>

ፓትርያርኩ በአኵስም የሚፈጸመውን  ሕገ ወጥ ሢመት “አልቃወምም፤ ከእኔ ውግዘት አትጠብቁ” አሉ

ፓትርያርኩ በአኵስም የሚፈጸመውን  ሕገ ወጥ ሢመት “አልቃወምም፤ ከእኔ ውግዘት አትጠብቁ” አሉ

ግዮን መጋዚን

* ለቋሚ ሲኖዶሱ አሳወቁ፤ ቋሚ ሲኖዶስ ለዛሬ 10፡00 አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

•  በመቐለው ጉዞ ለሕገ ወጥ ሢመቱ የሚጠቀሙበትን አይከን እንዳደረሱላቸው ተጠቁሟል፤

•  ‘መንበረ ሰላማ ቤተ ክህነትን’ በበጀት እንዲደግፉ ከደብረ ጽዮን ለተጠየቁት ተስማምተዋል፤

•  ለሕገወጥ ሢመቱ ዛሬ ጧት ዐዲስ አበባ የገቡት አባ ሰረቀ በኤርፖርቱ ደኅንነት ተይዘዋል፤

•  በ‘መንበረ ሰላማ’ ግፊት አገር በታኝ ፖሊቲካ ሲያቀነቅኑ የቆዩ የሥልጣን ጥመኛ ናቸው፤

የበደል አጀንዳን፣ ለአገር በታኝ የፖለቲካ ዓላማ እና ለአፅራረ ቤተ ክርስቲያን የኑፋቄ ሤራ እያቀነቀኑ በዚያ ሽፋን፣ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ለመፈጸም የተዘጋጁትን አራት የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትን በይፋ እንዲቃወሙ በቋሚ ሲኖዶስ የተጠየቁት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ “አልቃወምም፤ ደብዳቤም አልጽፍም” ሲሉ እምቢታቸውን ገለጹ፡፡

አራቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከቀኖና አፍራሽ ሕገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌዴራል መንግሥት፣ ይህንኑ የቤተ ክርስቲያን አቋም ዐውቀውት ከሕገ ወጥ ድርጊታቸው በማስታገሥ እንዲያግዙ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው በቋሚ ሲኖዶሱ አባላት የተጠየቁት ፓትርያርኩ፣ “ተበድለዋል፤ በደሉ ነው፤ በጭራሽ አልቃወምም፤ ደብዳቤም አልጽፍም፤ አላወግዝምም፤ አቋሜ ነው፤ ካራ በአንገቴ ማሳለፍ ትችላላችኹ፤ እዚያው እናንተው እንደፈለጋችኹ አድርጉ፤” ሲሉ፣ በታወቀው እንቢታቸው እንደጸኑ ታውቋል፡፡ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትም፣ ጦርነቱን ደግፈዋል ያሏቸውን አባቶችንም ሊነቅፏቸው ሲሞክሩ ታይተዋል፤ ተብሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር፣ ቋሚ ሲኖዶስ፣ በጽርሐ መንበረ ፓትያርኩ እና በቅርብ የሚገኙ ብፀዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ለዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ላይ ልዩ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል፡፡

ስብሰባው፣ በፓትርያርኩ አቋም ላይ ለውጥ የማያመጣ ከኾነ፣ በቀጣዩ እሑድ፣ ሐምሌ 9 ቀን የዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት እንዲካሔድ በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈው ውሳኔ፣ እንዲዘገይ ሊደረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

ከትላንት በስቲያ ወደ መቐለ ተጉዞ የተመለሰው የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ኮሚቴ፣ ዛሬ በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ የቃል ሪፖርት ያቀረበ ሲኾን፣ የልኡካኑ መሪ የነበሩት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ከቀድሞ ህወሓት ሊቀ መንበር ዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋራ፣ ከሰላም ልኡካኑ አባላት እየተነጠሉ ለብቻቸው ስለተነጋገሩበት ጉዳይ፣ ለቋሚ ሲኖዶሱ እንዲገልጹ በኮሚቴው አባላት ቢጠየቁም፣ “በግልጽ ከተናገሩት የተለየ አልተነጋገርንም፤” ከማለት በቀር በዝርዝር ለማስረዳት ፈቃደኛ ሳይኾኑ ቀርተዋል፡፡

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የመረጃ ምንጮች፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በመጪው እሑድ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በአኵስሙ ለሚካሔደው ሕገ ወጥ ሢመት የሚደረገውን ዝግጅት በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ከዐዲስ አበባ ኾነው ሒደቱን ከሚያሳልጡት ዋነኞቹ የልዩ ጽ/ቤታቸው ሠራተኞች ሲኾኑ፣ ከትላንት በስቲያው የመቐለው ጉዞ፣ ለሕገ ወጥ ሢመቱ የሚጠቀሙበትን አይከን ይዘውላቸው እንደሔዱና እንዳደረሱላቸው ጠቁመዋል፡፡ “አልፈተሽናቸውም እንጂ ብዙ ሻንጣ ነው የያዙት” ብለዋል አንድ የልኡኩ አባል፡፡

በተለይ ከዶር. ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋራ ከአንድ ሰዓት በላይ በዝግ ባደረጉት ምክር፣ በሕገ ወጡ ሢመት የሚጠናከረው ‘መንበረ ሰላማ ቤተ ክህነት’ ራሱን ችሎ እስኪቋቋም የካህናት ደመወዝ በመክፈል እና በሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲደግፉ በግልጽ እንደጠየቋቸውና እርሳቸውም እንደተስማሙ ተሰምቷል፡፡ ከአህጉረ ስብከቱ ጋራ በተገናኘ ሰሞኑን፣ በልዩ ልዩ ሰበብ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ወጪ የሚደረጉ ሒሳቦችም ኾኑ፣ የሕገ ወጡ እንቅስቃሴ የዐዲስ አበባ ተላላኪዎች(የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ፕሮቶኮል መምህር ልሳነ ወርቅ ደስታ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ ጽ/ቤት ዋና ሓላፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ እና በጡረታ ላይ የሚገኙት መጋቤ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም)፣ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግባቸው ተጠይቋል፡፡

ለአኵሱሙ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት፣ የግል እና የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች እንዲገኙ ጥሪ የተላለፈ ሲኾን፣ ከተሿሚዎቹ አንዱ እንደሚኾኑ የሚጠበቁትና በአውስትራልያ የቆዩት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አባ ሰረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፣ ዛሬ ጠዋት ዐዲስ አበባ ገብተው በትራንዚት ወደ መቐለ ሊጓዙ ሲጠባበቁ ታይተዋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ የትራንዚት በረራቸው ዘግይቶ፣ በአየር ማረፊያው የደኅንነት አካል ተይዘው በጥያቄ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አባ ሰረቀ በሚለው ስማቸው ሳይኾን፣ በሌላ የፓስፖርት ስም የገቡት የ‘ሀገረ ትግራይ’ አቀንቃኙ ግለሰብ፣ ወደመጡበት እንዲመለሱ ይደረግ እንደኾን ወይም ተፈቅዶላቸው ወደ መቐለ ያቀኑ እንደኾን ቆይቶ የሚታይ ይኾናል፡፡

በቀድሞው የህወሓት አመራሮች ፖለቲካዊ እገዛ የሚደረግለት፣ በጎሠኛ ጥላቻ በአበዱ የዳያስጶራው ጥቅመኞች እና በተሐድሶ ኑፋቄ አቀንቃኞች በገንዘብ እና በሚዲያ ቅስቀሳ የሚደግፉት፣ ኢትዮጵያን የመበተንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማውደም ፀራውያን የተባበሩበት አገር በታኝ እንቅስቃሴ ነውና፣ ዛሬ በቋሚ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ጉባኤ፣ በችግሩ ልክ መክሮ ተገቢውን አቋም ሊይዝበት ይገባል፡፡

https://fb.watch/lKtrn6EGtW/?mibextid=Nif5oz

Filed in: Amharic