>

አብይ አህመድ ብዙ ሊያስጮኽው የፈለገው፣ የሱማሌላንድ የኢትዮጵያው መንግስት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም አላማው ምንድነው?

አብይ አህመድ ብዙ ሊያስጮኽው የፈለገው፣ የሱማሌላንድ የኢትዮጵያው መንግስት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረም አላማው ምንድነው?

ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ወይስ የስልጣን እድሜ ማራዘም? እንዲህ አይነት ሰነድ በዚህ ሰአት ለምን መፈረም አስፈለገ? ባጭሩ፤

ከሶማሌላንድ በኩል።

ሶማሌላንድ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1991 ጀመሮ ከሶማሊያ ተለይታ ቆይታለች ። አለም አቀፉን ማህበረሰብ “ራሷን የቻለች ሃገር አድርገህ ቁጠረኝ” የሚል ያልተቋረጠ ተማጽእኖ አድርጋለች ። አንድም ሃገር እውቅና ሊሰጣት አልፈለገም። ኢትዮጵያን ጨምሮ። ለምን?

ጥቂት ምክንያቶች

• የተባባሩት መንግስታትና የአፍሪካ አንድነት ቻርተር፣ የሃገራትን የማይከፋፈል ሉአላዊ ግዛትነትና ክቡርነት የሚደነግግ አንቀጽ በምስረታ ሰነዳቸው ውስጥ ስለተካተተ ድርጊታቸው የአለም አቀፍ ህግና ስምምነቶች የሚጥስ ስለሆነ እውቅና መስጠት አልፈለጉም።

• ለሶሜላንድ አለም አቀፍ ህግ ጥሶ የሚሰጥ እውቅና የተለየ ስትራተጂክ ጥቅም ያስገኝልኛል ብሎ የሚያምን ሃገር አለመኖሩ፣ በተለይ ትልልቆቹ የአለም አቀፍን ህግ በመጣስ የሚታወቁት ሃገራት ሶማሊያ አንድ በመሆኗ ጥቅም እንጂ ጉዳቱ ስላልታያቸው ነው።

• በሌላ በኩል ትልልቅ ያልሆኑ ብዙዎቹ የአፍሪካ የአረብና የእስያ ሃገራት፣ በብዛት የተለያዩ የመገንጠልና ሃገር የመሆን ፍላጎት ያላቸው ማህበረስቦች በውስጣቸው ይዘወ የሚኖሩ በመሆኑ፣ ከሶማሊያ ለሚገነጠል ሃገር እውቅና በመስጠት ነገ ከራሳቸው ተገንጥለው ሃገር እንሆናለን ለሚሉ ክፋዮችቻው ሌሎች ሃገሮች እውቅና መስጠት የሚችሉበት የህግና የሞራል ማእቀፍ መፍጠር ስለማይፈልጉ ነው።

• በተለይ አፍሪካ ፣ በተለይ ደግሞ ወደ ምስራቅ አፍሪቃ ስንመጣ በቀላሉ እንደ ሱማሌላንድ ሃገር ልሁን የሚል ጥያቄ ሊያነሱ የሚችሉ በርካታ ማህበረስቦች ያሉበት ሁኔታ ስላለ ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠት በራስ ላይ ችግር መጥራት አድርጎ በሁሉም ሃገራት እንዲታይ አድርጎታል። ይህ እውነታ ሶማሌላንድ 33 አመታት ያስቆጠረ ህልውና ቢኖራትም ሉአላዊ ሃገር ሆና እንዳትቆጠር እንቅፋት ሆኖባት ቆይቷል።

• ሶማሌላንድ ሉአላዊ ሃገር ባለማሆኗ፣ በተከታታይ ከብዙ የአፍሪካ ሃገሮች የተሻለ ምርጫ ብታደርግም በምርጫ የመጣው መንግስቷ አለም አቀፍ ተቀባይነት የለውም። ሃገሪቱ በአለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት፣ የዲፕሎማሲ የፖለቲካ መድረኮች አትካፈልም። አትሳተፍም። ውል አትፈራረም። የዚህ መዘዝ ኢኮኖሚው ባላበት እንዲረግጥ፣ ደህነነትና ሰላሙ አስተማማኝ ሆኖ እንዳይቀጥል፣ ሁሌም ባልተረጋጋ ሁኔታ የምትኖር ሃገርና የፖለቲካ አመራራ አንዲኖራት አድርጎታል።

• በመሆኑም የሶማሌላንድ መሪዎች ሃገራዊ እውቅና ለማግኝት ምንም ነገር ለማድረግ ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ እንዲገደዱ አድርጓቸውል። የባህር በር መውጫ የተወሰነ መሬት ሰጥቶ ኢትዮጵያን ከመሰለ ሃገር እውቅና ማግኘት ትልቅ ነገር ነው። እርግጠኛ ነኝ አብይ አህመድ “በውደም ሆነ በግድ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የባህር በር ማግኝት ይኖርባታል” የሚል ዲስኩሩን ማሰማት ከጀመረ በኋላ የሶማሌላንድ መሪዎች “የአብይን ፍላጎት በማሳካት የሃገር እውቅና ማግኘት የምንቸለው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት ዝግጅት ሲያደርጉበት የቆየ መሆኑ አያጠያያቅም። ሰለዚህም የሶማሌላንዱ ሙሴ ቢሂ አብዲ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በግማሽ ቀን ውስጥ በተደረገ ውይይት መሬት ሰጥቶ የሃገር እውቅና አግኝቶ መሄድ ችሏል።

በኢትዮጵያ በኩልስ

በኢትዮጵያ በኩል ለሶማሌላንድ የሃገር እውቅና እንዳትሰጥ አድርጎ ያቆያት በርካታ ምክንያቶች ነበሩ። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ሆነ የአፍርካ አንድነትን ድርጅት ቻርተር መፈረም ብቻ ሳይሆን ድርጅቶቹን ከመሰረቱት ጥቂት ቀዳሚ ሃገሮች አንዷ ናት ። ከሌሎች ሃገሮች በተለየ የእነዚህ ተቋማት ደንቦችና ህጎች አክብራ መገኘት የሞራላን ታሪካው ግዴታ እንዳለባት የሚሰማት ሃገር ናት። ይህን ግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ ምወሰን አትችልም።

በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ እንደ ሱማሌላንድ ራሳችንን ችለን ሃገር መሆን እንፈልጋለን፣ እንሆናለን የሚሉ፣ እንዲያውም ይህን ፍላጎታቸውን የሚያበረታታ ህገመንግስት አጽደቃ፣ የሃገሪቱን የውስጥ አስተዳደር ለእንዲህ አይነቱ መገነጣጠል አመቻችታ የተቀመጠች ሃገር በመሆኗ በስልጣን ላይ ያሉ መሪዎቿ ለሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት የራሳቸውን ተገንጣዮች ማበረታታ ሌሎችም ሃገሮች ከኢትዮጵያ እንገነጠላለን ለሚሉ እውቅና እንዲሰጡ መንገድ የሚከፍት አርአያነት ያለው ሚና መጫወት አይፈልጉም ነበር።

የአብይ አህመድ መንግስት የዛሬ 6 አመት ወደ ስልጣን ሲመጣ ለሶማሌላንድ እውቅና የሚሰጥ ጥያቄ ቢቀርበለት “የሰይጣን ጆሮ አይስማ” የሚል መልስ ሊሰጥ እንደሚችል የታወቅ ነው። ዛሬ በትዊተሩ ገጹ ላይ እንዳሻው የሚሳለቅበትን የፈጣሪን ስም በከንቱ እየጠራ “የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ” በሚል ለሱማሌላንድ የሰጠውን እውቅና መንፈስዊ ቅብ ቀብቶት እያየነው ነው።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካም ሆነ ከምስራቅ አፍርቃ ሃገራት በተለዬ ለሶማሌላንድ የሃገር እውቅና መስጠት አደገኛ የብሄራዊ ጥቅም መዘዘ ያስከትልባታል ተብሎ ስለታመነ እስከ ዛሬ ይህን እርምጃ ሳትወስድ ቀርታለች። ታዲያ አሁን ምን መጥቶ ነው የአብይ አህመድ አገዛዝ ድንገት ብድግ ብሎ ለሶማሌላንድ እውቅና የሰጠው? ለዚህ መልስ የሚሆነው ነጥብ አብይ አህመድ “በውዴታም ሆነ በግዴታ የባህር በር እንዲኖረኝ አደርጋለሁ” ማለት ወጀመረበት ጥቂት ወራት ወደኋላ በመመለስ የሚገኝ ነው።

አብይ አህመድ “በጋር ስምምነት፣ ውልና ጥቅም ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያን የባሃር መውጫ ችግሮች ማስከበር ይቻላል” ከሚል እምነት ከአካባቢው ሃገራት ጋራ ወደጦርነት የሚወስድ ቀረርቶ ማሰማት የጀመረው፣ አገዛዙ በመላው ኢትዮጵያ ተቀባይነት እያጣ፣ ኢኮኖሚው እየተንኮታኮተ፣ የወታደርና የደህንነት አቅሙ እየመነመነ፣ በተለይ በከፍተኛ እብሪት “አማራን ሱሪውን አስወላቃለሁ” ብሎ የገባበት የማንበርክክ ጦርነት እራሱን ሊያንበረከከው የሚችል መሆኑን በተረዳበት ወቅት ነው።

አብይ ጥልቀት የሌው የፖለቲካ ግንዛቤ፣ እውነታን ለማንበብ የሚያስችል ብቃት ያጣ መሪ በመሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብ በተለይ የአማራን ህዝብ “የባሃር በር ላመጣልህ ነው” ብዬ ብነግረው “እኔ ለማስወገድ የጀመረውን ፍልሚያ ትቶ ከጎኔ እንዲቆም ማድረግ ፣ ስልጣኔንም ማራዘም እቻላለሁ” ከሚል ርካሽ ስሌት ውስጥ ገበቶ ነበር። የሰማው አላገኝም።

አብይ ሰለባህር በር ማውራት ከጀመረ ወራት ቢያልፉም እንዴት እንዳስማተኛ ከስማሌላንድ ጋር የባህር በር ማግኘት ስምምነት ከደረት ኪሱ ጎትቶ ማምጣት ቻለ የሚለው ጉዳይ በቀጥታ ከጥቂት ቀናት በፊት ከተከሰተ ሌላ አብይ ጉዳይ ጋር የተሳሰረ ነው። ብጹእ አቡነ ሉቃስ ለአብይ አህመድ የሚያገለግሉ ወታደሮችም ይሁኑ ሲቪሎች የተወገዙ ይሁኑ፣ የሃገር መከላከያ ወደቀልብህ ተመለስ፣ አብይ አህመድን ማስወገድ የማንኛውም አማኝ መንፈሳዊ ተግባር ነው ወዘተ.. የሚል መልእክት ማስተላለፋቸው ነው። በአብይ አህመድ አገዛዝ ተንገፍግፎ መሳሪያ አንስቶ ለሚዋጋው የአማራ ህዝብና ፋኖና ይህ ታጋይ መቼ ይደርስልናል እያለ ለሚናፍቀው ህዝብ ውስጥ የአቡነ ሉቃስ ንግግር ከመቶ ድሮኖች በላይ በስርአቱ ላይ ጉዳት አድርሷል። ስርአቱን ለሚታገሉ የመንፈስ ስንቅ ሁኗል። የአብይን እና የተላላኪዎቹን ህሊና ያሸበረውን የአቡኑን ድምጽ በሌላ ጭኽት መተካት አለብን የሚል ስሌት ነው የመግባቢያ ሰነዱን ፍሪሚያና ፊርማውን ተከትሎ የተፈጠረውን ጭኽት የወለደው።

የአብይ አህመድ አገዛዝ በሩጫ የሶማሌላንድን መሪ አዲስ አበባ አስጠርቶ፣ ለኢትዮጵያ ለቀጠናውና ለአፍሪካ አገራት ትልቅ ቀውሰ ሊፈጥር የሚችል ስምምነት ተፈራራሞ፣ በመንግስት ትእዛዝ የመንግስት ሰራተኞችን የስርአቱ ተከፋዮችን የደስታ ሰልፍ እንዲያደርጉ ያደረገበት ዋናው ምክንያት ይህ ነው። የአቡነ ሉቃስ መልእከት በአብይ አህመድ አገዛዝ መቀበሪያ ሳጥን ላይ የተመታ የመጨረሺያ ሚስማር ነው። የምናየው ትርኢት ክፉኛ የቆሰለ አውሬ የሲቃ ጭኽት ነው። ሌላም አደገኛ እርምጃ መጠበቅ ነው።

በዚህ ወቅት የአብይን ማንነት በሚገባ የተረዳው ህዝብ የአብይን የእበደት ድራማ ወደጎን ገፍቶ አይኑን ከዋናው ሰራው ላይ ሳይነቅል ይህን ግፈኛ ስርአት ለማስወገድ የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። እዚህ ሃተታ ውስጥ ሃብትና ድንቁርና በአንድ ላይ ተደምረው አፍሪቃን በአዲስ የእጅ አዙር የቀኝ አገዝዝ ውስጥ ለመጨመር እየዳከሩ ያሉ የተባብሩት ኢመሬት መሪዎች ሚና አልተነሳም። ከአለም አቀፍ ማሀበረሰቡ በተለየ የምስራቅ አፍሪካን የቀይ ባህርን ሃገራት በማበጣበጥ የቀጠናው የበላይ ገዥ እሆናለሁ የሚል ቅዥት ያላችው የተባባሩት አረብ ኤመሬት መሪዎች ይህ የኢትዮጵያን እና የሱማሌላንድ ውሳኔ ከጀርባ ሆነው የሚደግፉ መሆነቸውን መገመት ከባድ አይሆንም።

ትልቁ ቁምነገር አብይ አህመድ ለሶማሌላድ ሃገራዊ እውቅና በመስጠት የወስደው እርምጃ እሱና ተላላኪዎቹ እንደሚለፈፉት ኢትዮጵያን የጠቀመ እርምጃ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ የከፋ መዘዝ የሚያስከትል የሃገርን ብሄራው ጥቅምና ደህንነትን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ ጸረ ኢትዮጵያ ውሳኔ ነው። የምስራቅ አፍሪቃ ሃገራት በሙሉ ኢትዮጵያን በጠላትነት እንዲያዩ፣ ከተባባሩት አረብ ኢመሬት ውጭ ያሉ የቀጠናው ጉልበተኞችም ከተቀሩት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ጋር ተደምረው በኢትዮጵያ ላይ እንዲያሴሩ የሚያደርግ፣ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ ኢትዮጵያ የአንድነቱን ህብረት ከሚያናጉ ሃገራት ተርታ እንድትመደብ እንድተገለል ተደማጭነቷ እንዲቀንስ የሚያደርግ ውሳኔ ነው። መፍትሄው ይህን ነውረኛ መንግስት በተባባሩ ክንድ አስወግዶ ህዝባችን አብይ ወደቆፈረለት ሲኦል እንዳይገባ ማድረግ ነው።

አንዳርጋቸው ጽጌ

 02/01/2024

 

Filed in: Amharic