አቶ ልደቱ አያሌው፤ ፖለቲከኛ ወይስ ፖለቲካ ተንታኝ?
መስፍን አረጋ
ፖለቲከኛ ማለት የስልጣን ወይም ሌላ ግብ ያለው፣ ይህን ግቡን ለመምታት እስካስቻለው ድረስ ደግሞ ማናቸውንም ፖለቲካዊ ዘዴ ለመጠቀም የማያቅማማ የፖለቲካ ሰው ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ፖለቲከኛ ማለት ለዱቄቱ እንጅ ላፈጫጨቱ የማይጨነቅ፣ ፖለቲካዊ መርሑ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጨው (the end justifies the means) የሆነ የፖለቲካ ሰው ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል ጭራቅ አሕመድ የተዋጣለት ኦነጋዊ ፖለቲከኛ ነው፡፡ የጭራቅ አሕመድ ኦነጋዊ ግብ ደግሞ የአማራን ሕዝብ እና አማራዊ ናት የሚላትን ጦቢያን ድምጥማጧን አጥፍቶ ባማራ ሕዝብና በጦቢያ መቃብር ላይ የኦሮሞን አጼጌ (empire) መገንባት ነው፡፡ ወደ ግቡ ማምራት የሚችለው ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚችለው ደግሞ ጦቢያን የሚወደው ያማራ ሕዝብ በነቂስ ከደገፈው ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ያማራን ሕዝብ በማታለል ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ሲል ብቻ፣ የሆዱን በሆዱ ይዞ፣ አምረሮ የሚጠላትን ጦቢያን አበክሮ አወደሳት፡፡ የሚጠላውን በማድረግ የሚወደውን አገኘ፡፡ የሚወደውን ከያዘ በኋላ ደግሞ የያዘውን በመጠቀም የሚጠላውን ለማጥፋት ቆርጦ ተነሳ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፖለቲካ ተንታኝ ማለት ሊተገበሩ መቻል አለመቻላቸው ላይ ሳይጨነቅ የተለያዩ የፖለቲካ ሐሳቦችን በስፋት የሚተነትንና ባማራጭነት የሚያቀርብ የፖለቲካ ሰው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የፖለቲካ ተንታኝ ሲባል የፖለቲካ ተዋሪ (theorist) እንጅ የፖለቲካ ተግባረኛ (practicalist) አይደለም፡፡ የፖለቲካ ተዋሪ በመሆኑ ደግሞ ይበልጥ የሚያተኩረው ለሰሚው በሚያስደሰቱ፣ ነባራዊ ሁኔታወችን ያላገናዘቡ በመሆናቸው ግን ሊተገበሩ በማይችሉ ተምኔታዊ (utopian, idealist) የፖለቲካ አማራጮች ላይ ነው፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ተንታኝ ሥራ በየሚዲያው እየቀረበ ስለ ፖለቲካና ፖለቲከኞች መተንተን እንጅ፣ ፖለቲካዊ ተከታዮችን አፍርቶ የፖለቲካ ትግል በማደረግ ከፖለቲካዊ ግብ መድረስ አይደለም፡፡
በዚህ ረገድ ስናየው አቶ ልደቱ አያሌው የፖለቲካ ተንታኝ እንጅ ፖለቲከኛ አይደለም፡፡ አንድም ፖለቲካዊ ተከታይ ሊያፈራ ያልቻለውም ፖለቲካዊ ሐሳቦቹ ነባራዊ ሁኔታወችን ያላገናዘቡ በመሆናቸው ምክኒያት ወደ ምድር ወርደው ተግባራዊ በመሆን ሕዝብን በነቂስ ማነሳሳት የማይችሉ ባዶ ሐሳቦቸ በመሆናቸው ነው፡፡
አቶ ልደቱ አንድም ፖለቲካዊ ተከታይ ስለሌለው ምንም ፖለቲካዊ አቅም የሌለው የፖለቲካ ተንታኝ ነው፡፡ ጭራቅ አሕመድ ደግሞ አያሌ ፖለቲካዊ ተከታዮች ስላሉት ከፍተኛ ፖለቲካዊ አቅም ያለው ፖለቲከኛ ነው፡፡ ስለዚህም አቶ ልደቱ ጭራቅ አሕመድን “ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር” እያለ በሚያሳፍር ሁኔታ ከመለማመጥ በስተቀር በምንም መንገድ ሊገዳደረው አይችልም፡፡
አቶ ልደቱ የፖለቲካ ተንታኝ እንጅ ፖለቲከኛ ላለመሆኑ ከቅንጅት አብዮት በላይ ምስክር የለም፡፡ የቅንጅት አብዮት የመጀመርያው ዋና ግብ የጦቢያን ነቀርሳ (ወያኔን) መንቀል ነበር፡፡ ስለዚህም አቶ ልደቱ ፖለቲከኛ ቢሆን ኖሮ፣ ከግቡ ላይ ብቻ አተኩሮ፣ የነ ዲባቶ (doctor) ብርሃኑን ሸፍጥ ለጊዜው ችላ ብሎ፣ ወያኔን ለመንቀል ማድረግ የነበረበትን ሁሉ አድርጎ፣ መፈረም የነበረበትን ሁሉ ፈርሞ ግቡን ይመታ ነበር፡፡ ወያኔን ከነቀለ በኋላ ደግሞ እነ ዲባቶ ብርሃኑን ቀስ በቀስ በማራገፍ ቅንጅትን ከኢሕአፓ ሸፍጠኞች ሙሉ በሙሉ አጽድቶ፣ በራሱ እጅ አስገብቶ፣ በራሱ መንገድ ሊቀርጸው ይችል ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ባይችልም እንኳን፣ ወያኔን ለመንቀል ያንበሳውን ሚና በመጫወቱ ብቻ የጦቢያና የጦቢያውያን ዘላለማዊ ጀግና ይሆን ነበር፡፡ አቶ ልደቱ ግን ግብ ያለው ፖለቲከኛ ሳይሆን ግብ የሌለው የፖለቲካ ተንታኝ ስለሆነ፣ ዓይኑን በወያኔን ላይ ከማድረግ ይልቅ እነ ብርሃኑ በሚፈጽሙበት ተራ ሤራ ላይ አድርጎ፣ እነ ብርሃኑን የጎዳ መስሎት የቅንጅትን አብዮት በማክሸፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ በእጅጉ ጎዳ፣ የጦቢያ ሕዝብ ደግሞ ዓይንህን ላፈር አለው፡፡
በሌላ በኩል ግን ጭራቅ አሕመድ እንደ አቶ ልደቱ ግብ የሌለው የፖለቲካ ተንታኝ ሳይሆን ግብ ያለው ፖለቲከኛ ነው፡፡ ግቡ ደግሞ ወያኔን ጥሎ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ኦነጋዊ አጀንዳውን ማስፈጸም ነው፡፡ ስለዚህም ሙሉ ትኩረቱ በግቡ ላይ ስለሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሚሆን ድረስ ኦነጋዊ አጀንዳውን በጽኑ ከሚቃረኑት ከነ ዶክተር አምባቸው ጋር በመተባበር በነሱ ወሳኝ ደጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ በኋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ የሰጠውን ከፍተኛ ኃይል ተጠቅሞ እነዲባቶ አምባቸውን ረሽኖ አስወገዳቸው፡፡
በመድገም አጽንኦት ለመስጠት ያህል፣ አቶ ልደቱ ግብ ያለው ፖለቲከኛ ሳይሆን ግብ የሌለው የፖለቲካ ተንታኝ ነው፡፡ ባለመታደል ግን አቶ ልደቱ ራሱን የሚያየው እንደ ፖለቲካ ተንታኝ ሳይሆን እንደ ፖለቲከኛ አድርጎ ነው፡፡ አቶ ልደቱ ራሱን እንደ ፖለቲካ ተንታኝ ሳይሆን እንደ ፖለቲከኛ ማየቱ የሱ የራሱ ጉዳይ ስለሆነ እኔን አያስጨንቀኝም፡፡ እኔን የሚያስጨንቁኝ አቶ ልደቱን እንደ ፖለቲካ ተንታኝ ሳይሆን እንደ ፖለቲከኛ እየተመለከቱ፣ ያቶ ልደቱን ሊተገበሩ የማይቸሉ ፍሬከርስኪ ሐሳቦች እንደ ዋና ፖለቲካዊ አማራጭ የሚወስዱ አማሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አማሮቸ ሙሉ ትኩርታቸውን የሚያደርጉት ሊተገበሩ በማይችሉት ያቶ ልደቱ ተምኔታዊ ሐሳቦች ላይ ብቻ ስለሆነ፣ ከወሬ በቀር ምንም መተግበር አይችሉም፡፡ ስለዚህም አቶ ልደቱ ራሱን እንደ ፖለቲካ ተንታኝ ሳይሆን እንደ ፖለቲከኛ አድርጎ በማቅረብ፣ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ አማሮች ወያኔንና ኦነግን በወሬ ብቻ እንጅ በተግባር እንዳይታገሉ እያደረጋቸው ነው፡፡
በዚህ ረገድ ሲታይ፣ አቶ ልደቱ ያማራ ሕዝብ የሕልውና ጠላቶች የሆኑትን ወያኔንና ኦነግን በቀጥታም ባይሆን በተዛዋሪ የሚያግዝ ያማራ ሕዝብ የሕልውና ጠላት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ አቶ ልደቱ ከተደበቀበት እየወጣ በወያኔና በኦነግ ሚዲያወች ላይ በመቅረብ ትንታኔውን የሚተነትነው ያማራ ሕዝብ ትግል በተግባራዊ መንገድ ተቀጣጥሎ ወያኔንና ኦነግን ሊያቃጥላቸው ሲል ነው፡፡ ይህን ስታዝብ ደግሞ ያቶ ልደቱ ሙሉ ጥረት የአማራን ሕዝብ ውጤታማ ትግል አቅጣጫ በማስቀየር፣ ምንም ውጤት ወደሌለው ወደ ወሬ ትግል መለወጥ ይመስልኛል፡፡ አቶ ልደቱ እነ ጃዋርና ደብረጽዮንን ለመሰሉት ፀራማራ ጽንፈኞች የሚሰጠውን ከፍተኛ ክብር እነ ፕሮፌሰር አሥራትን ጨምሮ ያማራ ብሔርተኞች ናቸው ለሚላቸው ሰወች የሚያሳየውን ግልጽ ንቀትና ጥላቻ ሳስተውል ደግሞ፣ የግለሰቡን ማንነት በተመለከተ ወደማልፈልገው ድምዳሜ ሳልወድ በግዴ ማምራት ይቃጣኛል፡፡ ያማራ የሕልውና ጠላቶች የሆኑትን ወያኔንና ኦነግን በበጎ ዓይን እየተመለከተ በእከክልኝ ልከክልህ መንፈስ ያማራን የሕልውና ትግል ሊያግዝ የሚችለውን የኤርትራን መንግሥት ነክሶ መያዙ ደግሞ ድምዳሜየን እያጠናከረልኝ እቸገራለሁ፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ አቶ ልደቱ ማለት ያማራ ሕዝብ ወያኔንና ኦነግን ዐመድ ለማድረግ በትግሉ በሚያቅጣጥለው እሳት ላይ ውሃ እየጨመረ፣ አውቆም ሆነ ባለማውቅ ወያኔንና ኦነግን የሚያግዝ፣ በሐሳቡ ባይሆንም በምግባሩ ፀራማራ የሆነ ግለሰብ ነው፡፡ ስለዚህም ያማራ ሕዝብ ሕልውናውን መታደግ የሚችለው ላቶ ልደቱ ኢተግባራዊ እንቶ ፍንቶ ጆሮውን ባለመስጠት፣ እንዲሁም አቶ ልደቱ አውቆ የተኛውን ጭራቅ አሕመድን ለመቀስቀስ የሚጽፋቸውን ግልጽ ድብዳቤወች ንቆ በመተው፣ ወያኔንና ኦነግን \በሚገባቸውና\ /በሚገባቸው/ ቋንቋ እያናገረ በተግባር ሲታገላቸው ብቻ ነው፡፡
ላማራ ስለሆነም ለጦቢያ ሕልውና እንታገላለን የሚሉ ሚዲያወች ደግሞ፣ ባሁኑ ነባራዊ ሁኔታ ጦቢያን ለማዳን ያንበሳውን ድርሻ መጫወት የሚችለውና ያለበት ያማራ ሕዝብ መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ በዚህ መረዳታቸው መሠረት ደግሞ ሙሉ ትኩረታቸውን ያማራ ሕዝብ በሚያደርጋቸውና ሊያደርጋቸው በሚገባ ተግባራዊ የትግል ፈርጆች ላይ ብቻ ማዋል አለባቸው፡፡ ስለዚህም አቶ ልደቱን በየጊዜው እየጋበዙ ያማራን ሕዝብ ከውጤታማ ትግሉ እንዲያናጥብ መድረክ መስጠት፣ የትግላቸውን ዓላማ በፅኑ የሚፃረር መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡
መስፍን አረጋ
mesfin.arega@gmail.com