የማራቶን ጀግና አበበ ቢቂላ ቃለ – መጠይቅ (1967)
ሻምበል አበበ እስከ ስንተኛ ክፍል ተምረሃል ?
በ፲፪ ዓመቴ የቄስ ትምህርትን ፈጽሜያለሁ ይኸውም ዳዊትን ከአንዴ ሦስቴ ደግሜያለሁ በገጠር ውስጥ በአቅራቢያ የሚገኘው የመጀመሪያ ትምህርት ይህ ነው ከዚህ ሌላ በእንግሊዝ ት/ቤት ውስጥ አልተማርኩም የትምህርት ችሎታዬ እስከዚሁ ነው ግን እኔ ሌላ ጥሩና ትልቅ ትምህርት አለኝ የሚለውን አክሎበታል ።
የቄሱን ትምህርት ካገባደድክ በኋላ በምን ሥራ ላይ ተሠማራህ ?
ከዚህ በኋላ ነፍሴን አወቅሁ በኋላ የፈረስ ጉግስ ጨወታ በጣም እወድ ስለነበር በዚሁ በፈረስ ግልቢያ በጣም ጐበዝ ስለ ነበርኩ ያደንቁኝ ነበር በገና ጨወታና በሩጫም በጣም የታወቅኩ ነበርኩ ከዚህ በተረፈ ለቤተሰቦቼ በእረኝነትና በልዩ ልዩ በቤት ሥራ አገለግል ነበር።
ወደ እሩጫ ወይም ማራቶን ክፍል ስትገባ ያልፈቀ ደልህ ሰው ነበር?
ያማከርኩትም ሰው አልነበረም የከለከለኝም የለም።
አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ አበበ እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ሊገጥመው የቻለው የሰው ዓይን ስለበዛበት በቡዳ በልተውት ነው የሚባል ወሬ አለ ታዲያ አንተስ በዚህ ነገር ታምንበታለህ?
እርግጥ የዚህ ዓይነቱ ወሬ ብዙ ቦታ እንደሚወራ አውቃለሁ ይሁንና እኔ በዚህ በኩል ላምንበት አልችልም ምክንያቱም ዓይን ያያል እንጂ አይሰብርም ስለሆነም ይህ የፈጣሪ ትእዛዝ ነው እንጂ በሰው ዓይን ወይም በቡዳነት የተፈጠረ ነው ብሎ ለማመን አስቸጋሪ ነው
በዓለም ውስጥ በማራቶን ውድድር የምታደንቀው ማነው ?
እስከ አሁን በዓለም በማራቶን ውድድር በጣም የማ ደንቀው በመጀመሪያ እሮም ላይ ከኔ ጋር አብሮኝ የተካፈለው የሞሮኮው ተወላጅ እሬዲ የሚባለውን።
በአገራችን ውስጥ የምታደንቀው የማራቶን አትሌት ማነው ?
በአገራችን ሌላ ማን አለ? ያው ማሞን ነው እንጂ ሲል ተከታይ ወንድሙን አድንቋል።
ብዙዎቹ አበበ ችግርን በሩጫ አመለጠ ይሉሃል አንተስ ለዚህ ምን ትላለህ?
ብዙን ጊዜ በኛ በሰዎች ላይ ሰይጣናዊ ቅናት አለ ይኸውም ለዚህ ለጠየቅከኝ ጥያቄ መልስና ማስረጃ ልሰጥህ እችላለሁ መጀመጀሪያ እኛ ሰዎች ሐሞተ ደካማዎች ነን ምክንያቱም የራሳችንን አጥብቀን መያዝ እንተውና የሰውን በቅናት ስንከተል የያዝ ነውና ያሰብነው ይላላል ስለዚህ አሁን እኔ አበበ በእርግጥ በሥራዬና ሌት ከቀን ውርጭ ብርድ ፀሐይሙቀትእንቅልፍ እረፍት ሳልል አንድ ወር ወይም አንድ ዓመት ሳይሆን የዕድሜዬን እኩል ክፍያ ባደ ረግኩት ያለ እረፍት ከፍተኛ ተጋድሎ መሆኑን ለኔ ለግሌ ግልጽ ነው ።
አዎን አንተ እንዳልከው ሰዎች የሚያስቡት አስተሳሰብ እኔ አንዴ ወይምሁለት ሦስቴ ሩጬ በማሸነፍ ያገኘሁት ሹመት ይመስላቸው ይሆናል ። ሊሆንም ይችላል ግን ከሕዝብ አንድ የተዘነጋ ነገር ያለ ይመስለኛል ። ይኸውም አንድ ሰው ሽልማትና ከፍተኛ ማዕረግ የሚሰጠው በወሬ ወይም በጉራው አይደለም ። ለራሱ ለወገኑና ለአገሩ ከፍተኛ የሚያስመሰግን ሥራ የሠራ እንደሆነ ብቻ ነው አለዚያማ ይሄ ጉረኛና በወሬ የነገሠው ሁሉ አይሾም አይሸለምም እንዴ? ወጣም ወረደም እኔ በሩጫ ብቻ ሳይሆን በአገልግሎቴም ጭምር ያገኘሁት ነው እንጂ ኬትም መጥቼ በሩጫ ያገኘሁት ብቻ አለመሆኑን አንባቢ ያን ከልብ እንዲረዱልኝ እሻለሁ በማለት መልእክቱን አስተላልፏል ።
ምንጭ
የማራቶን ጀግኖች አበበና ማሞ፣አብዱ አህመድ፣1967
ምንዳር አለው ዘውዴ ፕሮፌሰር