>
5:42 pm - Tuesday March 21, 6778

ለሰው ሕክምና የሚውሉ መድኃኒቶች ጉዳይ፤ በቡሓ ላይ ቈረቈር

ለሰው ሕክምና የሚውሉ መድኃኒቶች ጉዳይ፤ በቡሓ ላይ ቈረቈር

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ እንድጽፍ ያሰገደደኝ ባገራችን አሉ ከሚባሉ የሪፈራል ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ ታዋቂ የሕክምና ባለሙያዎች ያገኘሁት አስደንጋጭ መረጃ ነው፡፡ ችግሩ ከረምረም ያለ ቢሆንም ሕዝቡ እንዲያውቀው ማድረጉ ተገቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነው ዲያቢሎሳዊ አገዛዝ ምንም ዓይነት ብሔራዊ አጀንዳ የሌለውና ተሠርቶ ያደረን አገር እስከነ የዕሤት ሥርዓቶቿ ንቅስ እያደረገ በማጥፋት ላይ የሚገኝ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር ለሰው ልጆች ሕይወት ዋጋ በማይሰጡ ምናምንቴዎች እጅ ከወደቀች ግማሽ ምእት ዓመት አሳለፍን፡፡ ዕብደትና ድንቊርና ሲተባበሩ ሰይጣናዊ ድፍረትን እንደሚያመጡ ምስክሩ የተቀደሰውን፣ የተከበረውን፣ አይነኬውን፣ ለሺሕ ዓመታት የተገነቡ መልካም ዕሤቶችን፣ በትውልዶች ጥረት የተቋቋሙና ብሔራዊ ምልክት የሆኑ ተቋማትን ባንድ ጀንበር ያለአንዳች መሳቀቅ የሚያፈርሱ የጥፋት ኃይሎች በዚህች በኛው ምድር መብቀላቸው ነው፡፡ 

እንኳን ከፍ ብለን የጠቀስናቸው አገር አፍራሽ ኃይሎች ምስቅልቅሏን አውጥተዋት ቀርቶ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ቢኖረን እንኳን ችግሮቻችንና ተግዳሮታችን እንደ ምድር አሸዋ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዙ ናቸው፡፡ በዓለም የገጠመን ተዋርዶአችን ሳያንስ ባገር ውስጥ የቁልቁለቱን መንገድ ከጀመርነው የግማሽ ምእት ዓመቱን ትተን በዚህ ሰባት ዓመት ጥፋቱ በብርሃን ፍጥነት ቀጥሏል፡፡ በኑሮው ውድነት የሚላስ የሚቀመስ እየጠፋ ነው፡፡ ሺሕዎች በረሃብ በጠኔ እያለቁ፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩቱ ደግሞ በሞት ደጃፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ገበሬው እንዳያርስ አገዛዙ ጦርነት ዓውጆበት ላገር የሚተርፈው ኃይል ለማኝ እየሆነ ነው፡፡ ባንዳንድ አካባቢ ጦርነቱ ሳይበግረው ደፋ ቀና ብሎ ያረሰው ገበሬ በማሳው ላይ ያለውን፣ የተሰበሰበውን እንዲሁም ወደ ጎታ የገባውን እህሉን የሚያቃጥል አረመኔ አገዛዝ ጋር እየታገለ ነው፡፡ ከብቶችንና የቤት እንስሳትን በጥይትና በከባድ መሣሪያ የሚጨፈጭፉ ጉዶችን እየታዘብን ነው፡፡ ባንፃሩም ዜጋው ከቦታ ቦታ ተቀንሳቅሶ መዋዕለ ንዋዩን ሥራ ላይ እንዳያውል እንዳይነግድ ጠንቀኛው የጐሣ ፖለቲካ እግር ከወርች ጠፍሮታል፡፡ የቀረን ዕድገትም ልማትም ያልሆነው ‹ኮሪደር› እና አርቲፊሻል ብልጭልጭ ነው፡፡ ለዛውም ያለ አንዳች ዕቅድና ዝግጅት ሕዝብን በገፍ አፈናቅሎ ሜዳ ላይ ወርውሮ፣ ባንዳንድ ቦታም በዕቅድ የተሠሩ ዘመናዊ ቤቶችንና ሕንፃዎችን (ያገር ሀብት) አፈራርሶ በቦታው ላይ ‹አበባ› በመትከል ነው፡፡

በማኅበራዊው ዘርፍ ትምህርት አፈር ድቤ በልቷል፡፡ ደናቊርት አገዛዞች ተቀዳሚ ተግባራቸው ድንቊርናን ማሠልጠን ነውና፡፡ ሕፃናቱ አፍ የፈቱበትን ቋንቋ ማንበብና መጻፍ እንዳይችሉ ተደርገው በአካልም ሆነ በአእምሮ የቀነጨረ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን ቀደም ሲል ራሱ አገዛዙ ያመነውን መሠረት አድርጌ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ የሚታጨደው የተዘራው ነውና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጣው ‹‹የተማረ ኃይል›› ባመዛኙ (ከታላቅ ይቅርታ ጋር) ‹ዕብቅ› እንዲሆን ተፈርዶበታል፡፡ በነጮቹ አባባል garbage in, garbage out እንደሚሉት ሆኗል፡፡

ሌላው የማኅበራዊው ዘርፍ ዋና ጉዳይ ጤና ነው፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም በገጠር ነዋሪ ነው፡፡ ጤናውንም የሚከታተለው በባህላዊና መንፈሳዊ ሕክምና ነው፡፡ የሚላስ የሚቀመስና ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የማያገኝ ሕዝብ በምን ዐቅሙ ነው ዘመናዊ ሕክምና ዘንድ ሒዶ አገልግሎት የሚያገኘው? መሠረታዊው የጤና የሕይወት ጉዳይ ቅንጦት ሆኖበት በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች በገፍና በግፍ እያለቀ ይገኛል፡፡ ፋሺስታዊው አገዛዝ እንዲሰደዱ ካደረጋቸው፣ ተምረው እንዲቦዝኑ ካደረጋቸው የሕክምና ባለሙያዎች አልፎ ተርፎም አገራችን የደከመችባቸውን ጥቂት ሐኪሞችን እየገደለ ይገኛል፡፡ ሰይጣናዊ አገዛዝ የፈጠረው ሁለንተናዊ ምስቅልቅል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንዳንድ የግልም ሆነ የመንግሥት የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎች ዘንድ የሚታየው ጥግ የደረሰ የሙያ ሥነ ምግባር መላሸቅ እና ጥቂት በማይባሉ የግል የሕክምና ተቋማት የሚታየው ቅጥ ያጣ ስግብግብነት/ዝርፊያ የሕይወት ማዳኑን ተግባር ሙሉ በሙሉ ተራ ንግድ ማድረጋቸውን እንድንታዘብ አድርጎናል፡፡ 

የዛሬው ርእሰ ጉዳይ ለሰው ሕክምና የሚውሉ መድኃኒቶችን ይመለከታል፡፡ ከታመኑ ምንጮች ባገኘሁት መረጃ መሠረት ባገራችን እንኳን እንደ ነቀርሳ/ካንሰር ላሉ ገዳይ በሽታዎች ቀርቶ በቀላሉ ሊድኑ ለሚችሉ በሽታዎች መድኃኒት የለም፡፡ አልፎ አልፎ የሚገኝ ከሆነም ገዝቶ መጠቀም የሚችሉት የዘረፉ ወይም በጣት ከሚቆጠሩ ሀብታሞች መካከል የሚገኙቱ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስደነግጠው ደግሞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መድኃኒቶች ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁናቴ በሕገ ወጥ መንገድ ወይም በኮንትራባንድ የሚገቡ ናቸው፡፡ በዚህም መልኩ ከሚገቡት መድኃኒቶች አብዛኞቹ የሐሰት መድኃኒቶች (falsified or substandard medicines) መሆናቸው በእጅጉ ያስደነግጣል፡፡ ሕመምተኛው በተለይም እንደ ካንሰር ያሉ በሽታዎች ተጠቂ የሆነው የማኅበረሰባችን ክፍል ቤት ንብረቱን፣ ከብቱን እህሉን ሽጦ፣ ተበድሮ ተለቅቶ ባገኘው ገንዘብ ፈውስ የማይሰጡ አልፎ ተርፎም ሌላ ጠንቅ የሚያመጡ የሐሰት መድኃኒቶችን ገዝቶ እንዲጠቀም ሲገደድ በሁለት ወገን (ከጤናውም ከገንዘቡም) ያጣ መሆኑ የግፍ ግፍ መሆኑን ማንም አንባቢ ይረዳዋል፡፡ እንኳን በየክፍለ ሀገሩ በዋና ከተማችን የሚገኙ የመድኃኒት መሸጫ መደብሮች (drug stores) ውስጥ የሚገኙ መድኃኒቶች ባመዛኙ በኮንትራባንድ የገቡ ናቸው፡፡ ስንቶቹ እውነተኛ ስንቶቹ ሐሰተኛ መሆናቸውን ፈጣሪ ይወቀው፡፡ የፌዴራሉ የመድኃኒት ቊጥጥርና አስተዳደር የሚባለው መ/ቤት ወይ የአገዛዙ ያልተጻፈ ‹ፖሊሲ› ሆኖ በትእዛዝ ሥራውን አቁሟል ወይም ከዐቅሙ በላይ ሆኖበት እንደ ተራው ሕዝብ ተመልካች የሆነ ይመስላል፡፡ በእኔ እምነት ላገር ደኅንነትና ለሕዝብ ሕይወት ደንታ የሌለው አገዛዝ ስለ ሕዝብ ጤና ቅድሚያ ሰጥቶ ይጨነቃል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው፡፡ አገዛዙና በቅርበት የሚገኙ ጥቂት ቡድኖች ከሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ ከኢትዮጵያ ውጭ ሔደው የሚታከሙበት ዕድል ስላለ ሕዝብ በበሽታ እንደ ቅጠል ቢረግፍ የሚያሳስባቸው አይደለም፡፡ በተለይም በነገድ ማንነቱ ለጥቃት ዒላማ የተዳረገው የዐምሐራ ሕዝብ ላይ ለዚህ ጥፋት ሆን ብለው ተግተው ሲሠሩ እንደቆዩና አሁንም ጥፋቱ መቀጠሉ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡

ዛሬ በተለዩ የሕክምና መስኮች ሕክምና የሚሰጥባቸው ተቋማት (referral hospitals/tertiary care centers)፣ የመንግሥትም ሆኑ የግል ሆስፒታሎች ውስጥ ዘመናዊና አስተማማኝ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የሕክምና መሣሪያዎች የሉም፡፡ አሉ የሚባሉ ጥቂቶቹም ያረጁና ጥገና የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በተለይም እንደ ነቀርሳ ላሉ በሽታዎች ትክክለኛውን ምርመራ ለማድረግም የሚረዱ ስለመሆናቸው ባለሙያዎች ይጠራጠራሉ፡፡ እነዚህ ሆስፒታሎች በመድኃኒት መደብሮቻቸውም (ፋርማሲዎች) ውስጥ መድኃኒቶች የሉም፡፡ በመሆኑም ተበድሮ ተለቅቶ ጥቂት ጥሪት የያዘው ታካሚ የሕክምና መሣሪያውንም ሆነ መድኃኒቱን (medical supplies and medicines) በራሱ እንዲያቀርብ የተገደደበት ሁናቴ ተፈጥሮአል፡፡ በልዩ ልዩ በሽታዎች ተጠቂ ከሆነው ከጠቅላላው ሕዝባችን ዐቅም ኖሮት ይህንን ሊያደርግ የሚችለው በጣት የሚቆጠር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለዛውም መድኃኒቱን የቻለ ከውጭ ያስመጣል፤ ያልቻለ ደግሞ ለመስማት ዦሮን ጭው በሚያደርግ ክፍያ የሐሰት መድኃኒቱን ይገዛል፡፡ የቀሪውና የአብዛኛው ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? መልሱን ለአንባቢው እተዋለሁ፡፡ 

ሕዝባችን ፋሺስታዊው አገዛዝ ከፈጠረበት የሰላምና ፍትሕ እጦት፣ የጦርነት፣ የሽብርተኛነት፣ ከቤት ንብረት የመፈናቀል፣ የመዋከብ፣ በኑሮ ውድነት ጨንገር የመገረፍ፣ ባጠቃላይ የአገር መፍረስ አደጋ ጎን ለጎን ታሞ ሕክምና ያለማግኘቱ፣ በሐሰተኛ መድኃኒት በጤናውና በገንዘቡ ጭምር ከፍተኛ በደል እየደረሰበት መሆኑ በቡሓ ላይ ቈረቈር ሆኖብናል፡፡

ለመሆኑ ባለፉት ሦስት አራት ዐሥርቶች የልዩ ልዩ ነቀርሳ በሽታዎች (በሁሉም የኅብረተሰባችን ክፍል) መስፋፋት ምክንያቱ ምንድን ነው? ጥናቶችና ግኝቶች ካሉ ምን ይላሉ? የአመጋገባችን ሥርዓት? ባገር ውስጥ በየስርቻው የሚመሩቱ እና ያለ ቊጥጥር ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚገቡት የምግብ ዘይቶች? በተመረዙና በተበከሉ ውኃዎች በቅለው ለሽያጭ የሚቀርቡ አታክልቶችና ፍራፍሬዎች? ገበሬዎች በግዳጅ በሚጠቀሙት የተፈጥሮ (organic) ያልሆኑ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎች ጠንቅ?  ከአፈራችንና ከአየራችን ጋር የሚስማሙ ሀገር-በቀል የእህል ዘሮች እያሉ ፈረንጆች የሚልኩልልን የተዳቀሉ ዘሮችን (genetically modified seeds) መጠቀም? በተለይም ፋሺስታዊ አገዛዞች በፈጠሩት የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት፣ በመግደል÷ በማፈናቀል÷ በሕገ ወጥ እስር÷ በማዋከብ÷ በጭካኔ ተግባራት÷ ባጠቃላይ ዕረፍት በመንሣት በሕዝብ ላይ ባስከተሉት የጭንቀት የጥበት ሕይወት ጫና ምክንያት? ዝርዝሩ መጨረሻ የለውም፡፡ በነቀርሳ ከተጠቃው ሕዝባችን መካከል ስንቱ ሕክምና ቦታ ይደርሳል? ሕክምና ቦታ ደርሶስ ስንቱ ወረፋ ሲጠብቅ ሕይወቱ ያልፋል? መረጃ እንደ ሰጡኝ የሕክምና ባለሙያዎች ምስክርነት ሕክምና ቦታ ከሚመጡ የካንሰር ሕሙማን መካከል መሣሪያና መድኃኒት ባለመኖሩ አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ወረፋ ሲጠብቁ ሕይወታቸው እንደሚያልፍ ነግረውኛል፡፡ የካንሰር በሽታዎችን ለማከም የሚውሉ መሣሪያዎችና መድኃኒቶች ባደጉም አገሮች ቢሆን በዋናነት በመንግሥት የሚቀርቡ ናቸው፡፡ እጅግም ውድ ናቸው፡፡ መድኃኒቶቹም በየትኛውም የመድኃኒት መሸጫ መደብር መደርደሪያ ላይ የማይገኙ በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ በሚገኙ ፋርማሲዎች ተይዘው በጥንቃቄ የሚከፋፈሉ ናቸው፡፡ እኛስ ጋ? ‹‹መንግሥት የለንም፡፡›› በመሆኑም እንኳን ድጎማ ሊያደርግ ዐቅሙ ካላቸው ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት በግል ሆስፒታሎች መሣሪያውና መድኃኒቱን ለማስገባት ተጠይቆ ፈቃድ ከልክሏል፡፡ ጥቂት ከአገዛዙ ጋር የሚሠሩ በዝርፊያ የበለጸጉ ዐዲስ ሀብታሞች በአገዛዙ ቡራኬ ከየዐረብ አገራቱ ‹መድኃኒቶችን› በኮንትራባንድ መልክ ያስገባሉ፡፡ ከሚገቡትም መድኃኒቶች አብዛኛዎቹ የሐሰት መድኃኒቶች (falsified or substandard medicines) እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በብድርም ሆነ በርጥባን መልክ የሚመጣው ገንዘብ ባመዛኙ ወደ ውጭ የሚሸሽ ሲሆን፣ ቀሪውም የገዛ ሕዝብን ለመጨረስ ለድሮንና ለጦር መሣሪያ ግዢ የሚውል ነው፡፡ ታዲያ ሥራ በቆመበት፣ አንዳች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሌለበት፣ በግል ጥረት ለሚያደርጉም ፈቃድ በማይሰጥበት አገር የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች አቅርቦት ከየት ይመጣል? እንዲህ ዓይነቱ በፋሺስታዊው አገዛዝ ሆን ተብሎ የሚፈጸም ዳተኝነትና የጥፋት ድርጊት በረቀቀ መልኩ ዘር ማጥፋት (systematic genocide) የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?

ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው?

ለእንደኔ ዓይነቱ ተራ ዜጋ የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም፡፡ የችግሩን ክር ስንተረትረው በዋናነት ወዴት እንደሚያደርሰን አላጣንውም፡፡ ዐቢዩ ችግር ራሱ ርጉም ‹አቢይ› መሆኑን የማያውቅ ካለ ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ተባብረን ይህንን ከሰው በታች ያዋረደንን ቆሻሻ ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ እስከነ ኮተቱ ማስወገድ ነው፡፡ ሊቃውንቱ ‹ለይሁዳ ወልዱ ወውሉዱ ወልዱ (ወያኔ፣ ብአዴን፣ ኦነግ/ኦሕዴድ እና ጭፍሮቻቸው) ይደምሰስ› / የይሁዳ ልጁ እስከ ልጅ ልጁ ይደምሰስ/ እንደሚሉት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው በውጩ ዓለም ተበትናችሁ በስደት የምትገኙ፣ በላቀ ደረጃ የሕክምና ልዩ ዕውቀት ያላችሁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ይህንን ምስኪን ሕዝባችሁን ብቅ እያላችሁ በምትችሉት ዐቅም እንድትታደጉት ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ፡፡

መልእክት ለዐምሐራ ፋኖ፤  የህልውና ትግል በሚደረግባቸው በአራቱም የዐምሐራ ክፍላተ ሀገራት የምትገኙ የፋኖ ወንድሞችና እኅቶች (አሁንም ደግሜ ደጋግሜ አሳስባለሁ) ለትግሉ እንቅፋት በመሆን የሕዝባችንን ሰቈቃ የሚያራዝሙትን የብአዴን ሰርጎ ገቦችን ከውስጣችሁ አጥሩ/ለዩ፡፡ ብአዴን የሚበርስበት መድኃኒት የለውም፡፡ በብዙ መሥዋዕትነት የመሠረታችሁትን ‹የዐምሐራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት/ዐፋሕድ/› የጎደለውን እየሞላችሁ እንደ ዓይናችሁ ብሌን ጠብቁ፡፡ እውነተኛ መሪዎቻችሁንም ተከባከቡ፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ ‹መለየትን የሚወድ ምኞቱን ይከተላል› እንዳለ ተመክሮ ተዘክሮ ተገሥፆ እምቢኝ አሻፈረኝ ያለው ከህልውና ትግሉ ከፍም ሲል ከኢትዮጵያ አንድነት በላይ አይደለምና በጊዜ መለየቱ የግድ የሚልበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል፡፡ ማስታመሙ ብሎም የርስ በርስ ግጭቱ መከረኛ ሕዝባችንን በእጅጉ የሚጎዳ ደምና አጥንት የተከፈለለትን የህልውናና የአገር አንድነት ትግል ከንቱ የሚያደርግ፣ ብሎም በጠላትነት ለሚገዳደረን ፋሺስታዊ አገዛዝና ከርሣም ተከታዮቹ ሲሳይ መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት የለብንም፡፡

Filed in: Amharic