>

የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን  በጐሣ መከፋፈል ህልውናዋን የማጥፋት ሰይጣናዊ ዕቅድ ዋዜማ ነው

የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን  በጐሣ መከፋፈል ህልውናዋን የማጥፋት ሰይጣናዊ ዕቅድ ዋዜማ ነው

ከይኄይስ እውነቱ

በርጉም ዐቢይ ዘመን ዦሮን ጭው የሚያደርግ ነገር መስማት የዕለት ዕለት ተግባራችን ከሆነ ድፍን 5 ዓመት ተቈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ከቆመችባቸው ዐበይት አዕማዶች ቀዳሚዎቹን ሁለቱን – ጥንታዊት÷ ታሪካዊት÷ ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን የኢኦተቤክ እና የዓለምን ታሪክ የቀየረው (በፀረ-ቅኝ ግዛት እና በፀረ-ፋሺስታዊ ተጋድሎ ድል በማድረግ) የሰው ልጆች በእግዚአብሔር ዘንድ እኩል መሆናቸውን ለዓለም ኹሉ በደም ያበሠረው የዓድዋ ድል – ላይ ቀጥተኛ ጥቃት በመፈጸም አገርን መናድ ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነማን ብሎ የሚጠይቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ የእውነትና የበጎ ኹሉ ጠላተ ለሆነው ዲያቢሎስ አድረው የራሳቸውን አገር፣ ቤተ ክርስቲያን እና ታሪክ ክደው፤ ጐሣዊ የድንቊርናና የዕብደት አገዛዝ ዘርግተው፤ በታሪካዊ ጠላቶቻችን እየታገዙ ሕዝብን እያመሱ የሚገኙ ወያኔ ሕወሓት እና በክፋቱ እነዚህን ከይሲዎች በብዙ እጥፍ ያስከነዳው ኦነጋዊው ኦሕዴድ ናቸው፡፡ ደመኛ የጋራ ጠላታቸው ያደረጉት ደግሞ የዐምሐራውን ሕዝብ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ድንክዬነታቸውን፣ መንደርተኛነታቸውን የበታችነት ስሜታቸውን ስለሚያጋልጥባቸው፡፡ በራሳቸው ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የኢትዮጵያዊነት እሤቶች ኹሉ ባለቤት ስላደረጉት፡፡ የዐምሐራው ሕዝብ እነዚህን አዋልደ ዲያቢሎስ ነገዳዊ ማንነቱ ሊጠፋ እስኪቃረብ ድረስ ታግሦአቸዋል፡፡ መከራና እንግልት÷ ክፋትና ውርደት ይበቃል የሚባልበት ጊዜ አለውና እጅግ ቢዘገይም ያ ጊዜ ደርሶ የማይቀረው የዳዊትና የጎልያድ ፍልሚያ ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን ‹ብዙ ሕዝብ እግዚአብሔር ነው› ይላሉ፡፡ እውነትን፣ ሕዝብንና እግዚአብሔርን የያዘ የድል ባለቤት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ፍልሚያ የሚያስከትለውን አገራዊ ጥፋት ሲያስቡት ይዘገንናል፡፡

ለዐምሐራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደሙ ሁለተኛ ተፈጥሮው ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የሚወዳትን አገሩን ከነ ሙሉ ክብሯና ኩራቷ ለማስቀጠል በቅድሚያ ህልውናውን/መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በአሁን ሰዓት የህልውና ማስከበር ተጋድሎ ላይ ይገኛል፡፡ የህልውና ማስጠበቁን ፍልሚያ እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት የጋራ ጠላቶቹ ኅብረት ፈጥረው፣ የተሐድሶ መናፍቃንን እና ለወያኔ ያደሩ፣ ዘረኝነትን ገንዘባቸው ያደረጉ፣ ከመንፈሳዊነት የተራቆቱ የትግራይ ‹ጳጳሳት፣ ካህናትና መነኮሳትን› ይዘው የኢኦተቤክ  ለመገንጠል የርጉም ዐቢይ ተላላኪዎች የሆኑትን እነ አካለ ወልድን ተቀላቅለዋል፡፡ ክርስትና፣ መንፈሳዊነትና ምንኩስና አፈር ድቤ ሲበላ እንዲህ ነው፡፡ ወያኔ ያለጥርጥር የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብና የአገራችን ቀዳሚ ጠላት ነው፡፡ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በጻፈው የደደቢት መግለጫው ላይ ጠላት አድርጎ የተነሣው የኢኦተቤክ እና ዐምሐራውን ነው፡፡ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ሕይወት ከመለያየት ይልቅ አብሮነት ይበጀናል ብለን በእጅጉ ደክመናል፤ ዝቅ ብለን ተለማምጠናል፡፡ ለመሆኑ ዐምሐራው በዚህ ረገድ የተለየ ኃላፊነትና ግዴታ ያለበት ይመስላችኋል? አንድን ማኅበረሰብ ወይም ጐሣ በጅምላ መፈረጅ ተገቢ አይደለም ብለን የሚቻለው ድረስ ተጠንቅቀናል፡፡ ቀደም ብለን ያነሣነው የወያኔ አቋም የትግራይ አኅጉረ ስብከት እና የአብዛኛው ትግሬዎች ኹሉ አመለካከት ከሆነ ለአብሮነት የምናደርገው ድካም ኹሉ ከንቱ ይመስለኛል፡፡ ርጉም ዐቢይ የሲኖዶሱን ክፍፍል እያርበደበደው ያለው ዐምሐራ ላይ ጫና ለመፍጠርና ለማንበርከክ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ርጉም ጌታቸውና ጓዶቹም የትግራይን ሕዝብ በጦርነት ካስፈጁት፣ በረሃብ ከጠበሱትና ካዋረዱት በኋላ ሕዝቡን ክደው ከርጉም ዐቢይ ጋር ገጥመዋል፡፡ የፖለቲካ ቆሻሻነት እዚህ ላይ ነው፡፡ ሁለቱም በሕዝብ ደም የተጨማለቁና አገር በማጥፋት የተጠመዱ ወንጀለኞች መሆናቸው እየታወቀ የቤተ ክህነቱ ሰዎች እርስ በርስ መካሰሳቸውና አንዱ ይቅርታ ተጠያቂ ሌላው ንጹሕ መስሎ ለመታየት የሚደረገው ሙከራ ለሥልጣን/ፓርቲ ፖለቲካ መሣሪያ የመሆን ወይም መንፈሳዊ ጥብዐት ከማጣት የመነጨ ወራድነት ነው፡፡ በደም የተጨማለቁት ወንጀለኞቹ ወያኔና ኦነጋዊው ኦሕዴድ ከኢትዮጵያ እንዲወገዱ ከየትኛውም ክፍል የሆኑ የሃይማኖት አባቶች ቢናገሩና ቢያወግዙ አንዳች ስሕተት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ አገር ወራሪውን የፋሺስት ጥልያን ጦር ቡራኬ ሰጥቶ እንደሸኘው የሮም ካቶሊክ ፓፓ ወያኔን ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ በጦርነት እንዲማገድ ቡራኬ የሰጡ የቤተ ክርስቲያን ‹አባቶች› ካሉ የእገሌ ሳይባሉ ጥፋት ፈጽመዋልና ይቅርታ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ቤተ ክህነቱ እና ሲኖዶሱ ይቅርታ መጠየቅ ካለበት የኢትዮጵያን ሕዝብ ባጠቃላይ፤ በተለይም ደግሞ ለ27 ዓመታት በፋሺስታዊዎቹ የወያኔና የኦነጋዊው ኦሕዴድ አገዛዞች የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማጽዳት፣ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙና የጦር ወንጀሎች ሲፈጸሙበት የቆየውንና አሁንም እየተፈጸመበት የሚገኘውን፤ በሚሊዮኖች ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በረሃብ አለንጋ እየተጠበሰ የሚገኘውን የምሐራ ሕዝብ፤ በጦርነቱ ደግሞ ዐምሐራውንና አፋሩን ጨምሮ የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን መካሥ ይገባል፡፡ ቤተ ክህነቱ እንደ እምነት ተቋም ምእመኑ በጅምላ ሲጨፈጨፍ አንዳች ተቃውሞ አላሰማም፤ ደሀ የበደሉትን ፍርድ ያጓደሉትን አላወገዘም፤ ለሞቱት ጸሎተ ፍትሐት አላደረገም፤ በጅምላ ሲቀበሩ ሥርዓት ያለው ቀብር እንዲፈጸምላቸው አላደረገም፤ የሟች ወገኖችን በቦታው ተገኝቶ አላጽናናም፤ የተፈናቀሉትን ረድቶ እንዲቋቋሙ አላደረገም፡፡ ይልቁንም አብዛኛው የሲኖዶሱ አባላት ሥጋዊ ምቾትና ጥቅምን ገሚሱም የግል ክብርን በማስቀደም በሕዝብ ደም ከተጨማለቀው ፋሺስታዊው አገዛዝ ጋር በኅብረት በመሥራትና መሣሪያ በመሆን ቤተ ክርስቲያንን እያፈረሰ ያለውን ኃይል  ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶችም በዚሁ ነውረኛ ድርጊት ቀጥለዋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተጠሩበትን መንፈሳዊ አገልግሎት ዕርግፍ አድርገው በመተው ቤተ ክርስቲያኒቱን አሁን ለምትገኝበት የህልውና ፈተና የነሱም ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የኢኦተቤክ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ‹አባቶችን› በነገድ ማንነታቸው አያውቁም፤ ማወቅም አይፈልጉም፡፡ የሲኖዶሱ አባላት ከፊሉ ከርጉም ዐቢይና ወያኔ ጋር ተሰልፈው፣ ከፊሉ ጥብዐት አጥተው የጐሣ ሹመትና አደረጃጀትን በዝምታ ካለፉ በኋላ አሁን ላይ በነገድ ማንነታችን ተለይተን እየተገለልን ስለሆነ በነገዳችን ስም ለመሰባሰብ አስበናል የሚሉ የሲኖዶሱ አባላት ሊያነጋግሩን ይፈልጋሉ የሚል (ያልተረጋገጠ) መረጃ ከአንድ ሚዲያ አድምጪአለሁ፡፡ ሚዲያው ይህንን አባባል (የተረጋገጠም ይሁን/አይሁን) ባያስተላልፈው መልካም ነበር፡፡ መንፈሳዊውን የሃይማኖት ጉዳይ እና ዓለማዊውን የሥልጣን/ፓርቲ ፖለቲካ ጉዳይ ባንድነት ማየት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ 

ዐምሐራው ተገዶ የገባበትን የህልውና ትግል ተገቢነት እንኳን ዐምሐራው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያምንበታል፤ ይደግፈዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የሲኖዶስ አባላት በሠሩት መሠረታዊ ጥፋት ምክንያት ተገፋን በሚል ምክንያት በነገድ/በጐሣ መሰባሰብ እንደ አማራጭ አይተውት ከሆነ ባጠቃላይ ከክርስትናው ዶግማ፣ ቀኖና እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ የሚያወጣ መሆኑ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ እንደተባለው ይህንን አስተሳሰብ የያዙ የሲኖዶሱ አባላት ካሉ የርጉም ዐቢይ ተልእኮ አስፈጻሚዎች አድርጌ ነው የማያቸው፡፡ ራሳቸውን በነገድ ማንነት የሚገልጹ የሲኖዶስ አባላት ኹሉ በእኔ እምነት መንፈሳዊ የመሆን/አለመሆን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከክርስትናው ተለይተዋል፡፡ 

በሲኖዶሱ ውስጥ እውነተኛ መንፈሳዊ አባቶች ካላችሁ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያናችን ማኅበራት ኅብረት በተጻፈላችሁ ደብዳቤ መሠረት እንድትፈጽሙ እንደ ልጅነቴ እያሳሰብሁ፤ የምእመኑና የካህናቱ ኅብረት በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ጉዳይ ሙሉ መብት እንዳለውና እንደሚያገባው የምታምኑ ከሆነ፣ የግል ክብራችሁን ወደ ጎን አድርጋችሁ ቤተ ክርስቲያናችንን ለመከፋፈል ብቻ ሳይሆን ለማጥፋት ያለመውን ፈተና ለማራቅ ከሲኖዶሱ ሳትለዩ ከምእመኑ ጋር ሆናችሁ ሰማዕት ለመሆን ጭምር በጥብዐት መዘጋጀት ይኖርባችኋል፡፡

 

 

Filed in: Amharic