>

የአምሓራ ህዝባዊ ግንባርን ለምን እንደግፋለን! (ብርሃኑ ድንቁ)

የአምሓራ ህዝባዊ ግንባርን ለምን እንደግፋለን!

ብርሃኑ ድንቁ

የወታደራዊውን ደርግ መውደቅ ተከትሎ ወያኔ ኢትዮጵያን ሻቢያ ደግሞ ኤርትራን ሲቆጣጠሩ የአምሓራ ህዝብ ስቃይ በይፋ ጀመረ። ጉዳዩን ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ ብሎም የተበዳዩ አምሓራ ድምጽ ለመሆን እኢአ 1984 ዓም “መላ አምሓራ ሕዝብ ድርጅት” (መአህድ) በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ አማካኝነት ተቋቋመ። የዚህ ድርጅት መመስረት በወቅቱ የነበረውን የአምሓራ ህዝብ ፍዳ በመጠኑ ሊገድበው ቢችልም – በርግጥ የአምሓራን ህዝብ አገር የማሳጣቱን ደባና በማይወክሉት ሰዎች እንዲመራ የተደረገውን ተንኮል እንዲሁም መላ ህዝቡን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት የታቀደውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሊቋቋመው አልቻለም። ወያኔ ይባስ ብሎ መሪውን በመግደል ከነጭራሹ መአህድ እንዲፈርስ አደረገ። የዋሁ አምሓራ – ግፈኞች ይሄን እንዲያረጉ ስለፈቀደላቸው ለዓመታት ያለመሪና ያለድርጅት መቆየቱ ግድ ሆነ። መሪና ድርጅት የሌለው ህዝብ በግፍና በኢ-ፍትሃዊነት (atrocity and injustice) መማቀቁ አይቀሬ ነው።

ሁኔታዎች እንደነበሩ አይቆዩምና ከዓመታት ግፍ በኋላ በአምሓራና በኦሮሚያ ክልሎች በተነሳው የህዝብ አመጽ ወያኔ ማንም ሳይነካት ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ብትፈረጥጥም ቅሉ አምሓራ የሚወክለው ድርጅትም ሆነ መሪ ስለሌለው ክፍተቱን (vacuum) ተከትሎ ብልጣብልጡ ኦህዴድ-ብልጽግና ኦሮሙማ ቡድን መንግሥታዊ ሥልጣንንና ወሳኝነትን (authority and decision power) ቀጨም አደረገ። አምሓራው ባለመደራጀቱ ምክንያት እንደቀድሞው ሁሉ እባሰ መከራ ውስጥ ከመውደቁም በላይ በኦሮሞ ጽንፈኞች መጠነ ሰፊ ጥቃት፣ ፍጅት፣ መፈናቀልና ስደት ደረሰበት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አምሓራው በገዛ ምድሩ በወያኔ ሠርጎ ገቦች ተወሮና ተጨፍጭፎ ንብረቱ ሳይቀር ወደመበት። ምስኪኑ አምሓራ ዛሬም “በመሳሪያ አስረክቡና ልዩ ኃይል ይፍረስ” ሰበብ በዘረኛው ኦሮሙማ መንግሥት እየተዋከበና እየተጨፈጨፈ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው አምሓራው መጠነ ሠፊ የሆነውን የሰቆቃ ድግምግሞሽ ለመታደግ በአገርም በውጭም መሰባሰብ የጀመረው። በተለይም በውጭ ሃገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በይፋ 51 ድርጅቶችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ የአምሓራ ንቅናቄ ተቁቁሞ በጋራ መስራት ተጀምሯል ። በአገር ውስጥም ቢሆን ባልተማከለ መልኩ የሚንቀሳቀስ ፋኖነትና ህዝባዊ እምቢተኝነት አለ። በዚህ ወሳኝ ወቅት ነው “የአምሓራ ህዝባዊ ግንባር” (Amhara People´s Front) የመመሥረቱ የምሥራቹ ዜና ከእስክንድር ነጋ አፍ ድንገት የተሰማው። ቀድሞም ቢሆን ክስተቱ እውን ሊሆን እንደሚችል ግምቱ ቢኖርም በእርግጥ ዜናው ከቆራጡ እስክንድር አንደበት መውጣቱ የብዙዎችን የተሰበረ ቅስም ጠግኗል።

በመሠረቱ የአምሓራ ህዝባዊ ግንባር መፈጠር ለተለያየ ሰው የተለያየ ስሜት መፍጠሩ አይቀርም። በኔ ግምት ለብዙ ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ህዝቡን አንድ አርጎ ሊያታግል የሚችል ወቅቱን የተንተራሰ ድርጅት መፈጠሩ የሚያሳድረው ሃሴት አንደኛው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ይሄ ግንባር በእሳት በተፈተነውና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲል መከራና ስቃይ በተቀበለው እስክንድር መመራቱ የጫረው ተስፋ ነው። ሌሎች ስሜቶችም ሊኖሩ ይችላሉ እኔን ግን ሁለቱን ሃሳቦች እጋራለሁ። ዘረኛው የኦሮሙማው መንግስት በአምሓራው ህዝብ ላይ ሙሉ ጦርነት ባወጀበት ጊዜ   የግንባሩ መመሥረትና መሪው ደግሞ ለሶስት አሥርተ ዓመታት በህዝብ ትግል የተፈተነው እስክንድር መሆኑ ግጥምጥሞሹን ታሪካዊ አድርጎታል። በጥቅሉ ስናየው የአምሓራ ህዝብ ከዘመናት ስቃይ በኋላ መሪውን አምጦ የወለደውን ያህል ነው የሚሰማው።

እናስ! ለምንድነው ይሄ የአምሓራ ህዝባዊ ግንባር መደገፍ ያለበት?

በግራም በቀኝም ብንመለከተው ሥርዓቱ የአምሓራ ህዝብን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጎጂ (vulnerable) አድርጎታል። በሌላ በኩል ደግሞ ነባራዊ ሁኔታው (objective condition) ነው የአምሓራ ህዝብ በአምሓራነቱ እንዲደራጅ፣ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት እንዲያሳይ ያደረገው። በውጭው ያለው የአምሓራ ህብረተሰብ በአንድ ድርጅት ጥላ ስር በመሰባሰብ ላይ ይገኛል። በአገር ውስጥ ያለው አደረጃጀት ግን ለጊዜው አንድ ወጥ አይደለም። አምሓራው በፋኖነት በተለያየ አካባቢ ነው የተሰባሰበው። የሠላማዊ ተቃውሞ ዘይቤዎቹም (methods of nonviolent protest) ቢሆን የፈረጠሙ አይደሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ በአገር ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ካልተመራ ትግሉ ፍሬዓማ ሊሆን አይችልም። ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን ያለው ውዳቂ መንግስት (failed state) እንክትኩቱ ቢወጣ፣ መውጣቱ አይቀርም፣ አምሓራውን ወክሎ በመንግስት ደረጃ እሚቀመጥ ኃይል ስለማይኖር ከዚህ በፊት እንደታየው ክፍተቱን ተከትሎ ሌላ ነፍሰ ገዳይ ቡድን እሥልጣኑ ማማ ወጥቶ የፈረደበትን የአምሓራ ህዝብ ላይ ይረባረብበታል። ለዚህ ነው በአገር ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ በአንድ ድርጅት የመመራቱ ጉዳይ ደግሞ ደጋግሞ ሊታሰብበት የሚገባው።

በአንድ ኃይልና በአንድ ድርጅት መመራት የሚያጎናጽፋቸው ጥቅሞች፤

1/ አንድ ሕብረት ካለ ምን መደረግ እንደሚያሻ በጋራ መወያየት ከመቻሉም ባሻገር ሁኔታን አስመልክቶ ትክክለኛ ግምገማ ይደረጋል (realistic assessment of the situation)፣ የመዳረሻ ግብና ዕቅድም ተቀርጾ (strategic planning) በማኒፌስቶ መልክ ሊገለጽ ይቻላል፤

2/ አንድ ወጥ አመራር ካለ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ (civil disobedience) በተመሳሳይ ቀን፣ ሰዓትና በሁሉም ቦታ ሊደረግ ይችላል። አምባገነኑ መንግስት ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ስለሚሆንበት በአፋጣኝ ወደ ድርድር ለመምጣት ይገደዳል። የትግሉ መፈርጠምና በአንድ ማዕከል መመራቱ የአገዛዙን ልፍስፍስ አስተዳደር በቶሎ ይመነድገዋል።

3/ በተለያዩ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘውን የፋኖዎች ቡድን ዓላማና ግብ አቀናጅቶ በጋራ የሚያታግለው አንድ ወጥ አመራር ነው። በተጨማሪም ታጋዮች፣ ከውስጥም ይሁን ከውጭ፣ አስፈላጊው አቅርቦትና ድጋፍ ማለትም ስንቅ፣ ትጥቅ፣ መጓጓዣ (supply and logistics) የሚቀርብላቸው የተማከለና የተቀናጀ ስልት ሲዘረጋ ነው።

4/ አንድ ወጥ መመርያና አንድ ድርጅት መኖሩ ከተለያዩ አካባቢዎች በዘር ማጽዳት (ethnic cleansing) ምክንያት የሚፈናቀሉትን የአምሓራ ህዝብ የሰብዓዊና የጤና እርዳታ እንዲደርሳቸው እንዲሁም የሰውን ልጅ በሚመጥን ሁኔታ መጠለያ እንዲያገኙ ለማድረግና እንባቸውን ለማበስ ይረዳል።

5/ አምሓራው በኅልውና ቆሞ ራሱን ሲያስከብር ነው አገራትም ሆኑ ድርጅቶች እውቅና (validity and legality) የሚሠጡት። ማዕከላዊ አሠራር ከድርጅቶችም ሆነ ከተለያዪ አገራት ጋር ተገቢውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት (international relations) ለማድረግ ወሳኝ ነው። የኢትዮጵያ መመሰቃቀል የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናን ከማናወጹም በላይ በቀይ ባህር በሚተላለፈው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ችግር መፍጠሩ ስለማይቀር ብሄራዊ ፍላጎታቸውን የሚያስቀድሙት ኃያላኖቹም ሆኑ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ጉዳዩን በአጽንዖት ለመከታተል ይገደዳሉ (in order to advance their own economic or political interests)።

6/ አንድ ወጥ የሆነ ጠንካራ ድርጅት መኖሩ ገና በጥርጣሬ ላይ ላሉ የአምሓራ ወገኖች የማንቂያ ደወል ይሆናል (increase awareness of the people of Amhara)። የድርጅት ጥንካሬ ነው ሁሉም እንዳቅሙና እንደየድርሻው የጋራ አስተዋጽዎ እንዲያረግ (collective participation) የሚገፋፋው።

ከላይ የተጠቀሱትእንዲሁም ሌሎች ያልተጠቀሱ ምክንያቶች፣ በጥቅሉ፣ የአምሓራውን ድርጅት መወለድ ከሠማይ እንደወረደ ጸጋ እንድንቀበለው ያደርጉናል። በተጨማሪም ግንባሩ የሚመራው እስክንድርን በመሰለ ጀግና ስብዕና መሆኑ ሃሌሉያ የሚያሰኝ ሆኗል። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ሲታደጋት ቆይቷል፣ ዛሬም አይተዋትም። ደግመን ደጋግመን “እውነትም ኢትዮጵያን እግዚአብሄር( አላህ) ይጠብቃታል” የምንለው ለዚህ ነው።

መቼም “ፍየል ከመድረስዋ …” እንዲሉ ግንባሩ ገና ከመመስረቱ ዘለፋ የሠነዘሩም አልጠፉም። ምን ይሄ ብቻ! ግንባሩ በእስክንድር መመራቱን ያወቁ ጥቂት መረን የለቀቁ ራስ ወዳዶችና እፍረተ-ቢስ ባንዳዎች በዚህም በዚያም አጸያፊ ቅርሻታቸውን መትፋት ጀምረዋል። አጉራ ዘለሎችና ባለጌዎች ያሉትን፣ ያወሩትን ሁሉ እዚህ ላይ መጥቀሱ የአስተዋዩን የአምሓራን ህዝብ ባህልና እሴት ማጠልሸት ስለሚሆን ደግሜ አላነሳውም። መናገር የምንችለው አንድ ሃቅ ግን አለ። የአምሓራ ህዝብ ድርጅቱንና መሪውን አምጦ ወልዷል። እውነት – ትላንትም ዛሬም ከአምሓራ ጎን ቆማለች። አምሓራው ከበረታ ከዚህ በኃላ ትግሉን ወደ ኋላ የሚጎትተው ምድራዊ ሃይል አይኖርም። ሁላችንም ከአምሓራ ህዝባዊ ግንባር ጋር አብረን ለመሥራት እንትጋ። መሪያችን እስከንድር ነጋ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያስመነድገው እንተማመናለን።

አምሓራ ስለቀድሞው መልካም ሥርዓት፣ ስለወደሙት ቅርሶች፣ ስለነጠፉት ባህልና እሴቶች ሲል አጥፊዎችን ይፋረዳል!


ድል ለአምሓራ ህዝብ!

ብርሃኑ ድንቁ
04/06/2023 – ኦስሎ፣ኖርዌ

Filed in: Amharic