ውኃና ኤሌክትሪከ አልባ ዐዲስ አበባ
ከይኄይስ እውነቱ
የዐባይን ልጅ ውኃ ጠማው፡፡ የኤሌክትሪክም ብርሃን ናፈቀው፡፡
ለመሆኑ ጀማውን ከሀገር ውስጥ እስከ ባሕር ማዶ የሚያጃጅሉበት፣ የማያቋርጥ መዋጮ በውድም በግድም የሚጠይቁበት፣ እኛን አንበሽብሾ ለጎረቤት እንሸጣለን ተብሎ የተፎከበረበት፣ከታሪካዊ ጠላት ጋር ሽርክና የፈጠሩበት፣ ጠላትን ለማስደሰት በትልቁ ተጀምሮ አሁን ላይ የኮሰመነው፣ ካልጠፋ ቦታ በፖለቲካ አሻጥር ድንበር ላይ ወስደው የሰነቀሩት፣ ከጥንስሱ እስካሁን የፕሮፓጋንዳ ማዕከል ያደረጉት አወዛጋቢው የዐባይ ግድብ የት ደረሰ?
ያለንበት ወቅት እንደሚታወቀው ወርኀ ክረምት ነው፡፡ ያውም ድቅድቁ የሐምሌ ጭለማ፡፡ ከላይ ውኃ ከታች ውኃ የሆነበት ጊዜ፡፡ ዝናቡ ቢያበሰብሰንም፣ በግብር ይውጣ የሚሠራው መንገድ መተላለፊያ ቢያሳጣንም፣ በክፍለ ሀገርም መሬት መንሸራተት አስከትሎ ወገኖቻችንን በሞት ቢነጥቅብንም፣ ዐዲስ አበባን ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እጦት እየናጣት ነው፡፡ ከአገዛዙ ጋር በዝርፊያ ለተሰማሩና (ከውኃ ክፍል ጋር በመመሳጠር ለሚሠሩ) ቆሻሻ ውኃ በቦቲ (የውኃ መያዣ የተገጠመለት ልዩ ተሽከርካሪ) ለሚሸጡ ወንበዴዎች ሠርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ያቀረብሁትን ጽሑፍ መለስ ብሎ ማየት ተገቢ ይመስላል፡፡ መቼም አንዳች ሀገራዊ አጀንዳ ከሌለው አገዛዝ መፍትሔ የሚጠብቅ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ የበሬው ‹ፍሬ› ይወድቅልኛል ብላ እንደምትከተለው ቀበሮ ብጤ ይሆናልና፡፡
በነገራችን ላይ ለማነሣቸው አንኳርም ይሁን ድቁቅ ሀገራዊ ጉዳዮች መፍትሔ እንዳትጠይቁኝ፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በማያወላዳ ቃል ነገረዋችኋልና፡፡ እኔ የምጨምርበት ከነ ቆሻሻ ‹ሥርዓቱ› የሚል ብቻ ነው፡፡ ለሁሉም ችግር/‹በሽታ› መፍትሔ (panacea) ባይሆንም ነቀርሳውን/ሰንኮፎን በዋናነት ይነቅላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ርጉም ዐቢይ ጨርቁን እስከሚጥል ድረስ በዐዲስ አበባ ውስጥ ‹ፕሮጀክት› በሚል የማይገባ ስም የሚፈጽማቸው ፌዞች ‹ዕቃ ዕቃ› የሚጫወት ኩታራ አስመስሎታል፡፡ ሰውዬው ኹለተኛ ተፈጥሮው የሆነው ቅጥፈት የመጨረሻው ጫፍ ደርሶ ከምሩ ራሱን ማታለል ከጀመረና ‹እውነት› ነው ብሎ መቀበል ከጀመረ ከራርሟል፡፡
ከጦርነት፣ ዝርፊያና ንቅዘት የተረፈውን የአገሪቱን ጥሪት በጊዜያዊ ብልጭልጭ ነገር ላይ እያዋለ ይገኛል፡፡ ይህንንም የሚያደረገው የጅምላ ግድያውን፣ በሚልዮን ማፈናቀሉን እና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተመሳጥሮ አብዛኛውን ሕዝብ መናጢ ማድረጉን በመቀጠል ነው፡፡ አንዳንድ የዋሐንና ከርሣም ደጋፊዎች ‹ከተማ ማደግ መዘመን› የለበትም ወይ? ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የማይረባ ጥያቄ፡፡ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ሕይወት ማዕከሉ የሰው ልጅ ነው፡፡ በነጻነት የተፈጠረ ሰው ነጻነቱ ካልተገፈፈ፣ መብቱ ከተከበረ፣ ለሕይወቱ ዋስትና ካለው፣ ሰላም ካለ፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሠርቶ ማደር ከቻለ፣ ለዚህም ዋስትናና ጥበቃ የሚያደርግለት ሕዝብና አገር የሚወድ ለብሔራዊ ጥቅም የሚሠራ መንግሥት ካለ፣ በዚህ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባደገበት ዘመን የሃምሳ ዓመቱን በዐሥር ዓመት ሊያከናውነው ይችላል፡፡ ሕዝብና አገርን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየሠራ ካለ ዲያቢሎሳዊ ኃይል ዕድገትና ልማት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡
ጥላውን እየፈራና ከሞት ለማምለጥ እንደ ዥብ ሌሊቱን እየዞረ ከተማ ማፍረስ ጽኑ ዕብደት እንጂ ባለአእምሮነት አይደለም፡፡ አብነት ካደረጋቸው፣ ሕዝብ መፍጃ ድሮን ከሚሰጡት እና በልዋጩ የመናገሻ ከተማችንን መሬት ያለ ማንም ከልካይ ከሚያከፋፍላቸው ጥቂት የዓረብ አገሮች መንግሥታት ያየውን እንደ ሕፃን ልጅ አይቅርብኝ ብሎ ቅዠቱን ሁሉ በዐዲስ አበባ ላይ እየሞከረ ነው፡፡
እናንተዬ ምን ዓይነት ሸላ ነው በከተማው ሌሊቱን ሙሉ በየመንገዱና ሕንፃው የብርሃን ጎርፍና ውኃ ሲያፈስ እያደረ፣ ነዋሪውን ሁሉ ጭለማ አልብሶና ውኃ ከልክሎ የሚዝናና የሚፈነድቅ? ለመሆኑ ብልጭልጩን ለማነው የሚሠራው? ማን እንዲያይለትና እንዲያደንቅለት ነው? ለግሉ እርካታ ነው? በውኑ በዚህ በማይፈወስ ድውየ አእምሮ እጅ መውደቅ የሱ ወይስ የኛ የሕዝቡ ጥፋት?