ጨለማ ከብርሃን ጋር ምን ኅብረት አለው
ከይኄይስ እውነቱ
በፖለቲካው ዓለም ያጭር ጊዜን ዓላማ ለማሳካት የሚደረግ ዘዴና ተግባር (ታክቲክ) ወይም የረዥም ጊዜን ግብ ለማሳካት የሚደረግ አጠቃላይ ዕቅድና ስልት (ስትራቴጂ) መሠረት አድርጎ አንዳንዴ ጠላት ከሚባል ኃይልም ጋር ‹ስልታዊ ኅብረት› ሲፈጸም ይስተዋላል፡፡ ይህ ሁናቴ በቆሸሸው የኢትዮጵያ የ‹ፖለቲካ› መልክዐ ምድር ይሠራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምንም እንኳን የፓርቲ (ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ) ፖለቲካ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ከተንኮል፣ ከሸፍጥ፣ ከመጠላለፍ፣ ከሴራና ዐድማ የነፃ ባይሆንም መሠረታዊ የዕውቀት ሀ ሁ እና መርህና ፍልስምናም አለው፡፡
ካንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የዐምሐራ ሕዝብ የህልውናና የአገር አንድነትን የማስከበር ትግል ውስጥ ይህንን ዓይነቱን አጕል ኅብረት የሚያቀነቅኑ የትግል ሚዲያዎች እንዳሉም አድምጬአለሁ፡፡ ብርቱ ጉዳዩ በመሆኑ አገርን ከሚወዱ ከጦርም ሆነ የፖለቲካ ጠበብቶች ጋር በእጅጉ መምከር የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ የተለያየ አቋምም ይዛችሁ ሕዝቡን አታደናግሩት፡፡ ፋኖዎችን በዚህ ረገድ ማገዝ ተገቢም ይመስለኛል፡፡ ባደባባይ ባይቻል በውስጥም አድርጉት፡፡ በተጨማሪም የትግል ሚዲያዎች በምታቀርቡት ጉዳይ ላይ ከርእሱ ጀምሮ ጥንቃቄ ብታደርጉ መልካም ነው፡፡ ለሕዝብ ተስፋ የሚሰጥ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አድርጋችሁ ባታቀርቡ፡፡ መርሐ ግብርሐችሁ ሁሌም ፋሺስታዊው አገዛዝ በሚሰጠው አጀንዳ ዙሪያ ለምን ያጠነጥናል? እምነት በእጅጉ የተሸረሸረበት ጊዜ ላይ የምንገኝ ቢሆንም መርሐ ግብራችሁን የአንድ ሰው ትርኢት አታድርጉት፡፡ በዚህ ረገድ ‹ኢትዮ 360› የደረሰባችሁን ክህደት በሚገባ እረዳዋለሁ፡፡ ቀድሞ÷ ሁሉን የሚያውቅ በሚመስለውና አቋሙን ከርሡ ባደረገ በወያኔ ካድሬው፣ ኋላም ሥሪቱ ብአዴናዊ በሚመስለውና የፖለቲካ ዕውቀት ጦመኛ በሆነው ‹ዜና አንባቢ›፡፡ እያልኹ ያለሁት ባልደረባ የሆኑ ተንታኞችን ጨምሩ ሳይሆን፣ አገራችንን የሚወዱ ሊቃውንት ሞልተዋልና እነሱን አቅርቡ ጋብዙአቸው እናንተ ብቻ ተናጋሪ አትሁኑ፡፡ በውስጥ የምታደርጉት ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁል ጊዜ ችግር የማይፈታ ‹ምስጢር› የሚባለውን እያጋለጣችሁና እየነገራችሁ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ይህም አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ትግሉን በማፋጠን ወንድሞቻችን በፖለቲካውም ሆነ በወታደራዊው መስከ ወጥነት እና ማዕከላዊነት ያለው አደረጃጀት ይዘው በመንቀሳቀስ ትግሉን በማሳጠር ረገድ እሤት የሚጨምሩ መርሐ ግብሮች ላይ ትኩረት ስጡ ለማለት ነው፡፡
ኅብረት ከማን ጋር? ከየትም አምጪው ዶቄቱን ፍጪው ፖለቲካ የኋላ ኋላ ከበድ ያለ ክፍያን ያስከትላል፡፡ ያልታሰበ ውጤትም ሊያመጣ ይችላል፡፡ ፋሺስታዊው የርጕም ‹አቢይ› አገዛዝ መወገድ አለበት ወይ? ሊጠየቅም አይገባም፡፡ እያንዳንዱ ቀን በአገርና በሕዝብ ላይ የጥፋት በመሆኑ እንደ ሕዝብ በእጅጉ ዘግይተናል፤ ተጠያቂም ነን፡፡ እንዴት የሚለው ግን ዓይናችንን ጨፍነን የምንገባበት ጉዳይ አይደለም፡፡
ፋሺስታዊውን አገዛዝ ለመጣል ‹ኅብረት› ቢደረግ እየተባለ የሚወራው እንደ ዓላማ እንደ ድርጅት የሞተ፣ የትግራይን ሕዝብ መቀመቅ የከተተና አሁን መያዣ አድርጎ የሚንቀሳቀስ፣ በምዕራቦቹ እርዳታና ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፈው ሀብትና የጦር መሣሪያ አልሞትኹም አለሁ ከሚለው ከወያኔ ሕወሓት ጋር ነው፡፡ አዎ ይሄ የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነ አሸባሪ ድርጅት ለጥፋት አያንስም፡፡ መዘንጋት የሌለብን ግን የጐሣ ሥርዓቱን በሕግ በመዋቅር ዘርግቶ ለኢትዮጵያ ጥፋት ለሕዝብ እልቂት ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሆነ የወንበዴዎች ስብስብ ነው፡፡ ይሄ ስብስብ ህልውናው አደጋ ላይ የሚገኘውን የዐምሐራ ሕዝብና ኢትዮጵያን ለመታደግ ከሚታገሉ ኃይሎች ይልቅ በዓላማም በፍላጎትም የሚቀርበው ወልዶ ላሳደገው የኦሕዴድ/‹ብልግና› እና ለባርያው ብአዴን ቡድኖች ነው፡፡ በነዚህ ኢትዮጵያ ጠል ቡድኖች መካከል ያለው ዋና ልዩነት ሥልጣንና በዚሁ የሚገኘው ዝርፊያ ነው፡፡ በመሆኑም ዋስትና በሌለው ግንኙነት፣ ምንም ዓይነት የታማኝነት የኋላ ታሪክ ከሌለው (no track record of honesty and trust) ወንበዴ ቡድን ጋር ‹ኅብረት› እንፍጠር የሚለው ሐሳብ አያስኬድም ብቻ ሳይሆን መሞከርም የለበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እንደሚለው ጨለማ ከብርሃን ጋር አንዳች ኅብረት የለውምና፡፡ አንዳንድ ወገኖች ይህ ዓይነቱ አመለካከት ለፋሺስታዊው የብልግና አገዛዝ እፎይታን የሚሰጠው አድርገው ያስባሉ፡፡ ጉዳዩን ገልብጠን ብናየው ይኸው ኃይል ራሱን ለማትረፍና ጥቅሞቹን አስልቶ በዓላማ ከሚመስለው ከኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዝ ጋር አይሰለፍም ማለትም አይቻልም፡፡
ይህ ዓይነቱ ከአጋንንታዊ ኃይል ጋር የሚደረግ ኅብረት ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅምና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በጥንቃቄ አመዛዝኖ፣ ከጭፍንና ከስሜት የጸዳ አመክኖዮአዊ ትንተናን መሠረት አድርጎ የሚደረግ ውሳኔ (calculated risk) የሚፈለገውን ውጤት ያስገኛል ወይ ብለን ብንጠይቅ አዎንታዊ መልስ ለማግኘት ይቸግራል፡፡ ‹ዕድሉን› ብንሞክረው በአጸፌታው ሊያስገኝ የሚችለው ጥቅምና ውጤት ልናጣ ከምንችለው ጥቅምና ውጤት በእጅጉ በልጦ የሚገኝ ነው ወይ (a risk worth taking) ብለን ብናሰላ ከዚህ ቆሻሻ ቡድን መሠረታዊ ጠባይ አንፃር የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አገርን ከዘረኛ ፋሺስቶች እጅ ነፃ በማውጣት ሒደት የማይቀለበስ ታሪካዊ ስሕተት እንዳይፈጸም ለሚመለከታቸው ሁሉ ማሳሰብ ነው፡፡ በተለይም የዐምሐራን ሕዝብ ህልውና እና የኢትዮጵያን አንድነት ለመታደግ ተገዶ ወደ ትጥቅ ትግል የገባው የዐምሐራ ፋኖ ፋሺስታዊውን የርጕም ‹አቢይ› አገዛዝ በራሱ ማስወገድ ዐቅሙም ብቃቱም አለው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የጎደለው ወጥነት ያለው ድርጅታዊ (የፖለቲካ/ወታደራዊ) አመራርና በማዕከል ደረጃ የሚሰጡ ውሳኔዎች በአራቱም ክፍለ ሀገራት ተከብረው እንዲፈጸሙ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ እንቅፋት የሚሆን ማናቸውም ኃይል ሁሉ የዐምሐራ ሕዝብ ብሎም የኢትዮጵያ አንድነት ፀር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ደጋግሜ እንደምለው የአገር ብሎም የዓለሙ ማፈሪያ የሆነውን ብአዴን የተባለ ነውረኛ ቡድን ከነ መዋቅሩ ያለ ርኅራኄ ለማጥፋት ቊርጠኝነት የጎደለው የዐምሐራ ፋኖ አርበኛም ሆነ አመራር ካለ እስካሁን በደምና ባጥንት የተፈጸመውን መሥዋዕትነት ከንቱ እንደሚያደርግ በቅጡ ሊረዳ ይገባል፡፡
በውስጥም በውጭም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ወሬ ማራገቡንና መከፋፈሉን አቁመን ጀግኖቻችንን በሚቻለው ሁሉ እናግዛቸው፡፡ ዐዲስ አበባን ጨምሮ ትግሉ በሚካሔድባቸው የአራቱ ክፍለ ሀገራት ዋና ከተሞች ውጤታማ ወታደራዊ ኦፐሬሽኖች መደረግ አለባቸው የሚሉ በርካታ ድምፆች ይሰማሉ፡፡ ጉዳዩን ለወታደራዊ ጠበብቱ በመተው አስፈላጊነቱ ለእኔም እንደ አንድ ዜጋ ይታየኛል፡፡ እንደ ሕዝብም ሁላችንም ድርሻ እንዳለን ዐውቃለሁ፡፡ ከፋኖዎቻችን ጋር የተቀናጀ ቢሆን ውጤታማ ይሆናል፡፡ እባካችሁ ውድ ጊዜአችንን በዕንካ ስላንትያ አናጥፋ፡፡ የአገዛዙ ‹ውሾች› ያላዝኑ፡፡ የነገር ‹አጥንት› በሰጡን ቊጥር እንደ ‹ጉንዳን› በዙሪያው አንሰባሰብ፡፡ እነሱን ትቶ ዓላማን እየተመለከቱ መጓዝ ነው ወደሚፈለገው ግብ የሚያደርስ፡፡
ምንም እንኳን አገራችን የምትገኝበት ሁናቴ ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ቢገኝም፣ ፋሺስታዊውን አገዛዝ ማስወገድ ይዋል ይደር የማይባል ጉዳይ መሆኑን ብንረዳም፣ እውን ከለየለት ወንጀለኛ – ኢትዮጵያን ‹ካፈረሰ›ና ለአረመኔ አፍራሾች አሳልፎ ከሰጠ – ቡድን ጋር ኅብረት ያስፈልገናል?