በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የባልደራስ ፓርቲ የአቋም መግለጫ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ለመጋቢት 3/2015 ዓ.ም. ሊያደርግ አቅዶ የነበረው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ በኦሮሚያ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት ሊሳካ አለመቻሉ ይታወቃል፡፡ በእናት ፓርቲ እና ጎጎት በተባለው የጉራጌ ፓርቲ ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው መንግሥታዊ አፈና በኢትዮጵያ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማቆጥቆጥ ተጥሎ የነበረውን ተስፋ ሙሉ በሙሉ ያጨናገፈና ጎጠኛ እና ፅንፈኛ የሆነው የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና ፓርቲ አምባገነናዊነት መስፈኑን የሚስረግጥ ተጨባጭ ድርጊት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 6/2015 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ ይኸንኑ ሃቅ ያጠናከረ ነው፡፡
በ2013 ዓ.ም. የወጣው የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስር የሚገኙ የስብሰባ ቦታዎችና አዳራሾችን ያለ አድልኦ ሁሉም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረጊያ ክፍት እንዲሆኑ የመፍቀድ ግዴታ እንዳለበት ቢደነገገም፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ ይኽ እድል ሲሰጥ የቆየው ከብልፅግና ጋር ተቀራራበው ለሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንጂ ለሌሎች ፓርቲዎች ይኼ መብት እንደተነፈገ ነው የሚታወቀው፡፡ በመሆኑም ለወደፊቱ ባልደራስም ሆነ ከተለጣፊነት ነፃ የሆኑ ሌሎች ፖርቲዎች የዚህ መብት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል የሚል እምነት አለን፡፡
የከንቲባዋ የዘር ፍጅት ጥሪ እና አዲስ አበባ
ወ/ሮ አዳነች አበቤ ሰሞኑን ለአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር “በምርጫ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ አዲስ አበባ ውስጥ ከአማራ ክልል በብዛት እየተሰደዱ በሚመጡ ወጣቶች የመንግሥት ግልበጣ ለማድረግ ሴራ እየተጠነሰሰ ነው።” በሚል አንድ ማኅበረሰብን ነጥሎ ለጥቃት እንዲዳረግ የሚያነሳሳ ዘረኝነት የተጠናወተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ይህ ዓይነት ንግግር የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና የኦሮሙማ መንግሥት በአማራው ማህበረሰብ ላይ ያለውን ጥላቻ ያንፀባረቀበት ብቻ ሳይሆን በወንጀል የሚያስጠይቅ፣ አንድን ማኅበረሰብ በሌላ ማህበረሰብ ላይ እንዲነሳ የሚገፋፋ፣ እንደ ሩዋንዳ ዓይነት የዘር ፍጅት እንዲፈፀም የሚጋብዝ ንግግር በመሆኑ ፓቲያችን ይህን ዓይነቱን ንግግር በፅኑ ያወግዛል፡፡ የኢትዮጵያ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በርካታ የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ተሰበጣጥረው የሚኖሩባት ከተማ ነች፡፡ ከእነዚህ መሃል አማራውን ብቻ ነጥሎ የጥቃት ሰለባ ለማድረግ በሩዋንዳ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን የዘር እልቂት ዓይነት በኢትዮጵያ ለመድገም መሞከር ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የጥላቻ ንግግር ምንጭ በማህበረሰብ ደረጃ አማራውና ኦሮሞው አብረው በሰላም ለመኖር ካለመቻላቸው የተነሳ አይደለም። በጎጠኝነት አስተሳሰቡ ምክንያት የበታችነት ስሜት የተጠናወተው የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና ፓርቲ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ህወሓትን እያስከነዳ ያለዉን የኦሮሙማ መንግስት የሃገር ዘረፋ ሊያስቀር የሚችል እምቅ ሃይል ያለው የአማራው ብሔርተኝነት እና በኢትዮጵያዊነት ጀርባ የተሰለፈው ኃይል ነው ብሎ ስለሚሰጋ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አበቤ ሰሞኑን በተለይ በአማራውና በአጠቃላይም በደቡብ ማህበረሰቦች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግራቸው “የሆዴን መከፋት ጥርሴ እየመለሰው፣ አለመኛ ነዋሪ እመስላለሁ ለሰው” የሚለውን የአማራውን ባህላዊ አነጋገር ያስታውሰናል፡፡ አማራው እየተከፋም ቢሆን የሃገር አንድነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በመስጋት ቢታገሰም፣ ይህ ትዕግስት ለኦሮሙማዉ መንግስት ካድሬዎች እንዳለማዎቅ እና ፍራቻ ተወስዷል። ከንቲባዋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአማራ ክልል ወጣት ወደ አዲስ አበባ በመሰደድ ላይ ነው ስትል እና ይህን የህዝብ እንቅስቃሴ ስትኮንን፣ እያለች ያለችው የኢትዮጵያ ዜጋ የሚባል ህብረተሰብ የለም፤ ያለው ኦሮሞ፣አማራ ወዘተ የሚባሉ ነዋሪዎች እና አማራ እና ኦሮሞ የሚባሉ ሀገሮች ናቸው የሚል አመለካከት እያራመዱ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከንቲባዋ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ “እየተሰደደ” ያለው ብዛት ያለው ህዝብ ከሃገሩ አንድ አካባቢ ወደ ሃገሩ ሌላ አካባቢ በነፃነት የመዘዋወር መብት ያለው ህዝብ መሆኑን ከመዘንጋታቸውም በተጨማሪ፣ የኦሮሙማው መንግሥት እስከ መጨረሻው እቆምለታለሁ የሚለው ህገመንግሥት ይህንኑ መብት በአንቀጽ 32 ላይ የደነገገው መሆኑን ሳታውቅ ቀርታ አይደለም። የብልፅግናው የኦሮሙማ መንግሥት ከህግ በላይ ነው ማለታቸው ብቻ ሳይሆን፣ አባባላቸው የሚያመለክተዉ ከተማውን እየመሩት ያሉት ከመመሪያ እና ከህግ ውጭ በእውር ድንብር መሆኑን የሚያረጋገጥ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ደግሞ ከንቲባዋ የተጠናወታቸው ኦነጋዊ አስተሳሰብ በዓየነ ህሊናቸው አዲስ አበበባን የሚያጠቃልል ኦሮምያ የሚባል ሃገረ-መንግሥት እንዳለ እያሰቡ፣ ከሌሎች የአካባቢ ሃገሮች ነዋሪዎች የሚጎርፉበት ሁኔታ እንደተፈጠረ፣ እነዚህ በብዛት ከአማራ “ሃገር” ወደ አዲስ አበባ “በስደት የሚጎርፉ” ሰዎች የኦሮሚያን ዳርድንበር ጥሰው ወደ ኦሮሚያ “ዋና ከተማ” ወደ ፊንፊኔ እየገቡ ነዉ የሚል አመለካከታቸውን እያንፀባረቁ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ የከንቲባዋ የዘር ፍጅት ቀስቃሽ አባባል ያልተከፋ ሰው የለም፡፡ ይህን በዘር ፍጅት ቅስቀሳ ላይ የተመሰረተ መርዘኛ የሆነ የከንቲባዋን አባባል ባልደራስ በከፍተኛ አፅንኦት እያወገዘ፣ የከንቲባዋ ይህ ኃላፊነት የጎደለው አባባላቸው የአዲስ አበባን ህዝብ የመምራት ችሎታ የጎደላቸዉ መሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ ፓርቲያችን ከሥልጣን ሊነሱ ይገባል የሚል አመለካከት አለው፡፡
መሃል አዲስ አበባ ላይ እየተካሄደ ስላለዉ የቤቶች ፈረሳ፣ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት፣መንግሥት መራሽ የመጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት
በመሃል አዲስ አበባ ባለማቋረጥ እየተካሄደ ያለው የቤት ፈረሳ እና የታሪክ ቅርሶች ውድመት ከዚህ የፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ለሃገረ- ኢትዮጵያ እና ፅኑ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ላለው የአማራው ማህበረሰብ ጥላቻ የሚቀዳ ነው፡፡ ሰሞኑን በርካታ የመኖሪያ ቤቶች በቡልዶዘር እየፈረሱ ናቸው፡፡ የቤት ፈረሳዎቹ በአብዛኛው እየተካሄዱ ያሉት ነዋሪዎቹ በተኙበት በውድቅት ሌሊት ነው፡፡ የአፍራሾቹን የጭቃኔ ጥግ የሚገልፀው ነዋሪዎቹ ለዘመናት የኖሩባቸውን ቤቶች ሲያፈርሱባቸው እቃዎቻቸውን እንኳን እንዲያወጡ አለመፍቀዳቸው ነው፡፡ በዚህ የመንግሥታዊ አረመኔነት ተግባር በርካታ አባውራዎች ከነቤተሰቦቻቸው መጠጊያ አጥተው በጫካና በሜዳ ላይ እንዲበተኑ ተገደዋል፡፡ እናት የተወሰኑ ልጆቿን ከከፊል እቃዎች ጋር ሜዳ ላይ በትና ሌላ የተረሳ እቃ ለማምጣት ወደ ፈረሰ ቤቷ ስትመለስ ከጓዙ ጋር በሜዳ ተቀምጠው ከነበሩ ሁለት ልጇቿ መካከል አንዱ በጅብ ተበልቶ መሞቱ የዚህ የመንግሥታዊ አረመኔነት ተግባር ዓይነተኛ ማስረጃ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ክልል በተለይም በፉሪ፣ በአቃቂ እና በጀሞ አካባቢዎች ከፍተኛ የከርስ ምድር ውሃ እንዳለ በደርግም ሆነ በወያኔ ዘመን የተካሄዱ ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኦሮሙማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ዙሪያ የተጠመጠመ ሽገር የተሰኘ አካባቢን በመፍጠር አዲስ አበባን የውሃ ሃብቷ የሚገኝበትን፣ የቆሻሻ መጣያ እና የአትክልት ምርት ማምረቻ ቦታዎቹዋን በጉልበት ወደ ኦሮሚያ ክልል እያካለለ በውሃ ጥም ሊፈጃት በምርት እጥረት ሊፈታተናት አቅዷል፡፡
ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የከተማው ነዋሪ በመጠጥ ውሃ ጥም እንዲጠቃ እየተደረገ ያለው መንግሥት መራሽ የሆነው የከተማው የውሃ እጥረት ጉዳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ያስችል ለነበረው ግዙፉ የገርቢ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመታት በፊት ሊዉል በቻይና መንግሥት ተመድቦ የነበረው ገንዘብ በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት ትብብር ተነፍጎት ጥቅም ላይ እንዳይዉል እንደተደረገ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ለዚህ ፕሮጀክት ተፈቅዶ የነበረው ብደር ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ባለመደረጉ ገንዘቡ ተመላሽ መደረጉ የታወሳል። በወቅቱ ፕሮጀክቱ ያልተደረገበት ምክንያት የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ግንባታ ውሃው ለሚተኛበት ቦታ፣ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያ ለሚገነባበት እንዲሁም በአጠቃላይ ለውሃው ተፋሰስ የሚውለውን መሬት ከሰው ንክኪ ነፃ አድርጎ ለማስረከብ ፈቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው፡፡ ያ በ2010 ዓ.ም. በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለገርቢ የአዲስ አበባ የመጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ጸድቆ የነበረዉ የቻይና መንግስት የብደር ገንዘብ እንደገና ባለፈው የካቲት ወር 2015 ዓ.ም. የቻይና መንግሥታዊ ባንክ በሆነዉ በኤግዚም ባንክ ሰሞኑን በድጋሚ ተፈቅዷል፡፡ በቅርቡ በቻይና ኤግዚም ባንክ ለ14 ፕሮክቶች እንዲወል ከተፈቀደው 622 ሚሊዮን ዶላር መካከል ሃምሳ በመቶው የሚውለው ለገርቢ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ጎጃም በሚወስደው መንገድ ከእንጦጦ ተራራ ጀርባ የሚገኘውን የገርቢ ወንዝ በማልማት የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ትርጉም ባለው መልኩ ይቀርፋል ተብሎ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት ታቅዶ የነበረ ነዉ። አሁን ደግሞ በድጋሚ በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. ከቻይና ኤግዚም ባንክ ለዚሁ የአዲስ አበባ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የተፈቀደዉን ገንዘብ የኦሮሙማዉ የኦህዴድ/ኦነግ የብልፅግና መንግሥት ፀረ አዲስ አበቤ በሆነው ፅንፈኛ እና ጎጠኛ የፖለቲካ አመለካከቱ ምክንያት ተግባራዊ እንዳይሆን እንዳያደርገው ያሰጋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው ሌላዉ መንግሥታዊ መር ተንኮል ደግሞ ኬላዎችን በአዲስ አበባ ዙሪያ በማበራከት የጤፍ እና የስንዴ ምርት ከአማራ እና ከኦሮሞ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ መከልከል ነው፡፡ በዚህም የአዲስ አበባን ሕዝብ ከውሃ እጦት በተጨማሪ በእህል ምርት እጦት ምክንያት ኑሮው ይበልጥ እንዲጎሳቆል እና በአዲስ አበባ መኖር እንዳይችል ማድረግ ነዉ። በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ የጤፍ እና የስንዴ ምርቶች ዋጋ መቀሌ እና አስመራ ከሚሸጡበት ዋጋ እንዲበልጥ መደረጉ፣ ከዚህ የኦሮሙማ መንግስት አዲስ አበባን ለመሰልቀጥ ካለዉ ህልም የሚቀዳ ነው፡፡ የኦሮሙማው መንግሥት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “የአዲስ አበባ ህዝብ ኦሮሞ ጠል ነው” በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካደረ ጉት ንግግር እና አዳነች አበቤ በቅርቡ ያደረጉት የአማራ ጠል ንግግር ወደተግባር እየተተረጎመ መሆኑን የሚያሳይ ነዉ።
የኦሮሙማው አገዛዝ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ያለውን ጥላቻ የሚያሳየው ሌላው መንግስታዊ ድርጊት ደግሞ የከተማውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በመቀነስ፣ ነዋሪው የሲሊንደር አቅርቦት እጥረት ባለበት ሁኔታ ህዝቡ በኤሌክትሪክ አብስሎ እንዳይበላ ኑሮውን ለማክበድ በእቅድ እየተፈጠረ ያለ የመንግሥት-ሠራሽ የኃይል እጥረት ነው፡፡ ከምግብ ዝግጅት በተጨማሪ ዘመናዊነት ያመጣቸው የቴክኖሎጅ ውጤቶች በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት ተግባሮቻቸው እየተስተጓጎሉ መሆኑ እየተለመደ መጥቷል፡፡ እነዚህ በዕቅድ እየተፈጠሩ ያሉ የመንግሥት ሰራሽ የኃይል እጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡
ለአባይ ግድብ መሠራት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ ብዙ የኢኮኖሚ አቅም ያለው የአዲስ አበባ ህዝብ ያዋጣው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁንና በአባይ ግድብ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመር የተገኘውን መጠኑ የጨመረ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በቅድሚያ የኢትዮጵያ ህዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ሲገባ፣ ከህዝቡ በመንጠቅ እና ቀድሞ ሲከፋፈል የነበረውን በቀድሞው ሁኔታ እንዳይዳረስ በማድረግ በምትኩ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬኒያ፣ ለጅቡቲ ለሱዳን በዉጭ ምንዛሪ እየተሽጠ ይገኛል፡፡ ወያኔ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰነዘረው ጦርነት ከሥልጣኔ ሊያፈናቅለኝ ነው፣ ጦርነቱን በመደበኛ ጦር መከላከል አልቻልኩም ብሎ በኦህዴድ/ኦነግ የብልፅግና መንግሥት በእጅጉ ለስልጣኑ በተጨነቀበት ጊዜ ከጎኑ በመቆም ለደረሰለት ለኤርትራ እንኳን ኤሌክትሪክ ልሸጥለት ሲል አልተሰማም፡፡
በአጠቃላይ የኦህዴድ/ኦነግ ብልፅግና ፅንፈኛ እና ጎጠኛ የገዥ ቡድን ኦነግ በምናቡ ለፈጥረው እና ሃምሳ ዓመት ለታገለለት የኦሮሚያ ሪፖብሊክ እዉን መሆን በአሁኑ ጊዜ ብቸኛ መሰናከል ሁኖ የተገኘው አማራ ይበዛበታል የሚለው የአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ ይህን ከተማ የሚያስርብ ፣የሚያስጠማ፣ ከመኖሪያው የሚያፈናቅል፣ በኃይል እጥረት እንዲጠቃ ለማድረግ ይጠቅሙኛል ብሎ በተግባር የሚተረጉማቸው የኢኮኖሚ እርምጃዎች ከዚሁ ፀረ ሀገረ-ኢትዮጵያ እና ፀረ አማራ ፖሊሲዉ የመነጩ እና የሚቀዱ ናቸው፡፡
ስለሆነም የአዲስ አበባ ህዝብ እነዚህን መንግሥት መራሽ የሆኑ የምርትና የአገልግሎት እጥረቶች ለማስወገድ አንድነቱን አስተባብሮ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሊያሰማና በህብረት በሰላማዊ ተቃውሞ ሊታገል ይገባል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
የብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም.