅና ይሠጣሉ። የዚህ ቡድን አባላት የምክንያት ድህነት ስለሚያጠቃቸው ማንም ፍጡር የመጣበትን ችግር ለመቋቋምና ጥቃትን ለማስወገድ በተለያየ መልኩ መደረጀቱ ተፈጥሯዊ መሆኑን አይቀበሉም። በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰው ልጅ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በሙያ፣ በሰፈር፣ በሃገር፣ በጎሳ፣ በፖለቲካ፣ ወዘተ፣ ይደራጃል።ታዲያ ይሄን ቢያውቁም እነዚህ ተላላና የአስተሳሰብ ደሃዎች አምሓራ መደራጀት አለበት ተብለው ሲጠየቁ – “አይ በጎሳ እየተደራጃችሁ ሃገር እንዳታጠፉ” በማለት መልሰው ይወቅሳሉ። የሚያሳዝነው እመጥፋቱ አፋፍ ስላለችው ኢትዮጵያ እንኳን ግንዛቤአቸው ጨንግፎ ገና መሬት ሊገዙ ቤት ሊገነቡ ያስባሉ። ሌሎቹ ብልጣብልጦቹና ተመጻዳቂዎቹ ስብስቦች – ኦሮሙማ ብብት ውስጥ ተወሽቀው ከጥቅሙ እየተቋደሱ፣ ከዝርፊያው እየተካፈሉ – “ኢትዮጵያ – ኢትዮጵያ” እያሉ የሚሸነግሉት ናቸው። እንዲህ ዓይነቶቹ መሠሪዎች አገሪቱን ማዋረዳቸው ሳያንስ የአምሓራው ዘር እንዲጠፋ ከጠላቶች ጋር ተባባሪ መሆናቸው የሚታወቅባቸው እንኳን አይመስላቸውም።
ውድ የአምሓራ ህዝብ ሆይ! ይሄን ሁሉ ጠላት እጭንቅላትህ ላይ አስቀምጠህ “ሁሉም ያልፋል” ብለህ ብታላዝን ጠላቶችህ አይተኙልህምና ከተኛህበት ነቅተህ አንድ እርምጃ ወደፊት ልትራመድ ይገባሃል። እንዴት? ለሚለው ጥያቄ የሚቀጥለው ሃሳብ አቀርባለሁ።
3/ የአምሓራ ሕዝብ መደራጀት አለበት
መደረጀት ተፈጥሮ ለፍጡራን የለገሰችው የመጀመርያ ደረጃ ጥቃትን መመከቻ ዘዴ ነው። የአምሓራ ህዝብ በዘመኑ የተዳረገበትንና በመሬት መንቀጥቀጥ ሳብያ እንደሚከሰት የውቅያኖስ ማዕበል ያክል ገዝፎ የሚወረወረውን ዘሩን የማጥፋቱን ድግስ ተደራጅቶ በጊዜ ካልመከተ በሌሎች ህዝቦች ማለትም በእሥራኤሎችና አርመኖች ላይ የደረሰው ዓይነት ተመሳሳይ የዘር ዕልቂት አያጋጥመውም ማለት ዘበት ነው። ስለዚህ አምሓራ ሆይ ተድራጅና ራስህንም ወገንህንም አድን።
በእርግጥ መደራጀት በአንድ ጀንበር የሚያልቅ ጉዳይ አይደለም። መደረጀት ጊዜ ይወስዳል፣ ጥንቃቄ ይጠይቃል፣ ትልቅ ትዕግስት ያሻዋል፣ ብልኅነትንም ይፈልጋል። መደራጀት ከሁሉ በላይ ደግሞ ቆራጥነት ግድ ይለዋል። ድርጅት በትንሽ ቁጥር ይጀምራል። እነሆ በትንሽ ቁጥር የተጀመረ ማህበር እንደ አስፈላጊነቱ ሊያድግ ይችላል። የቁጥር መብዛት እንደ ግብዓት መታየት የለበትም። ቁም ነገሩ መሬት የረገጠ ድርጅት እንዲሆን ማስቻሉ ላይ ነው። መደራጀታችንን የማይፈልጉ ከራሳችን ጉያ የወጡ ወንድም እህቶቻችን ስላሉ እጅግ እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ መሠራት አለበት። በተለይ “ለምን እንዲህ አይሆንም፣ ለምን እንዲህ አይደረግም ፣ እንዲህ ካልተደረገ ዋጋ የለውም” ወይንም እኔ ካልመራሁት አይሆንም – እኔ ነኝ አዋቂ ከሚሉ ሰዎች መራቅ ያስፈልጋል። በመሠረቱ አንዳንዶች እውቀት ቢኖራቸውም በተፈጥሯቸው ድርጅት የማይሹ ወይንም ማህበር አፍራሾች ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ድርጅት መሰናክልና እንቅፋት ባይለዩትም እንኳን ሠርጎ ገቦችን፣ ክፍፍል ጠንሳሾችንና አንጃ ፈጣሪዎችንና በተጻራሪ የቆሙትን ማጥራት ይጠበቅበታል። አደረጃጀት መሬት ከረገጠና ተግባብቶ መስራት ከተጀመረ አባላትን የማብዛት ተልዕኮ ማከናወን ይቻላል። ከላይ እንደተገለጸው ችግሮች ባይታጡም ድርጅቱ ሥር ከሰደደና ፈር ከያዘ በኋላ ማንም በቀላሉ ሊያፈርሰው አይችልም። በትንሽ በትንሹ የመደረጀቱ ጉዳይ በዓለም ዙርያ ከሠመረ በኋላ እነሆ በርካታ አምሃራዎች በጋራ ተግባብቶ ለመስራት ጥረቱን እናጎለብታለን።
4/ የአምሓራ ሕዝብ በጋራ መሰራት አለበት
ንብና ጉንዳን እንዲህ ሊጠነክሩ የቻሉት በጋራ መሥራት በመቻላቸውና ሥራዎችን በአግባቡ ስለሚከፋፈሉ ነው። አምሓራዎች በቡድን በቡድን መደራጀትን አገባደው ሲያበቁ መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ደግሞ ሥራዎችን ተከፋፍለው በጋራ መሰራት ይጠበቅባቸው። ዓላማዎች፣ እቅዶች፣ ትዕዛዞችና ድርጊቶች ከአንድ አቅጣጫ ወደ ታች ወርደው አባላት በቅጡ ሊተገብሯቸው ይገባል። በመሆኑም በአለም ላይ ያለውን አደረጃጀት አንድ አርጎ የሚመራ የበላይ አካል ያስፈልጋል። እስካሁንም ካለ እሰየው እሱን መቀላቀል ይቻላል።
ዘላቂ ስትራቴጂዎችን ከግቡ ለማድረስ አምሓራ በአንድ ትልቅ ማህብር ሥር ተደራጅቶ በትጋት መሥራት ይጠበቅበታል። ፋኖን አንድ የማድረጉን ትልም እንዲሁም የወልቃይትና የራያ ሁኔታ ሁላችንም በጋራ ልንሸከመው የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ። ምን ጊዜም ቢሆን ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩም ሆነ ቤንቺ ማጂ ዞን አልያም የትም ቦታ ቢሆን የሰው ልጅ ፍጅት ሲደርስ ሁላችንም ጥቃቱን በጋራ መከላከል ይኖርብናል። በተጨማሪም የተፈናቀሉትን በጋራ መደገፍ፣ የአምሓራውን ስቃይ ለአለም ህዝብ ማሳወቅና ግፈኞችን ለፍርድ የማቅረቡን ሥራ በጋራ መወጣት ይኖርብናል። አባላት አንድ የጋራ ሜዲያ የማቋቋሙንም ዕቅድ ሊያስቡበት ይገባል።
ወገኖቼ! ከላይ የጠቀስናቸውን ሁሉ በጥሞና ተገንዝበን ለተግባራዊነቱ በጋራ ከተነሳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እናመጣለን። እንኳንስ በአንድ ላይ መሥራት ጀምረን ይቅርና አሁንም ቢሆን ገና ለገና በአለም ዙርያ መደራጀት ስለ ማሰባችን ሲሰማ ጠላቶች የቱን ያህል መደናገጣቸውን እየታዘብን ነው። እምነትና ቃልን አክባሪነት የአምሓራ ሕዝብ መለያዎቹ ናቸው። አምሓራ የሚደራጀው እንደ ድሃጣኖቹ ስልጣን ለመያዝ ወይንም ለመገንጠል አይደለም። አምሓራ የሚደራጀው “አትንኩኝ በሰላም ልኑርበት” ብሎ ተፈጥሯዊ መብቱን ለማስከበር ብሎም ኢትዮጵያን ለማዳን ነው።
አምሓራዎች እንደራጅ – ህዝባችንን ከእልቂት እናድን ኢትዮጵያንም ከመፍረስ እንታደጋት።