>

የአማሮች ጥያቄ (ገለታው ዘለቀ)

የአማሮች ጥያቄ 

ገለታው ዘለቀ

የአማሮችን ትግል አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች የአማራ ብሄርተኝነት  (Amhara Ethno nationalism) ጥያቄ እያሉ ሲገልጹት አያለሁ። ይሄ የብሄርተኝነት ጥያቄ የአማራ ህዝብ ጥያቄ ነው ብዬ አላምንም። እኔም እንደ አንድ አማራ ይህንን አልጠይቅም። አማሮች ጥያቂያቸው እንደ አማራ የብሄር ፖለቲካን እንጫወት እንደ አማራ ፖለቲካዊ ብሄርተኛ እንሁን፣ ኢትዮጵያም በዚህ በብሄርተኝነት የፖፑቲካ እሳቤ ትመራ አይደለም የአማራ ጥያቄ። እንዴውም ሀገሪቱ ከብሄርተኛ ፖለቲክ እንድትወጣ አማሮች አምርረው ይሻሉ።ታዲያ የአማሮች ጥያቄ ምንድን ነው? ብለን ከጠየቅን የሚከተሉት ዋና ዋና ጥያቄዎች የአማሮች  ጥያቄዎች ናቸው።

1. በማንነቴ ምክንያት በሀገሬ በሰላም መኖር አልቻልኩም።

የመጀመሪያው ጥያቄ አማሮች በተለይ በአለፉት አምስት አመታት በማንነታቸው ምክንያት መፈናቀል፣ ግድያ፣ የንብረት መውደም ደርሶባቸዋል። በማያባራ መፈናቀልና ስደት ውስጥ ናቸው። በደራ፣በወለጋ፣በቤንሻንጉልና በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል። እስከአሁንም ተፈናቅለው መከራ ላይ ናቸው። አማሮች በማያባራ መፈናቀል ላይ ናቸውና አንዱ የአመጻቸው ምክንያት ይሄ ነው። የአማሮች ትግል በዚህ ረገድ መፈናቀል ይቁም ብቻ ሳይሆን እነዚህ ተፈናቃዮች ፍትህም አጥብቀው ይሻሉ። 

2.  የክልሉ መሪዎች አይወክሉኝም የአመራር ለውጥ ይምጣ!

አማሮች በማንነታቸው ምክንያት በማያባራ መፈናቀልና ስደት ውስጥ ባሉበት በዚህ ክፉ ጊዜ የአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ለአማራ ህዝብ ማንነት ተኮር ጥቃት መከታ መሆን አለመቻል ብቻ ሳይሆን ጥቃት የሚያስገቡ መሆናቸው፣ በክልሉ መልካም እያስተዳደረ ባለማስፈናቸው አማሮች ይህንን አመራር አምርረው መቀየር ይፈልጋሉ።

3.  አዲስ አበባ አትገቡም ልትሉን አትችሉም። አዲስ አበባ የሁላችንም ናት!

በተለይ በአለፉት ጥቂት አመታት አማሮች ላይ ያነጣጠረ ወደ አዲስ አበባ አትገቡም የሚባል ነገር የብዙ አማሮችን ስሜት ጎድቷል። አዲስ አበባ የሁላችን ሆና ሳለ በጠራራ ጸሀይ አዲስ አበባ አትገቡም የሚለውን ሀይል አማሮች አምርረው ይታገሉታል። አዲስ አበባ የሁላችን ናት ነው አንዱ የአማራ ትግል።
4. ትጥቅ ለመፍታት ጊዜው አይደለም!
የአማራ ገበሬ ትጥቅን እንደ ባህሉ ያየዋል። ሰው ሲሞት ጠመንጃ ያነግታል፣ ልጅ ሲወለድ ክርስትና ሲደግስ ያነግታል፣ ሰርግና ምላሽ ሲያደርግ ያነግታል፣ ደግሞ ክተት ሲባል ይከታል። ይህንን መብቱን ገበሬው ይፈልገዋል። አማራው በቅርቡ የተነሳውን የልዩ ሀይልና ፋኖ ትጥቅ አውርድ ጥያቄን የሚቃወመው አሁን ሀገሪቱ አልተረጋጋችም፣ እንደ አማራም ስጋቶች አሉብኝ፣ ስለዚህ ወቅቱን ጠብቁ መጀመሪያ ብሄራዊ ምክክር ይቅደም ነው አንዱ ግብግብ።

5. የጋራው ቤታችን አመራር ከሽፏል። አብይ አህመድ ከስልጣን ይውረድና ሽግግር ውስጥ እንግባ!

የአማሮች ሌላውና ትልቁ የትግል ጥሪ ደግሞ የ ጋራው ቤታችን አካባቢ የአመራር ክሽፈት ስለገጠመን ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር ሆነን ኢትዮጵያን እናትርፍ የሚል ነው። አሁን ያሉ የብሄር ግጭቶች፣ ጥላቻና መከፋፈል ከፌደራል መንግስት አመራር ክሽፈት የመጣ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሆነን ኢትዮጵያችንን እናንጽ ። ኢትዮጵያ ከባድ የሆነ የህልውና አደጋ በገጠማት ጊዜ የነበረንን ትብብር ዛሬም እናሳይ። ኦሮሞ ሆይ ጉዳትህ ጉዳቴ ነው ደስታህ ደስታዬ ነው፣ ትግራይ ሆይ ጉዳትህ ጉዳቴ ነው ደስታዬ ነው፣ ጉራጌ ሆይ ጉዳትህ ጉዳቴ ነው ደስታህ ደስታዬ ነው……..ስለሆነም ኑ! ኢትዮጵያውያን በጋራ ታግለን ለኢትዮጵያ ትንሳኤ እናምጣ። አብይ አህመድ ከስልጣን ይውረድና ሁሉን አቀፍ ሽግግር ይፈጠር ።ኢትዮጵያውያን ሁሉ በኑሮ ውድነት፣ በስራ አጥነት ጅራፍ እየተገረፍን አንኖርም። የአመራርና የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልገናል የሚል ነው የአማሮች ትግል። ፍትሀዊ የትግል ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች በሽምግልና  የሚፈቱ ሳይሆኑ በስርዓት ለውጥ የሚፈቱ ጥያቄዎች ናቸው። 
እነዚህን ጥያቄዎች በመረዳት የህዝቡን ትግል መደገፍ ይገባናል። ጥያቄዎችን ጽንፈኛ አናድርግ። በዚህ ስርአት የተጎዳው ሁሉም ነው። የተመቸው የለም። ስለዚህ ጉራጌው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ ወዘተ. በአንድ በኩል ከማንነቱ ጋር የተገናኙ ጥቃቶቹን እየመከተ እየታገለ ነገር ግን በጋራው ቤታችን አካባቢ የገጠመንን የአመራር ክሽፈት በጋራ ሆነን ማስተካከል አለብን። 


እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅልን

Filed in: Amharic