ወልቃይት እንደ ቀይ ባሕር
ፋኖ አርበኛ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው
አንቀፅ 39 ሚናውን እየተወጣ ይመስላል። ወያኔ የትግራይ ሪፐብሊክን ሊያውጅ ተፍ ተፍ እያለ ነው። የአዋጁን ነጋሪት ለመጎሰም የሚጠበቀው የወልቃይት ዶሴ ነው። ወልቃይትን በኃይል ወደ ትግራይ እንደ ሸገለለ የራሱን ሽራፊ ሀገር ያውጃል። ያለ ወልቃይት የትግራይ ሪፐብሊክን ማወጅ ደግሞ ታላቅ ዋርካ ላይ ራስን በገመድ አንቆ እና አንጠልጥሎ እንደ መግደል ይቆጠራል። መርከበኛ በሌለበት ውቅያኖስ ውስጥ ሰጥሞ በትንፋሽ እጥረት እንደመሞት ይሆናል። ለመሆኑ ይህ ምን ማለት ነው? ወልቃይት ለምናባዊቷ፣ ለመጭዋ የትግራይ ሪፐብሊክ ምኗ ነው?
ምንም እንኳን መሬቱ በታሪክም ሆነ በሕግ (የተወሰደው ከሕገ መንግስቱ መረቀቅ በፊት መሆኑን ልብ ይሏል) የአማራ አፅመ ርስት ቢሆንም ፣ በስነ ልቦና፣ በባህል፣ በትውፊትም ሆነ በቋንቋ የአማራ ቢሆንም ወያኔ ይህንን በኃይል ካልወረረ አዲሷን ሀገር እንደ ማይመሰርት ያውቀዋል። ወልቃይት ለትግራይ ከወያኔ የ50 አመታት ወዳጅ ሱዳን ጋር የመደናበሪያ ደረቅ ወደብ ነው። በጠላትነት የፈረጀውን የአማራን ሕዝብ እና በስጋትነት የፈረጀውን የኤርትራን ሕዝብ መነጣጠያ ግድግዳው ነው። በነገራችን ላይ ሰሞኑን ከኤርትራ ጋር የጀመረው ወዳጅነት ስልታዊ እንጂ ስትራቴጂያዊ ሊሆን አይችልም። ጊዜያዊ እንጂ ረዥም አይሆንም። ከ500 አመታት በፊት ሐርጌዎች በእነ ኑር ሙጃሂድ እየተመሩ ከገዳ ወረራ ይጠብቀናል ያሉትን የጀጎል ግንብ እንዳነፁት ሁሉ ወያኔ ወልቃይት ላይ አማራ እና ኤርትራን የሚለያይ ግንብን መገንባት ይፈልጋል።
ከአፄ ዮሀንስ ፬ኛ ገዳዮች፣ ከግብፅ ወኪል ወጊዎቻችን ከሱዳኖች ጋር ደግሞ የቆየ ወዳጅነት አለው። በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል ዘመን ሱዳን ደርግን ብቻ ሳይሆን ኢሕአፓ-ንም ለመደምሰስ አግዛዋለች። ሱዳን በተለይም የኢሕአፓ ወዳጅ መስላ ከጀርባ አፍና በማስወጋት በመተማ፣ በቋራ፣ በአለፋ፣ በአቸፈር ወንድዬ እና በመተከል ግንባሮች ብዙ ረድታዋለች። ለዚህ ወሮታዋም ወያኔ በአባይ ጸሀዬ ፈራሚነት፣ በደመቀ መኮንን አስፈፃሚነት የመተማን መሬት ቀንድሎ መስጠቱ የቅርብ ታሪክ ነው። የወያኔ እና የሱዳን ወዳጅነት በጀኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን ዘመንም ቀጥሏል። የወያኔ ወታደሮች አልቡርሀንን አግዘው የፈጥኖ ደራሽ ሰራዊቱን በመውጋት በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እየተሳተፉ ነው። እዚህ ላይ ሉዓላዊነታችንን ጥሳ ኤርትራ ወጋችን የሚለው ዋይታ የሞራል እና የሚዛናዊነት ጥያቄን ያጭራል።
አፍሪካውያን በእነ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ ቀስቃሽነት፣ በእነ ኢብራሒም ትራዖሬ መሪነት በሀገራቸው የሚገኙ የአውሮፓ የጦር ሰፈሮችን እያፈረሱ ባለበት በዚህ ዘመን ሱዳን ለወያኔ የጦር መሰረት ፈቅዳለች። በሁለት አመቱ ጦርነት በጭና እና በማይካድራ ንፁሃን አማሮችን በነሲብ የጨፈጨፈው ሳምሪ የተባለው የወያኔ ሰራዊት በዚያው ሰፍሯል። በሱዳን ጦርነት የሚዋጋውም ይኸው ነው።
የዚህ ሰራዊት አላማ በሱዳን እየታገዘ አማራን ከጀርባ በመውጋት ከበባ ውስጥ ማስገባትና ወልቃይትን መንጠቅ ነው። በለስ ቀንቶት ሊወጉት ሲገባቸው ለዚህ አላማው የሚያግዙት የፋኖ አደረጃጀቶችም አግኝቷል። ይህን ጉዳይ ዝቅ ብሎ እናፍታታዋለን። እስከዚያው ግን አዲሷ ሽራፊ ሀገር ወልቃይትን የምትሻባቸውን ምክንያቶች እንጥቀስ።
በጥቅሉ ወልቃይት ለትግራይ ሪፐብሊክ የምታስፈልግባቸው የሚከተሉት ምክንያቶች ናቸው:-
• ከሱዳን ጋር ለመደናበር
• ከኤርትራ ጋር ያለውን የድንበር ግንኙነት ለማስፋት
• የኤርትራ እና የአማራን (ኢትዮዽያ) የድንበር ግንኙነት ለመነጠል
• የሱዳን እና የአማራን (ኢትዮዽያ) የድንበር ግንኙነት ለመነጠል
• አማራን በኦነግ እና ወያኔ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት
• አሶሳ የሚገኘውን የአባይ ግድብ የአዲሷ የትግራይ ሪፐብሊክ አካል ለማድረግ
• ለም የእርሻ መሬት ለማግኘት
ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ከአማራው ተነጥቀው ለትግሬ የሚሰጡ ጥቅሞች ናቸው። እነዚህ ሳይኖሯት የትግራይ ሪፐብሊክ ብትመሰረት በአማራ፣ በኤርትራ እና በአፋር ከበባ ውስጥ የታጠረች ሀገር ትሆናለች። ይህ አዲሷ ሀገር ነገ ለምታነሳው የድንበር፣ የባህል፣ የሀይማኖት፣ የታሪክ . . . ጦርነት ከወዲሁ ተሸናፊ ያደርጋታል። በሸቀጣሸቀጥ፣ በግብርና ምርቶች እና በቤንዚን ችጋር ትታፈናለች። ለዚህም ነው ወልቃይትን አልቦ የትግራይ ሪፐብሊክን ማወጅ ራንስ እንደማጥፋት የሚቆጠረው።
የትግራይ ሪፐብሊክ ብቻውን የሚመጣ አይደለም። ከእርሱ ትይዩ የኦሮሚያ ሪፐብሊክም እየተሰራበት ነው። ለዚህም አስቀድሞ የተዘጋጁ ሁለት ካርታዎች አሉ።
ሁለቱ አደገኛ ካርታዎች
አንደኛው ወያኔ ያዘጋጀው የትግራይ ሪፐብሊክ ካርታ ነው። በዚህ ካርታ መሰረት አዲሷ ሀገረ ትግራይ ወልቃይትን ብቻ አይደለም ከአማራው ነጥቃ የምትወስደው። ግዛቷ ተከዜን ተሻግሮ በወልቃይት፣ ሁመራ፣ ቋራ፣ አለፋ፣ ጣቁሳ፣ ከፊል የአቸፈር ወንድዬ እና መተከል ቀጣናዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው። ይህም ሁለት ስትራቴጂያዊ አላማዎች አሉት:- የመጀመሪያው አማራ ከሱዳን ጋር የሚገናኝበትን ድንበር ሙሉ በሙሉ መቁረጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አሶሳ ድረስ ዘልቆ የአባይ ግድብን ወደ አዲሷ የትግራይ ሪፐብሊክ ለማካከል ነው። ግዛት ማስፋፋት እና ለም መሬትን መጨመር ብሎም አማራን ማዳከምና በአማራ ድክመት ላይ የራስን ጥንካሬ መገንባት ከሁለቱ ቀጥሎ ሊጠቀሱ የሚችሉ አላማዎቹ ናቸው። ይህም ኤርትራ ከኢትዮዽያ ስትነጠል በስልት ወሽመጥ እየተሠራ ኢትዮዽያ በአስር ኪሎ ሜትሮች ርቀት ከቀይ ባሕር እንድትነጠል የተደረገበትን ታሪክ ያስታውሰናል። ለዚህም ነው ወልቃይት የአማራ ቀይ ባሕር ነው የምንለው።
ሁለተኛው አደገኛ ካርታ ኦነግ ያዘጋጀው የኦሮሚያ ሪፐብሊክ ካርታ ነው። ካርታው የብልፅግና ሙሉ ድጋፍ አለው። በዚህ ካርታ መሰረት አዲስ አበባ ብቻ አይደለቺም ከአማራው ተነጥቃ ለኦሮሚያ የምትሰጠው። ደራን በመጨመርም አይበቃውም። አዲሷ ኦሮሚያ አዲስ አበባ እና ደራን ቁርሷ፣ ሙሉ ሸዋን ምሳዋ፣ ድፍን ወሎ-ቤተ አማራን ራቷ በማድረግ እስከ ራያ ድረስ የምትዘልቅ ነች። በዚህም የትግራይ ሪፐብሊክ እና የኦሮሚያ ሪፐብሊክ ራያ-አንጎት ላይ ተገናኝተው ይደናበራሉ። በሌላኛው ጠርዝ መተከል ላይ ተገናኝተው ይደናበራሉ። ሁለቱ አዳዲስ ሀገሮች አማራን በብቸኝነት በራሳቸው ከበባ ውስጥ ያስገባሉ። የኦሮሞ እና የትግራይ ሕዝብ ድፍርስ ውሃ ቢደርቅበትም ወያኔ እና ኦነጋውያን (ብልፅግናን ጨምሮ) ወይን ይራጫሉ። ለወይኑ ማወራረጃ ይሆን ዘንድ አዲሷ ሀገረ ኦሮሚያ የቻለቺውን ያህል ከጎጃም ቆርሳ ትወስዳለች። በተይም መተከል እና ሽንዲ ወንበርማ መቁረሻ ካራው ቀድሞ የሚዳስሳቸው የጎጃም ቀጣናዎች ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ በጎጃም እና በጎንደር ጠባብ ስፍራዎች ታጥሮ የሚቀረው አማራ አሽክላ ውስጥ የገባች ሚዳቋ ይሆናል። የሞት ፍርድ እስረኛ እንደማለት ነው። ካራ ተስሎ የሚጠብቀው ይሆናል። ከዚህ መዓት አምልጦ የሚተርፍ አማራ ቢኖር ከዳዊት ቬንጎሪዮን በፊት እንደ ነበሩት እስራኤላውያን የእግሩ መርገጫ አንድ ብርኩማ መሬት የሌለው በዓለም ዙሪያ የተበተነ፣ የተጠላ፣ የተናቀ ይሆናል። አማራን በማጥፋቱ በኩል እነ ደብረ ጽዮን እና እነ አብይ አብይ አሕመድ ያለአንዳች ልዩነት ይቀጥሉበታል። ምናልባት የሚያጋጫቸው አጀንዳ ካለ የአባይ ግድብ ይገባኛል ጉዳይ ይሆናል።
ይህ የሁለቱ ጸረ አማሮች ትብብር ለጊዜ ይፋ ላይሆን ይችላል። አማራው በበቂ ደረጃ ሲደክምና ሁለቱን አዳዲስ ሀገራ ለማወጅ ሲቃረቡ ነገሩን ጸሐይ ይሞቀዋል። እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ የትኛውም ፋኖ ለወያኔ አስፈላጊ አይሆንም። እስከዚያው ግን ‘አማራ አንድ የፋኖ አደረጃጀት ነው ሊኖረው የሚገባ። ሌላውን ደምስሱ። እናግዛችኋለን’ በማለት ለወያኔ ፍላጎት የማይገዙ ፋኖዎች ሁሉ ይደመሰሳሉ። በዚህም ጉዳዩን ከ1970ዎቹ ፖለቲካ ጋር ስናገናዝበው ሰሞኑን የተመሰረተው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል እንደ ኢሕዴን፣ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት እንደ ኢሕአፓ፣ ወያኔ እንደ ወያኔ፣ ብልፅግና እንደ ደርግ ይሆናሉ። ልዩነቱ ብልፅግና ከሀገር ከመኮብለል ይልቅ አዲስ ሀገር መስራች ሆኖ እንደገና መምጣቱ፣ ወያኔም አራት ኪሎ ከመግባት ይልቅ አዲስ ሀገር አዋልዶ መቀሌ ላይ መንገሡ ነው። ይህን ሂደት ለማስቀጠል ሱዳን የሰፈረው የወያኔ ጦር በቅድሚያ በወታደራዊ እገዛ ሰበብ አባይን ተሻግሮ ወደ መሀል አማራ ይገባል። በጦርነቱ ማለቂያም ‘የተሰው ጓዶቻችን እዚህ ተቀብረዋል። መስዋዕትነት ከፍለናል። ሱዳን የሰጠንን የጦር ሰፈር የተዋጋንለት አማራ እንዴት ይነፍገናል’ በሚል ሰራዊቱ ከሱዳን አስፍቶ እስከ መሀል የአማራ መስተዳድር ይሰፍራል። ወረራው እየተስፋፋ ካርታዎቹን ገቢራዊ ያደርጋል።
እነኝህ ሁለቱን አደገኛ ካርታዎች ከወረቀት ላይ አውርዶ መሬት ላይ ለማስመር አዲስ አበባን እና መቀሌን ማዕከላቸው ያደረጉ ሁለት አገዛዞች ሱዳን እና ወለጋ-ቢዛሞ ከሚገኙ ቅጥያዎቻቸው ጋር ሥራቸውን ይቀጥላሉ። አማራ ተከቧል። እንዴት ሰብሮ ይውጣ?
የአማራው የመከላከል ርምጃ
በቅርቡ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይልን (አፋብኃ) የመሰረቱ የፋኖ አደረጃጀቶች ከወያኔ ጋር በቅንጅት እንደ ሚታገሉ አስታውቀዋል። በአርበኛ አስረስ ማረ እና በጀኔራል ተፈራ ማሞ አንደበት በተለያየ ጊዜ ይፋ ያደረጉት የወያኔ ሽርክና ሱዳን እየተገናኙ እስከ መምከር ተደርሷል። ከዚህም ባለፈ ከአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ጋር በሚያደርጓቸው የጎንዮሽ ውጊያዎች በአንድ ግንባር እስከ መሰለፍ ተደርሷል። በጎንደር አርበኛ ከፍያለው ደሴ መስዋዕት በሆነበት የጎንዮሽ ውጊያ ከሱዳን ተነስተው የመጡ የሳምሪ ጦር አባላት ከብሔራዊ ኃይሉ ጎን ተሰልፈው መሳተፋቸው እሙን ነው። አፋብኃ-ን የመሰረቱ አደረጃጀቶች ወደ ኤርትራ ተሻግረው በሚሄዱበት ጊዜ ሱዳንን አቋርጠው ሲሄዱ አጅቦ የሚሸኛቸውም ሆነ የሚመልሳቸው በጀኔራል ሙዑዘይ የሚመራው የወያኔ ሳምሪ ጦር ነው። ተቋሙ በተመሰረተበት ጊዜም መስራች ጉባኤው የተደረገው በዚሁ በሱዳን ነው። በርግጥ መስራቾቹ በመግለጫ የነገሩን ቋራ ላይ የመሰረቱት መሆኑን ነው። ሆኖም ይህ ውሃ የሚያነሳ አይደለም። የታሪክ ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል የተነገረ ውሸት ነው። ሐቁ ሱዳን ጊዝራ ከተማ ውስጥ የራሳቸውን ሰራዊት 200 ኪሎ ሜትር ያህል አርቀው እና በሳምሪ ቡድን ታጅበው ለሳምንታት የተሰበሰቡ መሆኑ ነው። እንደተባለው ቋራ ቢደረግ ኖሮ እና የወያኔዎችም ቀጥተኛ ተሳትፎ ያልበረበት ቢሆን ኖሮ ከቋራ ይልቅ ለአራቱም የአማራ ጠቅላይ ግዛቶች አማካኝ የሆነ ስፍራ መምረጡ የግድ ነበር። ለምሳሌ ወደ ሱዳን ከመዝለቁ በፊት የራያው ዋርካው ምሬ ወዳጆ ከእነ አርበኛ ዘመነ ካሤ ጋር ጎጃም ሶማ በረኻ ነበር። ሶማ ለአጅሬ ጃኖራው አርበኛ ሐብቴ ወልዴም ለመንዙ አርበኛ ደሳለኝ ሲያስብ ሸዋ አማካኝ በረሃ ነበር። የአብይ አሕመድ ወራሪ አገዛዝ ጥቃት እንዳይሰነዝር ከታሰበም ሶማ ለአድፋጭ መሸሸጊያነቱ አመቺ ነው። ከታሪካዊነቱ አንፃርም ከታሰበ የአባ ኮስትር በላይ ዘለቀ ምሽግ ሶማ ከመይሣው ካሳ ምሽግ ከቋራ የሚያንስ አልነበረም። ከድካም አንፃር ከታሰበ ቋራ የሚቀርበው ለሐብቴ ብቻ እንጂ ለሦስቱ አርበኞች ሩቅ ነው። ይህ ከድካም፣ ከስንቅና ሎጀስቲክ እንዲሁም መንገዱ በረዘመ ቁጥር ከሚመጣው የደኅንነት ስጋት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ቁጠባ አንፃርም ሊታሰብ ይችላል። በመሆኑም እነኝህ ሁሉ ሲደማመሩ ስብሰባው ቋራ ሳይሆን ሱዳን መደረጉን ያመላክቱናል። ቋራ ተደርጓል ብለን ብናስብ እንኳን ቦታው የተመረጠው ለወያኔው ሳምሪ ቀረቤታ ስላለው ነው ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ የፋኖ አደረጃጀቶቹ ከወያኔ ጋር እንደሚሰሩ ካወጁ በኋላ የተነሳባቸው ሕዝባዊና ሰራዊታዊ ተቃውሞ ስላስደነገጣቸው የወያኔ ሽርክናቸውን ለመደበቅ ያደረጉት ነው። ጋብቻ ካወጁ በኋላ ከአጥንተ ሰባራ እንደማይጋቡ ሲነገራቸው ወደ እቁባትነት ቀይረውታል። እየሆነ ያለው ይኸው ነው።
በመሆኑም አማራ ማድረግ ያለበት በቅድሚያ ከወያኔ ጋር የሚሠሩ ፋኖዎችን መግራት ነው። ‘ተመለሱ፣ ጠላት እና አጋራችሁን ለዩ። የአዲስ አበባውም ሆነ የመቀሌው አገዛዝ ጠላቶቻን ናቸው’ ማለት አለበት። ከወያኔ ጋር የሚደረግ ሽርክና በሕዝባዊ ተቃውሞ መቆም አለበት። በብዙሃኑ ሰራዊት ተቃውሞ መቀልበስ አለበት። በዚህ ጦርነት የጠላት ልየታ ብዥታ ሊገጥመን አይገባም። ፋኖ “በአራት አቅጣጫ አይደለም በ44 አቅጣጫ ይምጡ በአፍንጫቸው እናቆማቸዋለን” እንዳለው በሁለት አቅጣጫ የመጡ ጠላቶቻችንን መክቶ ሊያሳየን ይገባል። መመከት ባይችል መወዳጀት ወደፊት የሚችል ትውልድ እንዳይመክታቸው አበክሮ ማምከን ነው።
በመሪ አልባው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል እና በአርበኛ እስክንድር ነጋ በሚመራው የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት መካከል ወደ ጎን የሚደረግ ውጊያ በሕዝባዊ ተቃውሞ መቆም አለበት። በሰራዊት እንጃ ባይነት መክሸፍ አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ሁለቱ አገደኛ ካርታዎች መሬት ላይ እንዲሰመሩ መፍቀድ ነው።