>
2:21 am - Tuesday March 28, 2023

ኢትዮጵያ የግፍ አገር ሆናለች (ከብርሃኑ ዘርጋው)

ኢትዮጵያ የግፍ አገር ሆናለች

ከብርሃኑ ዘርጋው


ጠቅላይ ሚኒስትሩን ገና በተዋወቅናቸው በዛ በሩቅ አምስት አመት የኢህአዴግን ግፍ እንደተጸየፉና ብዙ ስህተቶችን እንደሰራ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ይቅርታ እንዳደረገለት ደግሞም ወደ ለመለመው የብልፅግና መስክ እንደ ሙሴ ያን የመከራ ባሕር አቋርጠን እንድምንሄድ ሲነግረን ምን ያህሎቻችንን ቀልባችንን እንደሳበ ቤቱ ይቁጠረው:: የኢትዮጵያ ህዝብ ከልቡ የወደደው አምኖም ተስፋ የጣለበት መሪ ነበር ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም:: ቀኑ እየገፋ ወደ ምሽቱ ሲገባ አቢቹን እንደትኩስ ድንች ከአፉ እየተፋ ከተወዳጅነቱ ይልቅ መናቁ እየጨመረ ሄደ:: ኢትዮጵያም ሰላምና ደህንነት የጠፋባት አገ ሆነች:: እሱም ለዛፍ ተከላ አሳቡንና ጊዜውን ሰጠ:: ከአገር ሰላምና ደህንነት ይልቅ ስለመበልጸግና ስለእድገት መስበኩን ቀጠለ:: ሞት በዛ:: ለፍትህ መቆም ቀረ::

እስር ቤቶች በተለይ ስርአቱን በሚቃወሙ ሰዎች ተሞሉ:: እነታድዮስ ታንቱና የፍትህ መፅሄት አዘጋጁ ተመስገን ደሳልኝ መስከረም አበራም ተጠቃሽ ምሳሌ ናቸው::ጦርነቱ ከሚሊዮኖች በላይ ህይወት የቀጠፈ እንደሆነ እየታወቀ ማን ተጠያቂ መሆኑ ሳይታወቅ እርቅ ወረደ ተባለ:: የሞተው የተጎዳው ንብረቱና ሃብቱ ፈርሶ መኖሪያ አጥቶ በትግራይ በአማራና በአፋር የተፈናቀለው ሁሉ የሰው ልጅ መሆኑ ተረሳ:: ይባስ ብሎ ከሞተው ባልተናነስ ከኦሮሞ ክልል የሚፈናቀለው የሚሞተው አካሉ የሚጎድለውና በቀን በሌሊት የሚሰደደው ኢትዮጵያዊው በተለይ አማራው ቁጥሩ እጅግ በዛ:: ዲሞክራሲ መደለያ መሳሪያ የጉልበትና የማን አለብኝነት መገለጫ በመሆኑ ክልል እንድንሆን ህገ መንግስታዊ መብታችንን እናስከብራለን የሚሉ የወላይታና የጉራጌ ብሔሮችን አፈነ: አሰረ ደግሞም ገደለ:: በዚህ ሁሉ ችግር ላይ ኢትዮጵያ ዘር አይውጣልሽ የተባለች ይመስል ልጆቿ ሲጠለፉ ሲገረፉና ከእርጉዝ ሆድ ተዘንጥለው ሲወጡ ለፍትህ የሚሮጥ ለደህንነት የሚታገል የመንግስት አካል ሊደርስ ያለመቻል ብቻ ሳይሆን ፍላጎቱም አልታየም::

ጠቅላዩም ያው እንደለመዱት ባለሙያተኞችን እየሰበስቡ እንዴት ሃብታም ሊኮን እንድሚቻል መስበካቸውን አላቆሙም:: ይህ ሲሆን በአይናቸው ስር የኢትዮጵያን ያሁኑን መጥፎ ገጽታ የሚያንፀባርቁ ሁነቶች በሁለት ሴት ህጻናት ተንጸባረቁ:: የመጀመሪያዋ አማራ በመሆኗ አማራ ጠል የኦሮሞ ነፃ አውጭ ነን ባዮች ሊገሏት ሲሉ “ሁለተኛ አማራ አልሆንም” ማለቷ:: ያም ቢሆን ከሞት አላተረፋትም:: ትንሽ ልጅ መሆኗ ሴት ልጅም መሆኗ ለገዳዮቿ ብቻ ሳይሆን ከአገር መሪ ጀምሮ እስከ የአካባቢው አስተዳደሮች ላይ ያመጣው ጸጸት ወይም የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ያስገባ አልነበረም:: በቅርቡም ከአድዋ በአል አከባበር ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተደረገ የመንግስት ሃይሎች የጭስ ቦንብ ፍንዳታ “አይዟችሁ አትሽሹ ፈረስኛው ጊዮርጊስ ይደርስላችሁዋል” ያለችው ትንሽ ልጅ ናት:: በቤተ ክርስቲያን ላይ ከሰሩት የከሸፈ ሴራ ሁዋላ ቤተክርስቲያን ገብቶ ይህን ታሪክ የማይረሳውን ድፍረት መፈጸም አብይ የሚመራው ስርአት ከድሮው ያልተለወጠና ለአብይም የተሰጠው የሙከራ ጊዜ እንዳበቃ  የሚያመለክት ነው:: ወደ ዋናው ቁም ነገር ስንመለስ ኢትዮጵያ ታዳጊ ልጆቿን መጠበቅ የማትችል የግፍ አገር ሆናለች::

ከዚህ በፊት ያለፈቃዳቸው የተጠለፉ የኮሌጅ ተማሪዎች ጉዳይ የት ደረሰ?

በኦሮሞ ምድር ስለተገደሉ ታዳጊዎች ማን ጥብቅና ቆመ? ከዛስ አልፎ የአእምሮ ሁከትና ጭንቀት በነዚህ ነውጦች ምክንያት ለሚፈፅምባቸው ህጻናት ህክምናና  ምክር ተሰጥቷል? በኢትዮጵያ ምንም አይነት የሰላምና የደህንነት ዋስትና የሚሰጥ መንግስት የለም እስከሚባል ደርሰናል:: ይህም አስተሳሰብ ነገ ሊፈነዳ የሚችል የተቀበረ ብሶት ፈንጂ ነው:: ስለዚህ ህዝብ የህግን ጉዳይ በራሱ መንገድ ለመወጣት በሚችለው መንገድ በመታጠቅና ራሱንና ቤተሰቡን ከጥቃት መከላከል ቢጀምር ለሚፈጸመው እልቂት ተጠያቂው የአብይ መንግስት በየተዋረዱ ይሆናል:: የመንግስት ተቀዳሚ አላማ የህዝብን ደህንንት ማስጠበቅ ሲሆን አብይ ለምንድነው በዚህ ጉዳይ ላይ ቸል ያለው? ቸልታ ወይስ አቅምና ችሎታ ማጣት? ታዲያ ይህ እኮ አዲስ መሪና አዲስ መንግሥት የሚያስመሰርት ጉዳይ ነው:: ልብ እንዲሰጥህ ቸሩ አምላኬን እለምናለሁ:: እስከዛው ግን በጎችህን ጠብቅ:: አደራው ባንተ ነውና:

Filed in: Amharic