አሞራ በብዛት ሲያንዣብብ ካየህ ቅርጫ አለ ማለት ነው!
አብይ አህመድና ብአዴናውያን እስክንድር ነጋን ለምን ለቅርጫ ፈለጉት? ለምን የእስክንድር ነገር ለሁለቱም የእግር እሳት ሆነባቸው?
የሚያገናዝብ አእምሮ ካለህ የዚህን ጥያቄ ዱካውን ተከተል።
የአብይ አህመድን ገዳይ ስርዓት ከስሩ ነቅሎ (መንግሎ) ለመጣል በቁርጠኝነት የሚታገለው እስክንድር ነጋ ለምን ለዘመነ ካሴ፣ ለአበበ ፈንቴ ፣ ለአስረስ ማረ እና ለመሰሎቻቸው ስጋት ሆነ?
እውነት እስክንድር የዐማራ ህዝብ ጠላት ነው? የዐማራ ህዝብ መከራና ሰቆቃስ እንዲቀጥልስ ይፈልጋል? ለምን?
የብአዴን ወጣት ሊግ ደቀመዛሙርት እና የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች Roll modell ህወሃት ነች። አሁን አሁንማ ሳያቸው የቀራቸው ስሟን መኮረጅ ብቻ ነው።
ህወሃት “ዐማራ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን ይጨቁን ነበር” የሚለውን የሐሰት ትርክት ለኦሮሞዎችና ለሌሎች ብሔረሰቦች ስታስተምር “ጭቆናውን በጥልቀት ተንትና” በመፅሃፍ አሳትማለች፣ “ጡታቸው ለተቆረጠ” የኦሮሞ እናቶች “መታሰቢያ” አኖሌ ላይ ሃውልት አሰርታለች።
ትርክቱ በመማሪያ መፃህፍት ተካቶ የኦሮሞ ህፃናት እንዲማሩት አድርጋለች፣ ግጥምና ዜማ ተሰርቶለት ህዝቡ በቁጭት እንዲዘፍነው አድርጋለች። አሁን ድረስ ይህ የሐሰት ትርክት እውነት ነው ብለው የሚያምኑ ዛሬ ህወሃት ራሷ እያለቀሰች ብትነግራቸው የማያምኑ በርካቶች አሉ።
በዚህ የሐሰት ትርክት ምክንያት በርካታ ዐማራ ወገኖቻችን ህይወታቸው ተቀጥፏል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ ለስደትና ለመከራ ተዳርገዋል።
ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው ብአደኤናውያን እስክንድርን ቅስሙን ሰብረው፣ አንገቱን አስደፍተው ከዐማራ ፋኖ ትግል ለማስወጣት እረፍት አጥተው፣ ተናበው እየሰሩ ይገኛሉ። እጅግ በሚገርም ሁኔታ በጀት መድበው፣ “እስክንድር ነጋ ፋኖን በዶላር ገዛ” የሚል የሃሰት ትርክት ፈጥረው፣ ለትርክቱ ግጥምና ዜማ ሰርተው፣ ነጠላ ዜማ አዘጋጅተው ፣ በዘፈን ሰንደው ይዘው ተከስተዋል። መቸም ” ሞኝና ወረቀት እንዳስያዙት” ነውና ይህ ሳያላምጥ የሚውጠው የማህበረሰባችን ክፍል ዘፈኑን ተቀብሎ እስክስታውን እያስነካው ይገኛል።
አሁን መጠየቅ ያለበት ቁልፍ ጥያቄ አብይ አህመድ ፣ ዘመነ ካሴ፣ አበበ ፈንቴ፣ አስረስ ማረን የመሳሰሉ የብአዴን ወጣት ሊግ እና የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች በአንድ ድምፅ እሰክንድር ነጋን ለምን አምርረው ይጠላሉ?
በአንድ ድምፅ ሁሉም እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን እስክንድር ነጋ ይሰቀል፣ ይሰቀል ይላሉ? እውን እስክንድር ቢሰቀል ዐማራ ይድናል? አብይ አህመድስ ይሸነፋል?
እስክንድር ከአዲስ አበባ ገለል በማለቱ ሲታገልለት የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብ ምን አገኘ? “እብድ፣ ጭር ሲል የማይወድ” ሲለው የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብ አሁን ላይ ምን ይላል? አብይ አህመድ “ከእስክንድር ጋር ወደ ለየለት ጦርነት እንገባለን” ያለውስ ለምን ነበር?
ይህ ሁሉ ጆፌ አሞራስ በዚህ ሰዓት ለምን አንድ ላይ ተሰባሰበ? አብይ አህመድ በድሮን፣ በእግረኛና በብረት ለበስ፤ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች በእግር በፈረስ እስክንድር ነጋን ለምን ይፈልጉታል?
ከላይ በመነሻየ እንደገለፅኩት የተነሱትን ጥያቄዎች ይዞ የዐማራን ህዝብ የህልውና ትግል እግር በእግር ለሚከታተል ሰው መልሱ በጣም ቀላል ነው።
ሁለቱም አካላት እስክንድር እጅ ያዩት አንድ እውነት አለ። እስክንድር ነጋ የሚከተለው ስር ነቀል ለውጥ፣ መነሻውን የዐማራ ህዝብ ነፃነት መዳረሻውን የኢትዮዽያ አንድነት ያደረገው፣ በኢትዮዽያ ሉአላዊነት ላይ የማይደራደረው የእስክንድር ርዕዮተ ዓለም ሁለቱንም ወገኖች እንቅልፍ አልባ አድርጓቸዋል።
ይህ ሃሳብ ገበያ ላይ ያለውን ዋጋ እና ተቀባይነት ከወዲሁ ስለተረዱ ሁለቱም አካላት ከባድ ድንጋጤ ወድቆባቸዋል። በተጨማሪም አብዛኛው የዐማራ ፋኖ ታጋይ ይህን ሃሳብ ይገዛዋል። ማንኛውም ተራ የዐማራ ፋኖ ታጋይ በአጋጣሚ ሲጠየቅ የሚመልሰው ይህንኑ ነው። የዐማራን ህዝብ ነፃ ማውጣትና አባቶቻችን የሰሯትን ሀገራችን ኢትዮዽያን አንድነት ማስቀጠል!
በአንፃሩ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች በኋላ ኪሳቸው ተሸክመው የሚዞሩት እስክንድር እስካለ ድረስ ሊሳካ የማይችል ፣ ነገር ግን በእስክንድር መቃብር ላይ ብቻ እውን ልትሆን የምትችል ሃሳብ አለቻቸው። ለዚህ ነው አምርረው እስክንድር ነጋን የሚጠሉት!
የዐማራ ህዝብ ጠላቶች እስክንድርን ከተቻለ አሸማቀው፣ አዋክበውና አንገት አስደፍተው ደብዛውን በማጥፋት ይህን ሃሳብ ከምንጩ ለማድረቅና ከሰው ልብ ለማውጣት ከፍተኛ በጀት እና የሰው ሃይል መድበው ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ከአብይ አህመድ በላይ የሣልሣይ ብአዴን አዋላጆች እስክንድርን ይፈልጉታል። የግድያ ሙከራን ጨምሮ በርካታ የተቀናጀ ዘመቻ ተከፍቶበታል።
በዚህ ረገድ በተለይ ማረጃ ቴሌቭዥን፣ ሮሃ ሚዲያ፣ ABC ቴሌቭዥን ፣ ግዮን ቴሌቭዥን ከሣልሣይ ብአዴን አዋላጆችና ከስርዓቱ ተከፋይና ወዶ ገብ ግሪሳዎች ጋር በጥምረት ያሳዪት መናበብ እጅግ የሚገርም ነው!
ዐማራውን ከጫወታ ለማስወጣት ብላ በወቅቱ ህወሃት የለኮሰችው “የጨቋኝ ተጨቋኝ” እሳት መልሶ እርሷኑ እየበላት ይገኛል። እርሷም በተራዋ “ጨቋኝ ነበርሽ” ተብላ ኦህዴድ/ ኦነግ በተራው ግጥምና ዜማ አሰርቶ በብሔር ብሔረሰቦች እያስወገዛት ይገኛል።
“በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም” እና ልብ ያለው ልብ ይበል።
(ዳ.ጌ)