>

አቤ ጉበኛ፥ ለሐቅ የታመነ የፖለቲካ ነብይ

አቤ ጉበኛ፥ ለሐቅ የታመነ የፖለቲካ ነብይ

 

አርበኛ ፋኖ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው

 

ጊዜው  ሰኔ 25 ቀን 1925 ዓ.ም. ነው። በዚህ ቀን በዕለተ መርቆርዮስ ለሐቅ የታመነው የፖለቲካ ነብይ ሞገደኛው ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና አርበኛ አቤ ጉበኛ ተወለደ። የአባይ ብቻ ሳይሆን የአርበኝነት መፍለቂያ፣ የጤፍ፣ የማር እና የወተት ጎተራ ብቻ ሳይሆን የቅኔ፣ የድጓው የሊቃውንት መንበር ብሎም የምስጢራት ማመስጠሪያ በሆነው ጎጃም አቸፈር ወንድዬ፣ ኮረንች በአታ የተወለደው አቤ ጉበኛ ዛሬ 92ኛ አመት የልደት በዓሉ ነው። ይህ ሰው የእውነት ኑሮ ስለ እውነት የተሰዋ ጀግና ነው። እናቱ ወ/ሮ ይጋርዱ በላይ ይባላሉ። አባቱም የኮረንቹ ባላባት አቶ ጉበኛ አምባዬ ናቸው። ወ/ሮ ይጋርዱ ገና በ17 አመታቸው አቤን ወልደው ስላረፉ አቶ አምባዬ ያለ እናት ልጃቸውን ለማሳደግ ተገደዋል። 

አቤ ጉበኛ ከልጅነቱ ጀምሮ የአብነት ትምህርትን ቀስሟል። ከኮረንች በአታ በግምት በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጥንታዊቷ ይስማላ ጊዮርጊስ ከተማ ከየኔታ ገሰሰ ዘ-ይስማላ ዘንድ ይማር በነበረበት ጊዜ መርጌታውን ጉድ ያስባለ የትምህርት ችሎታ ነበረው። ቆይቶም የአስኳላ ትምህርቱን በዳንግላ ከተማ ተምሯል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በርካታ የውጣ ውረድ እና የስኬት ጊዜያትን አሳልፏል። በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ስር በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በጋዜጠኝነት፣ በጤና ሚንስቴር በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያነት አገልግሏል። ሆኖም ለሐቅ እና ለሰፊው ሕዝብ ከነበረው ውግንና የመነጨ ከሹማምንት ጋር ባለመስማማቱ የመንግስት ሥራዎቹን መቀጠል አልቻለም። 

በግሉ በሚፅፋቸው የድርሰት ተግባራት ላይ አተኮረ። የተለያዩ የመድረክ ቴአትሮችን፣ ተውኔቶችን፣ ረጅም ልብ-ወለዶችን፣ ግጥምን፣ ታሪካዊ ልብ-ወለድን መፃፍ የዕለት ከዕለት ሥራው ሆነ። በዚህም በኢትዮዽያ የስነ-ፅሁፍ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆነ። ከ20 በላይ መፅሐፍትን እና የመድረክ ቴአትሮችን አሳትሟል። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ልብ-ወለዶች ማለትም “The Savage Girl” (ጨካኟ ኮረዳ) እና “Defense” (አልሞት ባይ ተጋዳይ) የተባሉት መጽሐፍት በእንግሊዝኛ የተፃፉ ናቸው። 

የዚህ መጣጥፍ ማዕከላዊ ትኩረት የአቤን ግለታሪክ ከመተረክ ይልቅ ፖለቲካዊ ስብዕናውን እና የፖለቲካ ትንበያ ችሎታውን መዳሰስ በመሆኑ ሥራዎቹን ከመዘርዘር እቆጠባለሁ። ለመሆኑ ደራሲውን ተቀብሎ ያሳደገው የፖለቲካ ነፋስ እንዴት ነበር? የተረጋጋ ወይስ ወጀብ የሚያናውጠው? ደረቅ ወይስ ካፊያ የቀላቀለ? አስከፊ ወይስ አስደሳች? 

የዘመኑ የፖለቲካ ሁናቴ

 ወቅቱ ፋሽስት ጣልያን ከአርባ አመታት ዝግጅት በኋላ ኢትዮዽያን በድጋሜ ለመውረር ያቆበቆበበት ነበር። ሩባቲኖ የተባለው የጣልያን የመርከብ ንግድ ድርጅት በንግድ ሽፋን ወደ ኢትዮዽያ ገብቶ ወታደራዊ የስለላ ሥራዎችን ይሠራ የነበረበት፣ የካቶሊክ ሚሽነሪ ቄስ እና መነኩሴዎች በሀሳዊ ቆብ እና ነጭ ሻሽ ተሸፍነው ወታደራዊ የካርታ ስዕሎችን ይስሉ ብሎም የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንትን በዶግማ እና ቀኖና ያጋጩ፣ አለፍ ሲልም በቤተ ክህነቱ እና በቤተ መንግስቱ መካከል ስንጥቅ ይፈጥሩ የነበረበት ሰሞን ነው። በድምሩ ጣልያን በታሪኳ ካደረገቻቸው ጦርነቶች ሁሉ የላቀ የውጊያ ዝግጅት አድርጋ ኢትዮዽያን ለመውረር በአውራ ጣቷ የቆመችበት  ዘመን ነበር። በጠሊቅ ለመዘጋጀቷም ሁለት ምክንያቶች አሉት፦ 

1. በ1888 ዓ.ም. አድዋ ላይ የገጠማት ሽንፈት ዳግም እንዳይደርስባት በማሰብ ሲሆን 

2.ኢትዮዽያ የጸረ ቅኝ ግዛት ማዕከል መሆኗ ነበር። 

ይህ ሁለተኛው ምክንያት በበርሊኑ የቅርምት ጉባኤ ጭምር የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች የተስማሙበት ነው።  ኢትዮዽያ ላይ ካሸነፉ ሌላው የአፍሪካ ምድር ላይ በቀላሉ የድሎች ባለቤቶች እንደሚሆኑ ተንትነዋል። በመሆኑም ጣልያን ለወረራ ስትመጣ የጎረቤት ቅኝ ገዥዎች ማለትም የእንግሊዝና የፈረንሳይ ተራዳኢነትም ተጨምሮላታል። ፈረንሳይ ኢትዮዽያ ከውጭ የገዛቻቸውን የጦር መሳሪያዎች በቅኝ ግዛቷ ጅቡቲ በኩል እንዳታስገባ በደባ (Military Sabotage) ስትከለክል እንግሊዝ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ከሀገር እንዲሰደዱ የፖለቲካ ደባው (Political Sabotage) መሪ ነበረች። ሆኖም ኃይለ ሥላሴ በስደት ሆነው በፈቃዳቸው ዘውዳቸውን ለጣልያን እንዲያስረክቡ ለማድረግ የተሸረበው ሳይሳካላት ቀረ። በሂደት የመንግሥታቱ ማሕበር ጥርስ የሌለው አንበሳ እየሆነ፣ የአለም የፖለቲካ አሰላለፍ መልክ እና ቅርፁን እየቀየረ ወዳጅ የነበረው ጠላት፣ ጠላት የነበረው ወዳጅ መሆኑ ግድ ሆነ። በሁለተኛው የአለም ጦርነት አሰላለፍ ምክንያት እንግሊዝ ከጣልያን ጋር ጦር ተማዛ የኢትዮዽያ ሽርክ ሆነች። በርግጥ ከድል በኋላም ጣልያን ተሸንፋ ስትወጣ እንግሊዝ ኢትዮዽያን የራሷ ቅኝ ግዛት የማድረግ ሙከራ አድርጋለች። ይሁን እንጂ በኢትዮዽያውያን የአርበኝነት ጥንካሬ እና ንጉሰ ነገስቱ ከአሜሪካው ፕሬዚደንት ሩዝቬልት ጋር በፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የኃይል ሚዛኑ ጠንካራ በመሆኑ ሳይሳካ ቀርቷል። በመጨረሻም የእንግሊዝ ሙከራ የኢትዮዽያን ንብረት ዘርፎ ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ቅኝ ግዛቷ በማጋዝ ብቻ ተደመደመ። 

አቤ በተወለደበት ዘመን የሀገራችንን የውስጥ ፖለቲካ ስንመለከት  በቅኝ ገዥዎች ልክ ለጸረ ቅኝ ግዛት መዘጋጀት እንደ ሰባተኛው ሰማይ ርቆን ከዳግማዊ ምኒልክ ኅልፈት በኋላ በስልጣን ሽኩቻ የምንናቆርበት ጊዜ ነበር። በአንድ በኩል በቱርክ እና ጀርመን የሚታገዘው የልጅ እያሱ ቡድን፣ በሌላ በኩል የመኳንቱ እና ወዛዝርቱ ሙሉ ድጋፍ የነበረው የተፈሪ መኮንን (ኃ/ሥላሴ) ቡድን፣ በሌላ ገፅ የእቴጌ  ጣይቱ እና የሹማምንቱ ውዝግብ ሽቅብ የጎነበት ሰዓት ነው። 

ከሁሉም የከፋው ይህ ዘመን ከላይ በተጠቀሱት ሽኩቻዎች ምክንያት የሰገሌው የእርስ በእርስ ጦርነት የፈጠረው ዳፋ ቁልጭ ብሎ የሚታይበት መሆኑ ነው። 

አቤ ጉበኛ ሲወለድ የተቀበለው የፖለቲካ መልክ ይህ ነበር። የሦስት አመት እግር ተከል ልጅ ሆኖ ሳለ ነው ጣልያን ኢትዮዽያን የወረረቺው። አቤ የተወለደበት የአቸፈር ወንድዬ ግዛትም አርበኞቹ እነ ቢትወደድ አያሌው መኮንን፣ እነ ፊታውራሪ አውደው ሐበሻ፣ እነ ቢትወደድ መንገሻ ጀንበሬ እና ሌሎችም ከፋሽት የመርዝ ጋዝ ጋር ይፋለሙበት የነበረ ቀጣና ነው። ይህ ቀጣና ንጉሠ ነገስቱ ከሎንዶን በካርቱም ወደ አዲስ አበባ የገቡበት መንገድ በመሆኑ በድሉ ዋዜማም ከፍተኛ ትንቅንቅ የተደረገበት ነው። ፋሽስት ጣልያን በሶማሊያ ቅኝ ግዛቱ ያመረታቸው ገና ስም ያልወጣላቸው አዳዲስ የኬሚካል መርዞች በሄሊኮፍተር በስፋት የተረጩት በአቸፈር ወንድዬ ነው። በመሆኑም አቤ ከ3 እስከ 8 አመት በሚሆን የእድሜ ክልሉ ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ አለም ላይ ፈፅሞ ተደርጎ የማያውቀውን ዘግናኝ ጦርነት ተመልክቷል። “አማራ ጨቋኝ ነው” ብለው የተነሱ የተማሪ ፖለቲከኞችን ክፋታቸውን ለመግለጽ “ጥቁር ጣልያናውያን” ይላቸው የነበረው የጣልያንን ግፍ ከልጅነቱ ጀምሮ በማስተዋሉ ይመስላል።

ይህን የመሰለ የፖለቲካ ሁኔታ በነበራት ኢትዮዽያ ውስጥ ያደገው አቤ ጉበኛ በእውቀት ዘመኑ ወርቃማ ሥራዎችን ሠርቷል። በተለይም እንደ ወርቅ የነጠረ የፖለቲካ ስብዕናው ከሩቅ የሚለይበት ምልክቱ ነበር። መጭውን የፖለቲካ አዝማሚያ በመረዳት እና በልብ-ወለድ መጽሐፎቹ እንዲሁም በመድረክ ቴአትሮቹ ቁልጭ አድርጎ በማሳየትም ይታወቃል። በዚህም በፖለቲካ መተርጉማን እና በኪነ ጥበባት ሀያሲያን ዘንድ “ነብዩ ደራሲ” ተብሏል። 

የፖለቲካ ነብይ ሲባል? 

አቤን የፖለቲካ ነብይ ያስባሉት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነኝህ መካከል ጥቂቶችን እንጥቀስ፦ 

ደራሲው በስፋት የሚታወቅበት በመታተም ተራ ስድስተኛ መጽሐፉ የሆነው “አልወለድም” ነው። ድርሰቱ መንድ ላይ ተቀምጣ አምስት፣ አስር ከምትለምን የእኔ ቢጤ የተረገዘ ጽንስ በእናቱ ሆድ ውስጥ ሆኖ “እውነት በሌለበት አለም ለመኖር አልወለድም። የገዥዎች ኑሮ ማዳመቂያ ለመሆን እምቢ አልወለድም” እያለ ሲያምፅ ይተርካል። ይህ ፅንስ ያለ ፍላጎቱ በግዳጅ በሀኪም ተጎትቶ ከተወለደ በኋላ በሰላም ግሮ ከሚኖርበት ገዥዎች እየመጡ ቁምስቅል ሲያሳዩት፣ እነርሱንም ሲቃወም መፅሐፉ ይተርካል። በአጠቃላይ አቤ በዚህ መጽሐፍ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት መካከለኛ እና የበታች ሹማምንት ሰፊውን ሕዝብ ሲጨቁኑ ያሳያል። እዚህ ላይ ደራሲው ንጉሳዊ ስርዓቱን በመሰረታዊነት እንደሚቀበልና ዘውዱ ሕገ መንግስታዊ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን ልብ ይሏል። መኳንቱ ሕዝቡን ጭሰኛ እያደረጉ ይበድሉ የነበረበትን አሰራር አጥብቆ ይተቻል። ይህ በመፅሐፉ ቁልጭ ብሎ ከመቀመጡ በላይ ዘውዳዊ ስርዓቱ በወታደሩ እንደሚፈነቀል አስቀድሞ ተንብይዋል። አቤ እንደፃፈው ዘውዱ በደርግ የወታደሮች ስብስብ ተሰበረ። 

የፖለቲካ ነብይ ካስባሉት ክስቶች መካከል አንዱ ይህ ትንታኔው ነው። ለመሆኑ የኃይለ ስላሴን በደርግ መገልበጥ  እንዴት አስቀድሞ መተንበይ ቻለ? ሦስት የትንታኔ ሰበዞች ለዚህ ያበቁት ይመስለኛል፦ 

ሀ-የ1953ቱ የመፈንቅለ መንግት ሙከራ 

የተማሪዎች ንቅናቄ በክቡር ዘበኛ ጦር ዋና አዛዡ በጀኔራል መንግስቱ ንዋይ ወንድም ግርማሜ ንዋይ አማካኝነት ቤተ-መንግስት ድረስ ሰብሮ በመግባት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን አደረገ። በዚህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተሳተፉት ራሳቸው ጀኔራል መንግስቱ ንዋይ፣ የደህንነት ሹሙ ጀኔራል ወርቅነህ ገበየሁ (በርግጥ እሳቸውን ተገደው ገቡ እንጂ ፈልገው አልተሳተፉም የሚሉ አሉ) እንዲሁም የፖሊስ አዛዡ እና ሌሎች የፖሊስ እና የክቡር ዘበኛ ጦር አባላት ተሳትፈዋል። ከዚህ ክስተት በኋላ የክቡር ዘበኛ ጦር እንደፈረሰ የሚያትቱም አሉ። ግርማሜ  ራሱን ሲያጠፋ “ሙከራችን ስኬታማ ባይሆንም ለዘመናት የተማሪዎችን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያፍን የነበረው አንተ የምትመራው ጦር መበፍረሱ ደስተኛ ነኝ” ሲል ለጀኔራል መንግስቱ መናገሩን አቶ ብርሐኑ አስረስ የታህሳሱ ግርግር በተባለው መፅሐፋቸው አስፍረዋል። 

የሆነው ሆኖ እዚህ ላይ ለአቤ ጉበኛ ትንታኔ መሰረት የሆነው ጉዳይ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው የወታደሮች ተሳትፎ እና ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ነው። አድፍጦ የተቀመጠ፣ የተቆጣ ወታደር መኖሩም ታውቆት ነበር። ስለዚህ ከፍንቀላ ሙከራው ሁለት አመታት በኋላ ማለትም በ1955 ዓ.ም. አልወለድም-ን ለህትመት ብርሃን ሲያበቃ ገሀድ የወጡም ሆኑ ያደፈጡ ወታደሮች ተሰባስበው ንጉሱን መገልበጣቸው አይቀሬ እንደሆነ ፃፈ። ንጉሰ ነገስቱም ይህ ስላስደነገጣቸው መፅሐፉ ተሰብስቦ እንዲቃጠል አዘዙ። አልወለድም አመድ በመሆን ቀለማዊ ሰማዕትነትን ተቀበለ። ሆኖም ከአመድ ውስጥ ፈልጎም ቢሆን ሕዝቡን ከማንበብ ያገደው የለም። የአቤ የፖለቲካ ትንበያም ከ11 ዓመታት በኋላ በ1966 ዓ.ም. እውን ሆነ። ከአብዮቱ በኋላ የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ መተርጉማን “አዝጋሚው መፈንቅለ መንግሥት” (The Walking Coup Deta) እያሉ ስለመንቅለ መንግስቱ አመጣጥ የአቤን ኃሳብ ደግመው መፃፍ ቀጠሉ። 

ለ-የሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ

ይህ ወቅት ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡም በውስጣዊ የስልጣን ሽኩቻ ይናጡ የነበረበት እና መፈንቅለ መንግስት የተዘወተረበት ጊዜ ነው። አፍሪካ በወታደሮች እጅ ወድቃ የነበረበት ሰሞን ነው። ስለዚህ ‘ሀገር ለመምራት ጠመጃ እንጂ እውቀትም ሆነ መለኮታዊ ተቀብዖ አያስፈልግም’ የሚለው የአስር አለቃዎች ወረርሽኝ የኢትዮዽያ ወታደሮችንም እየለከፈ እንደነበር አቤ በንፅፅሮሽ ያስተዋለ ይመስለኛል። 

ሐ- የአፄ ኃይለ ስላሴ ኢ-ተራማጅነት 

ንጉሰ ነገስቱ በእነፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም አርቃቂነት የተዘጋጀ ሕገ መንግስት የነበራቸው ቢሆንም ከዘመኑ ተራማጅ ምሁራን ሹሞቻቸው ፍላጎት ጋር ተናበው አለመሄዳው የፈንቃዮችን ፍላጎት እና ጉልበት እንደሚያሳድገው እንዲሁም ጠላቶቻቸውን እንደሚያበዛው አቤ የተረዳ ይመስላል። በተለይም ሕገ መንግስታዊ ዘውዳዊ ስርዓት ይኑር የሚለውን ጥያቄ በሙሉ ልብ ያለመቀበላቸው እና ሕገ መንግስቱ ዜጋውን እና ሌሎች ሹማምንትን እንጂ እሳቸውን የማይዳኝ አድርገው ማሰባቸው ለፈንቃይ ወታደሮች ጉልበት እንደሚሆናቸው ሳይገምት አልቀረም። 

ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና አርበኛ አቤ ጉበኛን “የፖለቲካ ነብይ” ያስባሉት ሌሎች ድርሰቶችም አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ “የሮም አወዳደቅ” የተባለው ተውኔቱ ነው። በዚህ ድርሰት በኢትዮዽያ ዘውዳዊ ስርዓት ሊያከትም እንደሚችል ተንብይዋል። ኃይለ ስላሤ ስልጣን ቢለቁ የሚመጣው ለውጥ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ  ወደ ተክለ ጊዮርጊስ፣ ከተክለ ጊዮርጊስ ወደ ዮሀንስ፣ ከዮሀንስ አራተኛ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ. . . እንደተደረገው ሽግግር መሆኑ ቀርቶ የሰሎሞናዊ ስርዎ መንግስት ሊቋረጥ እንደሚችል አስቀድሞ አስጠንቅቋል። ሆኖም አሳሪ እንጂ ሰሚ ባለመገኘቱ የሆነው ሆነ። አቤም በአስደናቂ የአፃፃፍ ችሎታው፣ በግሩም የገጸ ባሕሪ አሳሳሉ፣ አንጎልን በሚጨምቅ ፖለቲካዊ ፍልስፍናው፣ በዳዮችን ቁጭ ብድግ በሚያደርግ ተንኳሽ አቀራረቡ፣ ሕዝብን በሚቀሰቅስ ለኳሽ አተራረኩ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርን በተጎናጸፈ የሞራል ልዕልናው እና በማይወላውል የፖለቲካ ስብዕናው በርካታ አድናቂዎች እያገኘ መጣ። 

የፖለቲካ ስብዕና

አቤ ወደ ቀኝ ይሁን ወደ ግራ፣ ወደ ፊት ወይም ወደ ኋላ የማያጋድል፣ ለሰፊው ሕዝብ እና ለሐቅ የታመነ ቀጤ የፖለቲካ ስብዕና ነበረው። ለአመነበት አላማው እስከ ሞት የታመነ ነው። ልክ እንደ ገጸ ባሕሪው እርሱም  “ግፋ  ቢል ብትገድሉኝ እንጂ ምን ታደርጉኛላችሁ” ሲል ይደመጣል። ይህም በተደጋጋሚ በተግባራዊ ሕይዎቱ ታይቷል። ለዚህ እንደምሳሌ የሚጠቀሰው የደርግን አገዛዝ የተቃወመበት ሂደት ነው። አቤ በአልወለድም መፅሐፉ የንጉሰ ነገስቱን በወታደሮች መገልበጥ ብቻ ሳይሆን  የደርግን ጸረ ሕዝብነትም ተንብይዋል። መጭውን ብቻ ሳይሆን የመጭውን አስከፊነት ጭምር ማወቁ የፖለቲካ ትንበያ ችሎታውን ከፍ ያደርገዋል።

በሁለቱ ስርዓቶች ላይ የነበረው ተቃውሞም የተለያየ ነበር። የደርግ ስርዓት ከስሩ ተነቅሎ መጣል አለበት ብሎ ያምን ነበር። ይህን ለማሳካት በድርሰት ሥራዎቹ ብቻ መታገል በቂ አልሆነለትም። በመሆኑም ቦላሌውን አውልቆ ቁምጣ ሱሪ በመታጠቅ፣ ብዕሩን አስቀምጦ ጠመጃ በማንገት ከጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ስሜነህ ደስታ ጋር ጫካ ገባ። በሜጫ እና በአቸፈር ወንድዬ ጫካዎች ሰራዊት ማሰልጠናቸውንም ተያያዙት። በባሕር ዳር፣ በዱር ቤቴ፣ በመራይ ወዘተ የደርግ ወታደሮችን እያደኑ የሽምቅ ጥቃታቸውን ተያያዙት። በአንድ አውደ ውጊያ አቤ በጥይት ተመቶ በመቁሰሉ ባሕር ዳር ለሕክምና ገባ። በባሕር ዳር ከተማ እየታከመ በነበረበት ጊዜ አለባበሱ ብቻ ሳይሆን የከተማው መልክና ሰውነቱም ስለተለወጠ እርሱ መሆኑን ያወቀ አልነበረም። ከብዙሃኑ ገበሬ አርበኞች እንደ አንዱ ሆኖ ነበር። ታላቁ ደራሲ የትጥቅ ትግል የመጀመሩ መረጃም አስቀድሞ በምስጢር የተያዘ ነበር። 

ከዚያ በኋላም በተለያዩ ምክንያቶች ወታደራዊ እንቅስቃሴው ተቋርጦ አቤም ከቁስሉ አገግሞ ወደ ድርሰት ሙያው ተመልሷል። 

በአንፃሩ በንጉሳዊ ስርዓቱ ላይ የነበረው ተቃውሞ በዚህ ልክ የጠነከረ አልነበረም። የሕዝብን ፍላጎት አስቀድሞ ከቀዳማዊ ምኒልክ በተዋረድ የመጣው ሰሎሞናዊ መንግስት እንዲቀጥል ይፈልግ ነበር። በመሆኑም በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ መንግስት ላይ የነበረው እንቅስቃሴ አስተዳድሩን የመግራት እንጂ የመንቀል አልነበረም። ጃንሆይም ይህንን ታሳቢ በማድረግ አቤ ጉበኛ የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ገዥ እንዲሆን ጠይቀውት ነበር። “ተበላሸ የምትለውን አሰራር ከውስጥ ሆነህ አብረን እናስተካክል” ብለውታል። በዚያን ጊዜ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት ማለት የአሁኖቹን ሁለቱን ሰሜን ሸዋዎች፣ ምስራቅ ሸዋን፣ ምዕራብ ሸዋን፣ ከፊል አሩሲን፣ አዲስ አበባን ወዘተ የሚያጠቃልል ነበር። ሆኖም አቤ ሹመቱን ሳይቀበል ቀርቷል። ላለመቀበሉ ሁለት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፦ 

1.የድርሰት ሥራዎቹ ውስጥ ጠልቆ ስለገባ ከስነ ጽሁፍ  ላለመውጣት 

2.የጃንሆይ ቢሮክራሲ በመላ ሀገሪቱ ጭሰኛውን ሕዝብ ያስከፋ መዋቅር ስለነበረው የአንድ ጠቅላይ ግዛት ገዥ ቢሆንም ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ በማሰብ ይመስል። 

ለመሆኑ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለአቤ ለምን ሸዋን መረጡለት? ለዚህ ሦስት የቢሆን ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፦ 

1- ሌሎች ጠቅላይ ግዛቶች በአካባቢው አልጋ ወራሾች አስቀድሞ የተያዙ በመሆኑ አዲስ ሰው ለመሾም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። ለምሳሌ በዚህ ወቅት አቤ ተወልዶ ያደገበት እና በቅርበት የሚያውቀው የጎጃም ጠቅላይ ግዛት በንጉሥ ተክለኃይማኖት አልጋ ወራሾች በእነራስ ኃይሉ የተያዘ ነው። እነርሱን ሽሮ አቤን መሾም ጦር ያማዝዛል። ከዚህ ቀደም ከአልጋ ወራሾች ነጥቀው ወንበሩን ለራስ እምሩ በመስጠታቸው የደረሰባቸውን ተቃውሞ አይተዋል። ከጠቅላይ ግዛት ያነሰ ስልጣን ደግሞ ለአቤ ያንስበታል። ከሸዋ በስተቀር ወደ ሌሎች ጠቅላይ ግዛቶችም ስንሄድ ነገሩ ተመሳሳይ ነው። በአንጻሩ በሸዋ የንጉስ ሣህለ ስላሴ አልጋ ወራሾች ከራሳቸው ከንጉሰ ነገስቱ ጀምሮ አራት ኪሎ ስላሉ ጠቅላይ ግዛቱን አሳልፎ ለመስጠት እምብዛም አይገዳቸውም። 

2- በወቅቱ አቤ ጉበኛ የሚኖረው በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ አዲስ አበባ በመሆኑ

3- አቤ ከተቃውሞ የመጣ በመሆኑ በኃይለ ስላሴ ዘንድ ሙሉ እምነት ስላልተጣለበት እና በቅርበት ለመከታተል እንዲያመች

 ከአገዛዞች ባሻገር

አቤ ጉበኛ ወዳጅ ለማብዛት፣ ጠላት ለመቀነስ ሲል በሽፍንፍን የሚያልፋቸው ፀረ ሕዝብ አጀንዳዎች አልነበሩም። ሽርክናው ከሰፊው ሕዝብ እና ከሀቅ ጋር ነው። ተጠሪነቱ ለእነኝሁ ነበር። ከደርግ እና ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ መንግስት በተጨማሪ ‘ሕዝብን ይጎዳሉ’ ያላቸውን ሁሉ በሰላ ብዕሩ ይቃወም ነበር። 

በክርስትና፣ በተስካር፣ በቁርባን እያሳበቡ ሕዝብን የሚበዘብዙ ካሕናትን በሚያውቁት ቅኔ ይኮረኩማቸዋል። በብዕሩ ይገስፃቸዋል። ጥራዝ ነጠቅ የተማሪ ፖለቲከኞችን “ጥቁር ጣልያኖች” ሲል ይወርፋቸዋል። “ኢትዮዽያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት ናት” የሚሉ ጥራዝ ነጠቆችን ቀርቶ ከሀገርና ሕዝብ፣ ከብሔራዊ ጥቅም ውጭ ግላዊ ስሜት ላይ አተኩረው ስለ ፍቅር ይፅፉ የነበሩ ደራሲዎችን ስንኳን “ባልተኞች” እያለ ይሸነቁጣቸው ነበር። 

ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም እያሉ ይጎርፉ የነበሩ አለም አቀፍ የፖለቲካ ገበያተኞችንም ከመተቸት ወደ ኋላ አላለም። አቤ በተራ ሰዋ ሰው ከሚፅፈው ይበልጥ በአሽሙር እና በቅኔ የሚፅፋቸው ለበደለኞች የጣት ቁስል ሆነው ሲጠዘጥዙ ይኖራሉ። በአንድ ወቅት የደርግ ሶሻሊስት ካድሬዎች በባሕር ዳር ከተማ “ማክሳዊ”፣ “ሌኒናዊ”፣ “ኤንግልሳዊ” የሚባሉ ስልጠናዎችን እየሰለጠኑ ነው። ስልጠናው በሳምንታት የሚያልቅ ነበር። አቤም “ማርክስ፣ ሌኒን እና ኤንግስ የሚባሉ ሰዎች ደደቦች ስለነበሩ ሶሻሊዝምን ለማጥናት አመታትን ፈጀባቸው። የእኛ ገበሬዎች ግን ሊቆች ስለሆኑ ትምህርቱን ይኸው በሳምንት እየጠጡት ይወጣሉ” ሲል ነበር አሽሙራዊ ትችቱን ያቀረበው። ይህ እነማርክስን እንደ ሦስቱ ስላሶች ለሚቆጥሩት ባለቀይ መፅሐፍት ደርጎች መንፈስ ቅዱስን የማራከስ ያህል ነበር። 

አቤ ከፕሮፖጋንዳ ሰለባነት የነፃ እውነተኛው የዳግማዊ ቴዎድሮስ ታሪክ ይፋ እንዲሆን ያደረገው አስተዋፅኦም ከፍተኛ ነው። እርሱ “አንድ ለእናቱ” ታሪካዊ ልብ-ወለድን ከመፃፉ በፊት ስለ መይሣው ካሣ የነበረው ትርክት በፈረንጅ ጠላቶቻችን በጥላቻ የተተረከ እና ወወሸት ነበር። ቆራጭ፣ ጨካኝ ይባል የነበረውን ቴዎድሮስ ጀግና እና እንደ ሰው ሩህሩህ እንደነበርም አሳይቶናል። ተራ የኮሶ ሻጭ ልጅ ይባል የነበረውንም ከሰሎሞን የሚወለድ የነገስታት ዘር መሆኑን ሀረግ ስቦ አሳይቶናል። ጸረ ቤተ ክርስቲያን ይባል የነበረው ዘወትር ዳዊት ደጋሚ የመድኃኒዓለም ባሪያ፣ የስላሴ ገዳም ያደገ የስላሶች ልጅ መሆኑን ነግሮናል። ከአንድ ለእናቱ በኋላ የተሳሳተው ትርክት ተገልብጧል። 

በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ወጀብ የአቤ ጉበኛ ቀጤ መስመር ለአፍታ አልተወላገደም። ለአንዱ ወግኖ ቢፅፍ ብዙ ሥልጣን፣ ብዙ ገንዘብ እና ሌላም ጥቅም ያገኝ መበር። ሆኖም ይህ ከሕዝብ ጥቅም አልቀደመበትም። ልጆቹን ለማሳደግ ገንዘብ ሲያጥረው በባሕር ዳር ጎዳናዎች ሱቅ በደረቴ እየሠራ፣ አገዛዞች ሲጠነክሩበት እስከ ኢሉባቡር ጎሬ ድረስ ተግዞ እየታሰረ፣ መጽሐፎቹን በአዲስ አበባ ለማሳተም ሲከለከል አስመራ በድብቅ እያሳተመ በበትር ተደብድቦ ሰማዕት እስከሆነበት ጊዜ ድረስ ከሰፊው ሕዝብ እና ከሐቅ ጋር ኖረ። 

 አሟሟት

ሞገደኛው ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና አርበኛ አቤ ጉበኛ በወቅቱ ኑሮውን ካደረገበት ከባሕር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ ነበር። ወደ አዲስ አበባ የመሄዱ ምክንያት አዲስ መጽሐፍ ለማሳተም እና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ቴአትር ለማሳየት ነበር። ደብረ ማርቆስ ከተማ ሲደርስ በደርግ ታገተ። ሆኖም ከወቅቱ የሀገሪቱ መሪ እና የደርግ አለቃ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘንድ “ልቀቁት ይምጣ” የሚል ትዕዛዝ በመድረሱ ተለቀቀ። እንዲለቀቅ የተፈለገው ለመግደል ከደብረ ማርቆስ ይልቅ አዲስ አበባ የተሻለ ወጥመድ መሆኑ ታምኖበት ይመስላል። ኤልያስ አያልነህ ‘የአቤ ጉበኛ ብእራዊ ተጋድሎ’ በተሰኘው መጽሐፉ ይፋ እንዳደረገው ቅዳሜ ምሽት የካቲት 1 ቀን 1972 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ በበትር ተደብድቦ ወድቆ ተገኘ። በዚሁ አካባቢ የሚገኘው የአቸፈር ቡና ቤት ባለቤት የነበሩ እናት አስተባብረው ሰዎች አነሱት። ሆኖም ወደ ሆስፒታል ከመውሰድ ይልቅ አስቀድሞ ምኝታ ክፍል ተከራይቶበት ወደ ነበረው አርባ ምንጭ ሆቴል ወስደው አስተኙት። በማለዳው እሁድ ወደ ዻውሎስ ሆስፒታል ተወሰደ። እዚያም ከአፍታ በኋላ ሕይዎቱ ማለፉን ሀኪሞች አረዱ። 

ለሕዝብ መብትና ጥቅም ሲል የተዋጋውን፣ የቆሰለውን፣ የታሰረውን፣ የተደበደበውን እና በመጨረሻም የተገደለውን የአቤ ጉበኛን አስክሬን ከዻውሎስ ሆስፒታል ተቀብሎ አፈር የሚያለብስ አንድ ሰው ጠፋ። በመጨረሻም ማዘጋጃ ቤት ሊቀብረው ሲል አቶ ሲራክ ቀለመ ወርቅ የተባሉ ሰው ደፍረው ገቡበትና አስክሬኑን ተቀበሉ። ሲራክ፣ አቤ የዳንግላ ትምህርቱን አቋርጦ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ሲሄድ የተዋወቃቸው ወዳጁ ናቸው። ባለሱቅ ነበሩ። 

ታዲያ ሲራክ ከተቀበሉ በኋላ የአስክሬን ምርመራ መደረግ አለበት ተብሎ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ተወሰደ። በዚህም የአንጎሉ የውስጠኛ ክፍል ማበጡ፣  ደም ወደ ጭንቅላቱ ውስጥ መፍሰሱ በአጠቃላይ በስለት አልባ ወይም ዱልዱም መሳሪያ ጭንቅላቱን ተደብድቦ መገደሉ ተረጋገጠ። ይህንን የአስክሬን ምርመራ ማስረጃ ኤልያስ  በራስጌ  በተጠቀሰው መጽሐፉ አትሞታል። 

ማክሰኞ የካቲት አራት ቀን 1972 ዓ.ም. የአቤ ጉበኛ አስክሬን ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ አካባቢው ጎጃም ተወሰደ። ፊደል በቆጠረባት ጥንታዊቷ ከተማ ይስማላ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተቀበረ። ዛሬም አቤ ነጭ ጠጨባብና ነጭ ሱሪ ለብሶ፣ “አልወለድም” ያለውን መጽሐፉን ገልጦ፣ ፊቱን ወደ ምስራቅ አዙሮ ቁሞ የሚታይበት ሀውልት በመቃብሩ ላይ አለ። የቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር ዋናው መግቢያ ላይ መሳለሚያው ስር እንደቆመ ነው። ዛሬም ድረስ በይስማላ ታሪክ በሰው አምሳል ተቀርፆ የቆመ ብቸኛው ሐውልት ነው። 

እዚህ ላይ አንድ ገጠመኝ አለኝ፦ እኔ የዚህ መጣጥፍ ጸሀፊ ተወልጄ ያደግኹት በዚሁ በአቸፈር ወንድዬ ነው። እግር ተከል ልጅ እያለሁ ጆሮየን ያመኝ ነበር። እናቴ ወ/ሮ መንግስቴ ላቃቸው (ዛሬ እማሆይ) ሀኪም ቤት እንድሄድ አትፈልግም ነበር።  እንድትወስደኝ ሰዎች ሲመክሯትም “እሱ የምኪሀል (የሚካኤል ማለቷ ነው) የስለት ልጅ ስለሆነ ራሱ መላኩ ያድነዋል” በማለት ክርስትና ከተነሳሁበት ከታላቁ የላሊበላ ቅዱስ ሚካኤል ደብር ወስዳ ታስቆርበኛለች። ጸበል ታስጠምቀኝማለች።

 (በነገራችን ላይ እዚህ ላይ የጠቀስቀኩት “ላሊበላ” ጎጃም አቸፈር ወንድዬ ያለ ሌላ ላሊበላ እንጂ ላስታ ላሊበላ አይደለም። ንጉስ ቅዱስ ላሊበላ ወደ እየሩሳሌም ከመሄዱ በፊት እንደነበረበት ትውፊት ያወሳል። እናም ቀደምት ላሊበላ እየተባለ ይታወቃል። ዛሬ ላስታ ካሉት የሚመሳሰሉ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትም አሉት)

ወደ ጆሮ ህመሜ ልመለስ። ሰዎች እናቴን ከህመሜ ቶሎ እንድፈወስ ወደ ሦስት የተለያዩ ደብሮች ወስዳ ማስቆረብ እንዳለባት ይመክሯታል። መንፈሳዊ ምክሮችን የመቀበል ልማዷ ከፍተኛ ስለሆነ ቶሎ ተቀበለቻቸው። ስለዚህ እንደ አባቴ ቤት ከማየው ከሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ደብር በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሌላ ሁለት አድባራት የመሄድ እድል ገኘሁ። ከነፍስ አባታችን (እኔ የነፍስ አባት ለመያዝ ባለደርስም የቤተሰባችን ብቻ ሳይሆን የሰፈራችን አባት ነበሩ። ናቸውም)  ከየኔታ አንተነህ እና በእሳቸው ዙሪያ ከማያቸው ቀሳውስት በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ በሌላ ካህን እጅ የመቁረብ፣ በሌላ ቄስ መስቀል የመዳሰስ በረከት ገጠመኝ። 

ሁለቱም የላሊበላ ጎረቤት አድባራት ናቸው። በእግር ከአንድ ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ያስሄዳሉ። እነዚህ ደብሮች አቤ ጉበኛ የተወለደባት ኮንች በአታ እና የተቀበረበት ይስማላ ጊዮርጊስ ናቸው።  

በአንድ ዕለተ ሰነበት እሁድ ይስማላ ጊዮርጊስ ስንደርስ እናቴ ወደ ቅጥር ግቢው የሚያሳልፈው የድንጋይ ካብ አጥር በር ስር ቆማ ትሳለምና ተንበርክካ መሬቱን፣ ቁማ የድንጋይ ካቡን ጠርዝ ትስማለች። ይህን ጊዜ እኔ በአንድ እጄ የነጠላዋን ጠርዝ ቁጭቱን እንደጨበጥሁ እጎኔ ፊቱን ወደ እኔ አዙሮ የቆመውን ግዙፍ ሰውየ አያለሁ። ሳየው ሳየው ዝም ብሎ ያየኛል። ፊቱን አያዞርም። አይንቀሳቀስም። ዓይኔን ነቅየ እቆይና እንደገና አየዋለሁ። ሁኔታው ሳይለወጥ እያየኝ አገኘዋለሁ። ሰው ነው ወይ? ለምን አይቀሳቀስም? አይደክመውም? ምንድን ነው? የልጅነት አዕምሮየን ያስጨቀዋል። 

አሁንም አተኩሬ ሳየው እቆይና አለቅሳለሁ። እናቴ  በነጠላዋ ሸፋፍና ታባብለኛለች። ሰይጣን አስፈራርቶኝ  ስለሚመስላት የቆመውን ደብርኛ ሁሉ እየጣሰች ከአንዱ ቄስ አጠገብ ትወስደኝና በመስቀል ታስዳስሰኛለች። እኔ ግን ሳየው ትኩር ብሎ የሚያየኝ፣ ዝምታው እንግዳ ሆኖብኝ የሚያስለቅሰኝ ሌላ ሳይሆን ከጎኔ የቆመው የሞገደኛው ደራሲ፣ ጋዜጠኛ እና አርበኛ አቤ ጉበኛ ሐውልት ነበር። 

ዝክረ አቤ ጉበኛ

አቤ ለሕዝብ እና ለሀገር ባደረገው አስተዋጽኦ ልክ አልተዘከረም። እንዳውም ተረስቷል ቢባል ይቀላል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በብዙ ግፊት ጥቂት ማስታወሻዎችን ማቆም ተችሏል። በይስማላ ከተማ ወደ ጉድሪ መውጫ አካባቢ አንድ መንግስታዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በስሙ ተቋቁሞ በማስተማር ላይ ይገኛል። በዚሁ ከተማ የሕዝብ ቤተ መጽሐፍት በስሙ ተከፍቷል። በዱርቤቴ ከተማ በአቤ ጉበኛ ስም የሚጠራ የባሕልና ኪነ ጥበባት ቡድን እንደነበረም አስታውሳለሁ። ሙያዊ እድገትን ጨምሮ አባላቱ በተለያዩ ምክንያቶች ዱርቤቴን ሲለቁ ከስሞ ይሁን ወይም ይቀጥል አላውቅም። 

በቀደምት ላሊበላ ከተማ አቢሲኒያ ባንክ አንድ ቅርንጫፉን በአቤ ስም ሰይሟል። 

ሆኖም እነኝህ ማስታወሻዎች ከአካባቢው ዘዋራነት የተነሳ ለብዙሃኑ ኢትዮዽያዊ ተደራሽ አይደሉም። በመሆኑም አቤ በደርግ ወታደሮች በትር እንደ እባብ ተቀጥቅጦ፣ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ተወግሮ ሰማዕትነትን በተቀበለበት አዲስ አበባ ጎጃም በረንዳ ግዙፍ የመታሰቢያ ሀውልት ሊቆምለት ይገባል። በግፍ በግዞት በታሰረባት ጎሬ ከተማ መታሰቢያ ሊሠራለት ይገባል። በጎሬ ከተማ ይተኛባት የነበረቺውን ጠባብ ክፍል ከ9 አመታት በፊት በአካል ተገኝቼ ጎብኝቻለሁ። በወቅቱ የኢትዮዽያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቢሮው አድርጓት ነበር ያገኘኋት። ቤቷ እንደ ብዙሃኑ የጎሬ ቤቶች የተዛመመች እና ለመፍረስ የቃጣት ነበረች። 

ከባለመብቶቹ ጋር በመስማማት ወይም ሌላ ሕጋዊ ሂደቶች ካሉ በመጠቀም መጽሐፎቹን መልሶ ማሳተምና ማሰራጨት፣ ወደ ፊልምና መሰል ዝግጅቶች መለወጥ ተገቢ ነው። በአጠቃላይ አቤን ከዚህ እና ከመጭው ትውልድ ጋር የበለጠ ማቀራረብ ያስፈልጋል። ያለፉትን ከረሳን መጭዎች ይቀራሉ! ያሉትም ይደክማሉ!

 

Filed in: Amharic