ጀግናን እያሳዘኑ መሸኘት እስከመቼ ?
ደቻሳ አንጌቻ ታደሰ
ስለ ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ጀግንነት ብዙ ስለተባለ ስለእሱ መናገር አልፈልግም ። በአንፃሩ ብዙ ዋጋ ለሀገር የከፈለን ጀግና ስርአቶች የሰጡት ምላሽ ላይ ጥቂት ልበል ። ግንቦት 1983 ዓ.ም ላይ የመንግስት ለውጥ መጣ ። በስደት ኬንያ የነበረው አሊ ወደ ሀገሩ ተመለሠ ። የጠበቀው ግን ሽልማት ሳይሆን እስር ሆነ ።
ህወኃት መራሹ ኢህአዴግ ያለምንም ፍርድ ለ11 አመት በወህኒ ቤት በግፍ እስር አማቀቀው ። በሰራው ጀብድ የተሸለመውን የህብረተሰባዊት ኢትዮጵያ የላቀ የጀግና ሜዳዩን ነጠቀው ። ሰርቴፊኬቱን ወሰደበት ። ግራንድ ዩኒፎርሙን ቀማው ። በመለዮ የነበሩ ፎቶግራፎቹን ጠራርጎ ወሰደበት ።
በጠቅላላ ክብሩና ትዝታውን ነጥቆ ታሪክ አልባ ሊያደርገው ሞከረ ። ከግፍ እስሩ ሲወጣ ትዳሩና ቤተሰቡ ተበትኖ ጠበቀው ። ጡረታ አልተከበረለትም። የአገልግሎት ክፍያ አልተሰጠውም ። ህይወት ሲጨልምበት የጥይት ፍንጣሪ በተሸከመ ገላው ሸክም በመሸከም ፣ የቀን ስራ በመስራት ፣ ጎዳና እያደረ ኑሮውን መግፋት ተያያዘው ። በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የአሊን ውለታ የሚያቁ ኢትዮጵያዊያን ገንዘብ አዋጥተው ልከውለት ለገጣፎ ድሬ የሚባል አከባቢ የጨረቃ ቤት ቀልሶ የቀን ስራ እየሰራ ኑሮውን መግፋት ያዘ ።
በሂደት የቆሠለ ገላው እየተሸከመ መኖር ስለከበደው በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን በየወሩ በሚልኩለት መጠነኛ ተቆራጭ ገንዘብ ህይወቱን ይገፋ ነበር ። 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሲመጣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በከንቲባ አዳነች አቤቤ በኩል ለአሊ የቤት ስጦታ እንደሚያበረክትለት በይፋ በሚዲያ ቃል ገባለት ። የቁልፍ ርክክብ ሲያደርግም ፎቶ አንስተው ዜና ሰሩበት ። አሊም ደስ አለው ። የመኖር ተስፋው ጨመረ ።
በአዲስ አበባ ከተማ እየኖረ የተሻለ ህክምና እንደሚያገኝ ገመተ ። የቀድሞ የጦር ሜዳ ጓዶቹን እያገኘ ቡና እየጠጣ የጀግንነት ትዝታውን እንደሚያወጋ አሰበ ። ሆኖም የከተማ መስተዳደሩ አሊን ረሳው ። የጀግናውን ስምና ክብሩን ለምርጫ ቅስቀሳ ከሸቀጠበት በኃላ ቃሉን በላ ።
አሊ ተስፋ ሳይቆርጥ ከለገጣፎ /ድሬ የሚያነክሰውን እግሩ በከዘራ እየደገፈ ፒያሳ ወደሚገኘው ማዘጋጃ ቤት ደጋግሞ ቢመላለስም ለተገባለት የቤት ስጦታ ምላሽ የሚሰጠው አካል አጣ ። በሁኔታውም ተስፋ ቆረጠ ። በመከዳቱ በጣም አዘነ ። እንዳዘነም በጥቂት ቀን ህመም ወደማይቀርበት አለም ሄደ ። ለጀግናው ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ በተከታታይ በመጡት አገዛዞች የተሰጠው ምላሽ ይሄ ነው ።
በሰላም እረፍ አሊ