>

ምናልባት የርጉም ዐቢይ ጦር ከዐምሐራ ‹ግዛቶች› ቢወጣስ?

ምናልባት የርጉም ዐቢይ ጦር ከዐምሐራ ‹ግዛቶች› ቢወጣስ?

ከይኄይስ እውነቱ

የዐምሐራም ሆነ የቀረው ኢትዮጵያዊ ግዛት ወያኔ ሕውሓት እና ኦነግ ተሠርቶ ያደረን አገር ለማፍረስ በጻፉት ‹የደደቢት ሰነድ› የተዋቀረው ‹ክልል› ያሉት በረት ወይም የወያኔ የግብር ልጅ ኦሕዴድ/ኦነግ ተሸክሞ የሚዞረው የቅዠት ካርታ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ርእሰ ጉዳይ አድርጌ በጥያቄ መልክ ያነሣሁት አሳብ ምድር ላይ ያለውን እውነታ – በይፋ የጦርነት ቀጣና የሆኑትን አራቱን የዐምሐራ ክፍላተ ሀገራት (ሺዋ፣ ቤተ-ዐምሐራ፣ ጎጃምና ጎንደር) – መሠረት በማድረግ የቀረበ ነው፡፡ 

ርጉም ዐቢይ የሥልጣን ዕድሜውን አንድም ቀን እስካራዘመለት ድረስ እንኳን ለዐምሐራው እየማገደ ላለው የራሱ ጦር አንዳች ደንታ እንደሌለው ደጋግሞ አሳይቶናል፡፡ ንጹሐን ዐምሐራዎችን ብቻ ሳይሆን የራሱን ጦር ሰው አልባ በሆነ አውሮፕላን (በድሮን) እስከመምታት ደርሷል፡፡ ይህ ልቡሰ ሥጋ ሰይጣን ተስፋ በቆረጠ ቊጥር ጥፋቱ እየጨመረ እንደሚሔድ ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ በጫናም ሆነ ራሱን የሚያተርፍ መስሎት በማያቋርጥ ሁናቴ ሽንፈት የደረሰበትን ጦሩን ከዐምሐራ ግዛቶች አወጣለሁ ቢል ቀጣይ ርምጃችን ምን ይሆናል? 

በእኔ እምነት ፋኖው የዐምሐራ ሕዝብም ሆነ የአብራኩ ክፋይ ጀግናው ፋኖ ባገዛዙ ዘሩን ለማጥፋት ጦርነት ታውጆበት ወደ ህልውና ትግሉ ሲገባ የቆመለት ዓላማ መልሱን በማያሻማ ሁናቴ አስቀምጦታል፡፡ መነሻዬ የዐምሐራ ህልውና መዳረሻዬ የኢትዮጵያ አንድነት በሚል፡፡ በሌላ አነጋገር ርጉም ዐቢይ እንዲሁም የሕወሓትና ኦነግ ቆሻሻ አስተሳሰብ ከምድራችን ተወግዶ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በእኩልነት የሚታዩበት የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት መሆኑን በደማቁ የተሠመረበት ነው፡፡ ባጭሩ የዐምሐራ የህልውና ትግል የምንይልክን ቤተ መንግሥት ላይቆጣጠር አልተጀመረም፡፡ ምክንያቱም ፋሺስታዊው አገዛዝ እስካልተወገደ ድረስ ለዐምሐራውም ሆነ ለኢትዮጵያ ደኅንነት ዋስትና የለምና፡፡

ታዲያ ይህ ስኬት ትግሉን ለጀግኖቻችን ብቻ በመተው የሚደረስበት ሳይሆን ተደጋግሞ እንደሚነገረው ማንም ኢትዮጵያዊ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኝ በትውልዱ ዐምሐራ ብቻ ሳይሆን ትግሉን ተስፋ የሚያደርገውና ዕጣ ፈንታችን ዕድል ተርታችን በጋራ የተሳሰረ መሆኑን የሚያምን ኢትዮጵያዊ በሙሉ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በሚችለው መንገድ አረመኔያዊውን አገዛዝ ፋታ ሳይሰጥ መታገል ይኖርበታል፡፡ በሌላ ቋንቋ ማንኛችንም ከትግሉ በአፍኣ ሆነን የራሳችንን ጥግ ይዘን ነፃ አውጪ መጠባበቅ የዘመናት ስንፍናን እና ግዙፍ ጥፋት መድገም እንደሚሆን ለአፍታ መዘንጋት የለብንም፡፡ በባለቤትነት መንፈስ የምንነሣበት ጊዜ በእጅጉ ዘግይቷል ከሚባል በቀር አሁን ነው፡፡ በተለይም የዐዲስ አበባ ነዋሪ በሙሉ ልጆችህን ቤተሰብህን ለዚህ ፋሺስታዊ ኃይል በየዕለቱ እየገበርህ የምትዘልቅበት ሁናቴ ባስቸኳይ ሊቆም ይገባል፡፡ ይሄም ኑሮና ሕይወት ሆኖ ያሳሳል እንዴ?

አሰፍስፈው የሚጠባበቁን፣ ሰይጣናዊውን ዓለም የተቆጣጠሩት ምዕራባውያን እና ፋሺስታዊውን አገዛዝ የሚራዱት ቱርክና አንዳንድ የዓረብ አገራት በደም በሕይወት እየከፈልን ባለው መሥዋዕታችን ጣልቃ ገብተው ተስፋችንን እንዳያጨልሙብን ነቅተን ተግተን ልንከታተል ይገባል፡፡ ኹለንተናዊ ትግላችን እንደተጠበቀ ሆኖ ጩኸቱ ለእኛ ውድቀት ወደሚያስቡት ምዕራባውያን ሳይሆን ክርስቲያኑም ሆነ እስላሙ ወደሚያመልከው ፈጣሪው ሊሆን ይገባል፡፡

በመጨረሻም ከርእሴ በመጠኑ ያፈነገጠ ጉዳይ በማንሣት ነገሬን እቋጫለሁ፡፡ ባለፈው ጊዜ የህልውና ትግላችንን በብርቱ እየተፈታተኑት ስላሉ ከሀዲዎችን እና በሃይማኖትና በሽምግልና ስም የተሰማሩ ሐሰተኞች ተላላኪዎችን በሚመለከት አንድ ጽሑፍ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ እነዚህን ሆን ብለውም ይሁን በእውር ድንብር የተሰማሩ ተላላኪዎችን በቊጥጥር ሥር ያዋሉ ጀግኖቻችን ሲገሥፁና ሲመክሩ እገረ መንገዳቸውን (ተላላኪዎቹ አርፈው እንዲቀመጡ በማሰብ) የፌዴራሉ መንግሥት ከፈለገ ያነጋግረን የሚል ቃል ሰምቼአለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ‹መንግሥት› የላትም፡፡ በመጀመሪያ የዘር ማጥፋት እየፈጸመብን ያለ ፋሺስታዊ ቡድን ተራ ወንበዴ እንጂ መንግሥት ሊባል አይገባም፡፡ ጠላትን በግብሩ መግለጽ እንጂ ልማድ ሆኖብን የአክብሮት ቃላት መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ ወራዳ ባለጌን በስሙ መጥራት ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠልም ለዓመታት በጨዋ ደንብ አቤት ስንል ስንለማመጠው ቆይተን ንቆን በአውሮፕላን ጭምር እየፈጀን ያለውን አረመኔያዊ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስወገድ መገላገል እንጂ ዕውቅና ሰጥተነው ከዐምሐራ ሕዝብ ፊት እንዲቆም በጭራሽ አንፈቅድለትም፡፡ ወግድ! አንተ ሰይጣን! ማለት ብቻ ነው የሚገባን፡፡ በነገራችን ላይ የሥርዓት መንግሥት አወቃቀርን በሚመለከት በብዙዎች ዘንድ መሠረታዊ ስሕተት አስተውላለሁ፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን አንድ አገር የትኛውንም ሥርዓተ-መንግሥት (ፌዴራል ወይም አሐዳዊ) ይከተል የሚኖረው አንድ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ በአስተዳደር ግዛቶቹ ልክ ሠላሳ መንግሥት አይኖርም፡፡ በግዛቶች ወይም በክፍላተ ሀገራት ውስጥ የሚኖረው መንግሥት ሳይሆን አስተዳደር ብቻ ነው፡፡ መስተዳድር ብሎ መግለጽ ይቻል ይሆናል፡፡

 

ድል ለዐምሐራ ፋኖ! ድል ለኢትዮጵያ!!!

Filed in: Amharic