>

የአማራ ህዝባዊ ግንባር መግለጫ!

የአማራ ህዝባዊ ግንባር መግለጫ!


ሰኔ 6 2015 ዓ.ም/መከላከያ በደምበጫ፣ ጂጋ እና ፍኖተ-ሰላም በንፁሃን ላይ የፈፀማቸውን ግድያዎች እና እንግልቶች እናወግዛለን!!/ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች በአማራ ላይ እየተፈፀመ ያለው ጭፍጨፋ አድማሱን አስፍቶ ወደ አማራ ክልል እየገባ ይገኛል። በደብረ ኤልያስ የተፈፀመው የገዳማውያኑ ጭፍጨፋ የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። 

መንግሥት እኩይ ተግባሩን በሙሉ አቅም ለመፈፀም እንዲያመቸው ያለመ በሚመስል መልኩ፣ የአማራ ክልልን በሁሉም አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት እያዋከበ እና እየወጋ ይገኛል። ይህ ባለፉት ሳምንታት በጎንደር፣ በሸዋ እና በወሎ ተደጋግሞ የተፈፀመ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ  ግንባሩን ወደ ጎጃም አዙሯል። 

በዚህም መሠረት፣ ሰኔ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. አመሻሽ ጀምሮ በምዕራብ ጎጃም፤ ደንበጫ ከተማ በቡድን መሳሪያዎች የተደገፈ ተኩስ ከፍቷል። በዚህም እስከ 10 የሚደርሱ ንፁሃን ሰዎች ከመከላከያ ሰራዊት አባላት በተተኮሰ ጥይት መገደላቸው ታውቋል። የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል። 

በደምበጫ በተፈፀመው የተቀጣጠለው የህዝብ ተቃውሞ ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም አጎራባች ከተሞች ወደሆኑት ጅጋ እና ፍኖተ ሰላም ተስፋፍቶ ውሏል። 
በመከላከያ በኩል ተኩሱና ግድያው የቀጠለ ቢሆንም፣ ተደጋጋሚ ሞት፣ እስር፣ አፈናና ጭፍጨፋ የታከተው የአማራ ሕዝብ መንገዶችን በመዝጋት አላንቀሳቅስ ብሎታል። 

በዚህ ሂደት ህዝቡ እያደረገ ያለው ቅንጅታዊ የሞት ሽረት ትግል የሚደነቅ መሆኑ በገሃድ ታይቷል።
መንግሥት ከዚህ ተምሮ ከእኩይ ድርጊቱ ሊቆጠብ  ይገባል። በየመንደሩ የሰገሰገውን መከላከያ ሰራዊት በአስቸኳይ ከስምሪት አንስቶ በሀገር ዳር ድንበር ጥበቃው በማሰማራት፣ የከተማውን ጉዳይ ለፖሊሶች ማስረከብ ይገባዋል። 

የአማራ ሕዝባዊ ግንባር ለሟች ሰማዕታት ቤተሰቦች መፅናናትን፤ እንዲሁም ሟቾች ነፍሳቸው በአጸደ ገነት እንዲያርፍ፣ቁስለኞችም ፈጣን ፈውስ እንዲያገኙ እየተመኘ፣ ትግሉን አጠናክሮ ህዝብን ከጥቃት ለመታደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ተግቶ ይቀጥላል።

ሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም./የአማራ ሕዝባዊ ግንባር!
መነሻችን አማራ፣ መዳረሻችን ኢትዮጰያ!

Filed in: Amharic