የገዱ አንዳርጋቸው ይሁዳዊ “ብልጣብልጥነት”
ከሁለት ሳምንት በፊት፥ እጅግ የማከብረው የሃይማኖት መምህር ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ካስተማራቸው ስብከቶቹ አንዱን ከዩቲዩብ ላይ ሳዳምጥ ነበር። ሰባኪው በትምህርቱ ሙሴና የአስቆሮቱ ይሁዳን ያነፃፅራል። የነገሮችን at face value እና intention በመለየት ዙሪያ ነው የሁለቱን ሰዎች ታሪክ ያመጣው።

ሳሚው ከገዳዩ ይልቅ ፃድቅ ነው ሊያስብል ይችላል። “The devil is in the detail” እንዲሉ ዘመዶቻችን፥ የነገሮችን intent ስንመረምር ነው፥ አንዳንዴ መግደልም መግደል የማይሆነው፣ መሳምም ከንክሻም የከፋ አደገኛ መሆኑን የምናየው። የይሁዳ ብልጠት በዚህ አይበቃም። አይሁድ ክርስቶስን ለመውገር ብዙ ጊዜ ሞክረው ከያዙት በኋላ ከመካከላቸው የተሰወረበት ጊዜ ብዙ ነው። ይሁዳ ይህቺን ጠንቅቆ ያውቃል።
በይሁዳ ስሌት መሠረት ለአይሁድ ካህናት ክርስቶስን ስሞ ከሰጠ በኋላ፥ ክርስቶስ በተለመደው ተአምር ከመካከላቸው ተሰውሮ ሲያመልጣቸው፥ አጅሬው 30 ዲናሩንም ቀርጥፎ፣ ምንም እንዳላደረገ ሰው የክርስቶስ ሐዋርያ ሆኖ ለመቀጠል ነበር ዕቅዱ። ከመባ ላይም የሚሰርቅ ሌባ እንደነበር ሳንዘነጋ። ዕቅዱ ግን ሲከሽፍበትና ክርስቶስ ለሞት ተላልፎ እንደተሰጠ ሲያይ ሄዶ ያደረገውን አደረገ።
የብአዴኑ ይሁዳ ገዱ አንዳርጋቸውም፥ ወደ አሜሪካ ከመጣ እንኳ ስንትና ስንት ወራት አልፈውት ፥ በእነዚያ ወራቶች በፋሽስታዊው የአብይ አህመድ መንግስት ዙሪያ ቃል ሳይተነፍስ ኖሮ፥ በዳንኤል ክብረት ስም አብይ አህመድ ገዱንና ጓደኞቹን እየሰደበና እየረገመ መፅሐፍ ሲፅፍባቸው፥ ልክ የአስቆሮቱ ይሁዳ የተቀደሰውን የመሳሳም ሠላምታ ለእኩይ አላማው እንደተጠቀመበት ሁሉ፥ የብአዴኑ ይሁዳ ገዱ አንዳርጋቸውም የተቀደሰውን የአማራ ትግል ታክኮና ለአማራ ህዝብ የተቆረቆረ መስሎ፥ የምናውቀውን የአብይ አህመድ ባህርይ እንደ አዲስ ሊነግረን ተጋጋጠ።

መሠሪው አብይ አህመድ የፋኖን ትግል “ህዝባዊ መሠረት የሌለው ይልቁንም ያኮረፉ ብአዴኖች የሚዘውሩት ነው” …የብአዴኑ ይሁዳ ገዱ አንዳርጋቸውም በወጣትነትና በጉልምስና ዘመኑ ሲበድለውና ሲያስበድለው የነበረውን የአማራ ህዝብ መደበቂያ በማድረግ ለአማራ የተቆረቆረ በመምሰል፥ እንደ አማዞን ወንዝ የረዘመ Sugarcoated የሆነ በውስጠ-ወይራ የመልስ ምት ይዞ ብቅ አለ።
የብአዴኑ ይሁዳ እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ 30 ዲናሯንም፣ ከክርስቶስ ጋር ሆኖ ሳይራብና ሳይጠማ፣ ሳይደክምና ሳይታመም የመኖር ቁማርን አስልቶ ነው ፅሁፏን ያወጣት። በአንድ በኩል፥ በመፅሐፍ ፅፎ የጦስ ዶሮ ያደረጋቸውን ፋሽስቱ አብይ አህመድን መበቀል፣ በሌላ በኩል “ገዱ ተፀፅቶ ይቅርታ ጠይቋል” በሚል ሽፋን የአማራ ትግል መሪ ሆኖ የመውጣትና ትግል የመጥለፍ።
ገዱ አንዳርጋቸው ከፈለገ ከአብይ አህመድ ጋር እንኳን መሰዳደብ ቀርቶ መገዳደልም ግለሰባዊ መብቱ ነው፤ ነገር ግን የአማራን ትግል ጭምብል ማድረግና የአማራ ተቆርቋሪ መስሎ መምጣት አይችልም!!
ፋኖ በነፍጥ የሚጋደለው እንደሙሴ የወገኖቹ ስቃይ ቢያመው ነው፣ ገዱ ዛሬ አማራን የሳመው ግን እንደ አስቆሮቱ ይሁዳ ሁለት ቁማሮችን አስልቶ ነው!!
“ወግድ ይሁዳ!!” እንዲሉ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱ፥ እኛም የብአዴኑን ይሁዳ (ገዱ አንዳርጋቸውን) ወግድ (ዞር በል! ) ልንለው ይገባል!!
( ዴቭ ዳዊት)