>
5:42 pm - Tuesday March 21, 9871

ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የተሠጠ አስቸኳይ መግለጫ

ታላቁ አርበኛ ኮሎኔል ታደሠ እሸቱ እና ጓዶቻቸው የከፈሉት የሕይወት መስዋዕትነት ትግላችንን ይበልጥ ያጠናክረዋል

 

የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ቁልፍ የትግል ግንባር በሆነው ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ደቡባዊው የግዛቱ ክፍል ተከታታይ ውጊያዎችን አቅዶ በመምራት፣ በማደራጀት፣ ውጊያን በማቀናጀት ድል በመምራት የሚታወቁት ታላቁ የጦር አባት ኮሎኔል ታደሰ እሸቴ ከአጃቢዎቻው ጋር ሆነው ውጊያ ከሚመሩበት ቀጠና ከአገዛዙ ጠላት ሰራዊት ጋር ተፋልመው በጀግንነት ተሰውተዋል፡፡

በአገዛዙ ሠራዊት ውስጥ አሁንም ድረስ ያሉ ጓደኞቻቸው በጥቅም ተገዝተው ህዝባቸውን ሲጨፈጭፉ፣ ጀግናው ኮ/ል “በጥቅም አልገዛም፣ ህዝቤንም አልከዳም” ብለው ለእውነትና ለነፃነት እንደ አባቶቻቸው የመጨረሻውን የክብር ዋጋ ከፍለዋል። የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ አስተዳደር እና የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ዕቅድና ስትራቴጂ ክፍል መምሪያ ኃላፊ በመሆን የህልውና ትግሉን ታግሎ በማታገል የፊትአውራሪነት ቦታውን የያዙት ኮሎኔል ታደሰ እሸቴ፣ በላይ ጋይንት ወረዳ ዛጎች ቀጠና በተካሄደው ከባድ ፍልሚያ በርካታ የጠላት ሰራዊት አጋድመው፤ ከእነ አጃቢዎቻቸው በክብር የተሰውት ዛሬ ማለዳ የካቲት 22/2017 ዓ.ም ነው።

ኮሎኔል ታደሰ እሸቴ በውትድርና ሙያቸው አንቱ የተባሉ፣ በተለይም የውጊያ ስልጠና፣ ኢንዶክትሪኔሽን፣ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይል ስምሪት፣ ሎጀስቲክስ፣ቅኝት፣ ተልዕኮ፣ ግዳጅ አፈጻጸም፣ ወታደራዊ ግምገማ፣ መልሶ ማደራጀት፣ የጦር ምህንድስና፣ የግንባር ውጊያ፣ የአንገት ቦታ ቁጥጥር፣ ገዥ መሬትን ቀድሞ መያዝ፣ ምሽግ ሰበራ በልዩ ሁኔታ የተካኑባቸው ወታደራዊ የሕይወት ገጻቸው ስለመሆኑ አብረዋቸው የታገሉ የትግል ጓዶቻው ብቻ ሳይሆኑ ጠላትም ጭምር የሚመሰክርላቸው ነበሩ።

ታላቁ የጦር ሰው በዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋዜማ ለአማራነት ክብር፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ አንድነት በክብር ተሰውተዋል፡፡

የጋይንቱ አንበሳ፤ የጎንደሩ የጦር አባት፤ የአማራው መከታ ፣ኢትዮጰያ አለኝታው እና የህልውና ትግሉ የክብር ዘብ ኮሎኔል ታደሰ እሸቴን በትግሉ ውስጥ የነበራቸው የፊትአውራሪነት ሚና ሁሌም በወርቅ ተፅፎ የሚኖር ታሪክ ነው።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ኮ/ል ታደሰ እሸቴ ለተሰውሉት የተከበረ ዓላማ ያለውን ቁርጠኝነት በዚህ አጋጣሚ እየገለፅ፣ መላ ሠራዊታችን፣ ደጋፊዎቻችንን እና ህዝባችን በተከታታይ ለምናስተላልፋቸው መመሪያዎች እና ትዕዛዝ በተጠንቀቅ እንዲጠብቀን እናሳስባለን።

ክብር ለሰማዕቶቻችን!

ድል ለአማራ ፋኖ እና ድርጅቱ አፋህድ! 

 

Filed in: Amharic