>
5:26 pm - Wednesday September 15, 4990

የአትሌቲክስ ዲፕሎማሲ እና ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ!!

የአትሌቲክስ ዲፕሎማሲ እና ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ!!

ተረፈ ወርቁ ደስታ

አበበ በቂላ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ማራቶንን ሪከርድ ሰብሮ ባሸነፈ ማግሥት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በፊት ገጻቸው ላይ የሚከተለውን ዜና ይዘው ወጥተው ነበር፤ ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የጣሊያን አገር ሁሉ ወታደር አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮም ወረረችው፤››

ታሪክ እንደሚነግረን፤ አበበ በቂላ የመጀመሪያው አፍሪካዊ/ጥቁር የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነው፡፡ ይህ የአበበ ብቂላ ድል በርካታ የማራቶንና የረጅም ርቀት የኦሎምፒክ ጀግኖችን አፍርቷል፡፡ ለ27 ጊዜያት የዓለምን ሪከርደሮችን የሰባበረው የክፍለ ዘመናችን ጀግና አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴም ደግጋሞ እንደሚለው፤ የእነ አበበ ብቂላና የእነ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የኦሎምፒክ ድል በደም ውስጥ ሰርጾ በዓለም የኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ምልክት እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ይህ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ደጋግሞ የነገሠበት የኦሎምፒክ ድል ለኢትዮጵያና ለመላው አፍሪካ የአትሌቲክስ ዲፕሎማት/የክብር አምባሳደር እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ለአብነትም፤ እንደ አትሌት ኃይሌ ያሉ የክፍለ ዘመናችን የአትሌቲክስ ጀግኖችና አምባሳደሮች፤ በደቡብ አፍሪካዊው የፀረ-አፓርታይድ ታጋይና የነጻት አባት በኔልሰን ማንዴላ ልብ ውስጥ የኢትዮጵያውያንን የነጻነት፣ የአሸናፊነት የድል አድራጊነት መንፈስ ከፍ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ሥላሴ በአትላንታ ኦሎምፒክ ለሀገሩና ለአኅጉሩ አፍሪካ ላመጣው ድል/የወርቅ ሜዳሊያ- ኔልሰን ማንዴላ ለጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የሕይወት ታሪካቸውን የከተቡበትን ‹‹Long Walk to Freedom›› መጽሐፋቸውን በፊርማቸው አበርክተውለታል፡፡

ማንዴላ በመጽሐፉ የውስጥ ሽፋን ባሰፈሩት መልእክታቸውም፤ ጀግናውን አትሌት ሻለቃ ኃይሌን፤ ‹‹አንተ የአፍሪካ/የጥቁር ሕዝቦች የጀግንንት ሕያው ተምሳሌት/the African Legend›› በማለት ነበር ያሞካሹት፡፡ ሻለቃ ኃይሌም በተራው ለእኚህ ታላቅ የነጻነት አባትና አርበኛ በትላንታ የኦሎምፒክ ተወዳድሮ ያሸነፈበትን ማሊያና ቁምጣ ልኮላቸዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ ጀግኖች አትሌቶቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ክብር፣ መወደድና ዝና ለሀገረ ገጽታ ግንባታና ለውጪ ግንኙነት/በአትሌቲክስ ዲፕሎማሲ ረገድ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሀገራችን በረጅም ርቀትና በማራቶን ሩጫ በዓለም መድረክ የገነነ ስምና ዝና ያላት ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም ይህን በዲፕሎማሲው መስክም ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ የአትሌቲክስ ዲፕሎማሲ ጉዳይን በተመለከተም ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ከአዲስ ዋልታ/ካሪቡ አፍሪካ ጋር ያደረገውን ቆይታ በዚህ ማስፈንጠሪያ/ሊንክ መመልከት ይቻላል፡፡

“ለድጋፍ ነበር የሄድኩት፣ ወርቅ ይዤ ተመለስኩ” – ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ – ክፍል 1 | ካሪቡ አፍሪካ (youtube.com)

https://youtube.com/watch?v=i-wjapagIQg&si=G1A9_405nezKX8AT

Filed in: Amharic