>

የትራምፕ (አውሮፓ) የስደት ፖሊሲ - የአባይ ፖለቲካ ስደተኞች ዕጣ ፈንታና የአርበኝነት ግዴታ

የትራምፕ (አውሮፓ) የስደት ፖሊሲ የአባይ ፖለቲካ ስደተኞች ዕጣ ፈንታና የአርበኝነት ግዴታ

ሠርጸ ሚካኤል

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ ተስፋ ሰጪ መስሎ የተጠበቀው ዴሞክራሲና ልማት ህልም ሆኖ ቀረ። ዓለም ባንክ ያበጀው የመዋቅር ማሻሸያ ማማለያም ውስጡ ሲፈተሽ ሾላ በድፍን ነበር። የቀድሞውን አምባገነን አብጠልጥሎ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አምባገነንም ጭካኔን አበርትቶ ምዝበራን፣ ሙስናን እጥፍ ድርብ አሳደገ። ሁኔታውን የተረዳው ምዕራቡ ዓለም በሩን ወከክ አድርጎ ሲከፍተው ባለሥልጣኑም ቱጃሩም፣ ወጣቱም ጉብሉም፣ ጋዜጠኛውም ወታደሩም፣ ተዋናዩም ድምጻዊውም፣ አርሶ አደሩም ዘላኑም፣ እግር ኳስ ተጫዋቹም አትሌቱም፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባሉም የፓርላማ አባሉም፣ ወዘተ፣ ለስደት ተዘጋጀ። ስደት ለምዕራቡ ዓለም ድርብ ድርብርብ የጉልበት ምንጭ ሆነ። ስኮላር ሺፕ እና ዲቪ ሳይቀሩ አዕምሮንና ጉልበትን መሳብያ ተደረጉ። በደሉ ብዙ ነው። ሆን ብሎ ግጭትን በመፍጠር ድሆች እርስ በእርስ ሲዋጉ መሳርያ ሻጮችና መድሃኒት አከፋፋዮች ይበለጽጋሉ። በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በተፈጠረው ስጋት ተሰዳጅ የሆነው ምስኪን ደግሞ ባልፈለገው ሥራ ተመድቦ የእድሜ ልክ ተበዝባዥ ይሆናል። ትላንት ቅኝ ገዥነት ዛሬ ስደት የተፈጥሮንና የሰው ኃይልን ማሟጠጫ ሁነኛ የምዝበራ ብልሃት ተደረጉ። ከግሪክና ሮማ ከቀሰሙት እውቀት በተጨማሪ ምዕራብያኖች የካፒታሊዝምን ደልዳላ መንገድ ያበጃጁ ብልሃተኞች በመሆናቸው ለአንዱ አገር እዳ የሆነው ለራሳቸው ምንዳ ያደርጉታል። ስደት የተራራን ያህል ግዙፍ የውቅያኖስ ያህል ጥልቅ ነውና ለመጻፍ እንኳን ቢሞከር ይሄ ገጽ አይበቃውምና ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመለስ።

በኢሚግራሽን እና በምራብያዊው ዴሞክራሲ እጣ ፈንታ ላይ ጥያቄ ቢያስከትልም የፕሬዚዴንት ትራምፕ የስደት ፖሊሲ ስደትን የመጨረሻ ተስፈ አድርገው የሚጠባበቁትን ግፉዓኖችን አሳዝኗል። እ..20 ጃንዋሪ2025 ዓም ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ እንደተመረጡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ መከላከል ጀመሩ። ትራምፕ ከስደት ጋር በተያያዙ በርካታ ተፈጻሚ ትዕዛዞችን በመፈረም በስደት ሥርዓቱ ላይ በርካታ ለውጦችን በማቅረብ የድንበር ማቋረጫዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠበቁ ትዕዛዝ ሰጡ። ትራምፕ ስደተኞች ለብሔራዊ ደኅንነት እና ለሕዝብ ደኅንነት ከፍተኛ ሥጋት ይፈጥራሉ የሚል እምነት ያላቸው ሲሆን ይልቁንም ስደተኞች በንጹሐን አሜሪካውያን ላይ አስጸያፊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ አንዳንዶች ደግሞ በስለላ፣ በኢኮኖሚያዊ ስለላ እና ከሽብር ጋር ለተያያዙ ተግባራት ዝግጅትን ጨምሮ በጠላትነት የተሰማሩ ናቸው የሚል ነቀፋ ሠንዝረዋል። ትራምፕ በርካታ ስደተኞች የአሜሪካን ህዝብ ልግስና አላግባብ ተጠቅመዋል ሲሉም ይወነጅላሉ። ስደተኞች በዩናይትድ ስቴትስ መገኘታቸው አሜሪካንን እና ግብር ከፋዮችን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ አስደርጓቸዋል ሲሉም አምርረው ይናገራሉ።

ስደት የጉልበትና ዓዕምሮ ምንጭ (labour and brain drain) ሆኖ ቢቆይም አሁን ደግሞ የቋንጃ እከክ ሆኖብናልሲሉ ቀኝ አክራሪዎች መናገር የጀመሩት መሳርያ የታጠቁ ሽብርተኞች በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ቻርሊ ሄብዶ ቢሮ ገብተው የ12 ሰዎችን ደም ሲያፈሱ ነው። አስቀድመው መሳርያ ያነገቱ ሰዎች ዘፈን ወደ ተዘጋጀበት አዳራሽ ድንገት በመግባት ያለልዩነት ተኩስ ከፈቱ። ብዙዎች አዳራሹን በፍጥነት በመልቀቅ ሊድኑ ቢችሉን ደርዘን ያህል ሰዎች በግፍ ተረሸኑ። እርጉዝ ሴት እመስኮት ላይ በመንጠልተል ራሷን ለማዳን ሞከረች፣ አንዳንዶች የሞቱ መስለው እወለሉ ላይ ተዘረሩ። ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነበር ፖሊሶች ደርሰው ሽብርተኞቹን ያስወገዱት። በዚያን ሠዓት 89 ሰዎች ሞተው ተገኙ። ሆላንድ ጥቃቱን አሰቃቂ (horror) ስትል አወጀች። በእርግጥ ሁኔታው አሳዛኝ ነበር። ከግድያው በኋላ የፈረንሳይ ምሁራን ሙስሊሞችን እንደ መሰረታዊ የስጋት ኃይሎች ፈረጇቸው። ቀኝ አክራሪዎችm – “መጻተኛ የመሰሉት ስደተኞች እያደር እራሳቸውን አገለሉ፣ ስደተኞች ሽብርተኞች ሆኑ፣ ወዘተ፣ እያሉ በተለያየ ርዕስ ሥር መጻፍ የጀመሩት በአውሮፓ ውስጥ ይህ ዓይነቱ ወንጀል ከተከሰተ በኋላ ነው።

ዋናውን ጉዳይ ለማንሳት ልሞክር። የምዕራብያኑ ዓለም የኤሚግሬሽን መሥሪያ ቤቶች በቀኝ አክራሪዎች ወቀሳ ሥር የወደቁ ሶስት ዓይነት የፖለቲካ ስደተኞችን አኳኋን ታዝቧል። እስኪ እንመልከታቸው።

አንደኛ – የሃገራቸው መንግሥት በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት አደጋ እንዳያደርስባቸው የሸሹ ፖለቲከኞች መኖራቸው ይታወቃል። አንዳንዶቹ ስደት የጠየቁበት አገር ጥገኝነት ከሰጣቸው በኋላ ዜግነታቸውን ሳይቀይሩ አርፈው ተቀምጠዋል። አንዳንዶች ደግሞ ዜግነታቸውን ቀይረውም ቢሆን ተቃውሟቸውን ቀጥለውበታል። ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ በለስ ሲቀናቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው ከገዥው መንግሥት ጋር ተሞዳሙደው ጥቅም ሲቃርሙ ይቆያሉ። አልመች ያላቸው ሰበባ ሰበብ ፈልገው ዳግም ዜግነት ወደሰጣቸው አገር በመመለስ ሲያበላ ሲያጠጣቸው የነበረውን መንግሥት ይወነጅላሉ። ይህ ብልጣብልጥነት ወሰን ይበጅለት ዘንድ ቀኝ አክራሪዎች አጥብቀው ይሟገታሉ።

ሁለተኛ – የሃገራቸውን መንግሥት ተቃውመው ጥገኝነት ተፈቅዶላቸው የመኖርያ ፈቃድ ካገኙ ጥቂት ዓመታት በኋላ ጥቂቶች ወደ ሃገራቸው በመመለስ ከወነጀሉት መንግሥት ጋር እጅና ጓንት በመሆን የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ያሳድዳሉ። ወደ ሃገራቸው መመለስ ከማይፈልጉት መካከል አንዳንዶች በሶስተኛ አካል በኩል ገንዘብ እየላኩ ጎጆ ሲቀይሱ አንዳንዶች ደግሞ የሃገራቸውን መንግሥት እየወነጀሉ እህት ወንድሞቻቸው፣ ዘመዶቻቸው እንዲሰደዱላቸው በየአደባባዩ ይጮሃሉ። ይህ ድርጊት ቀኝ አክራሪዎችን እጅግ አሰልችቷል።

ሶስተኛ – እትውልድ አገራቸው እያሉ በፖለቲካ ፓርቲያቸው ውስጥ ሲታገሉ ቆይተው አመቺ ጊዜ ጠብቀው የሚሰደዱ ፖለቲከኞች አሉ። ጥቂቶቹ እስኪሰደዱ ድረስ የፓርቲ ፕሮግራም ቀርጸው በግልጽ የመንግሥት ተቃዋሚ መስለው እየታዩ በስውር ደግሞ በቢዝነ መስክ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ ይቆያሉ። እነዚህ የፖለቲካ ተጽእኖ ማሳረፍ የሚችሉት ፖለቲከኞች የገዢውን ፓርቲ ዕድሜ ማራዘም በማቻላቸው ከራሱ ከገዥው መንግስት ድጎማና ጥበቃ ይደረግላቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ የፖለቲካ ነጋዴዎች ፖለቲካን የመሰደጃ ሰበብ ያደርጉታል። ቀኝ አክራሪዎች እንዲህ ዓይነቶቹ ውሸታሞች ወደ አገራቸው ዝር እንዲሉ ስለማይፈልጉ የፖለቲካ ሸማ ያጠለቁ ነጋዴ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን ይወተውታሉ።

በአውሮፓ የሚገኙ ቀኝ አክራሪዎች የስደት ፖሊሲ እንዲስተካከል ብዙ ወትውተዋል። አሁን ደግሞ የትራምፕ አስተዳደር፣ በሚያስገርም ፍጥነት፣ አዳዲስ አደናጋሪና አስገራሚ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዎችን አውጥቷል። ፖሊሲው ከጦርነት እና ረሃብ፣ እገታ እና እስር የሚሸሹ እውነተኛ ስደተኞችን መጉዳቱ ባይቀርም የነጋዴ ፖለቲከኞች ዕጣ ፈንታን ሊገታ ይችላል።

እውነት ኅያው ነች። ትራምፕ አዲስ የስደት ፖሊሲ ቀረጹም አልቀረጹም እንደ ኢትዮጵያዊ ልናውቃቸው የሚገቡ ብዙ ቁምነገሮች ነበሩ። ቀድሞ ፖለቲካ ለሕዝብ ሲባል መዋዕትን መቀበያ ቁርጠኝነት ነበር። ዛሬ ፖለቲካ የፖለቲካ ንግድ ማሳለጫ በመሆኑ የአገርን አንጡራ ገንዘብ ማሸሽያና መሰደጃ ሆኗል። ባይሰደድም እንኳን በስብሰባ ምክንያትም ወደ ውጭ የሚጓዝ ፖለቲከኛ ትምህርት ከመቅሰም ይልቅ ገንዘብ አባክኖ ይመለሳል። የጉብኝት ቪዛም በጥቁር ገበያ የተዘረዘረ ዶላር መሰብሰብያ ከሆነ ሠንብቷል። ምዕራብያኖቹ ገንዘብ ላላቸው ሰዎች ቪዛ የሚሰጡት በንጉሡና በደርግ ዘመን የተነፈጉትን ምንዛሬ ለማካካስ ሲሆን መዝባሪ ፖለቲከኞችና ደንታ ቢስ ግለሰቦች፣ አወቁም አላወቁም ተባባሪዎቻቸው ናቸው። ትክክለኛ መንግሥት ቢኖር ኖሮ ይህን መከላከሉ የሥራው ግዴታ ነበር።

ምንም እንኳን የገንዘብ ፍሰቱ (remittance) ለደሃ አገሮች የገቢ ምንጭ ቢሆንም የስደትን መቆም በእርግማን ውስጥ የተገኘ ምርቃት (blessing in disguise) አድርገን እንውሰደው። ምዕራብያውያኑ በራቸውን ከዘጉ ባለሥልጣናት ገንዘብ አያሸሹም ፖለቲከኞችም በሀገርና በሕዝብ መቀለዳቸውን ያቆማሉ። ስደት ከቆመ አባቶች እንደ አቡነ ጴጥሮስ እውነትን ያስተምራሉ፣ ይሞቱለታልም። ስደት ከቆመ ፖለቲከኞች እንደ ኢሕአፓዎች፣ መኢሶኖች እና ቅንጅቶች ቆራጥ ይሆናሉ። ስደት ከቆመ ወታደሮች እንደ አድዋና ካራማራ ብሔራዊ ድሎችን ያስመዘግባሉ። ስደት ከቆመ ማውራት መተዳደርያ ያደረጉት ገለል ብለው ማስተዋል ያላቸው ወደፊት ያመጣሉ። ፖለቲካችን መፍትሄ አልባ የሆነው ወንጀል የፈጸሙ ፖለቲከኞች የመንግስት ተቃዋሚዎች ሲሆኑ እንደ ወዳጅ በመታየታቸው ሳብያ በየስብሰባው በቀረቡ ቁጥር ምክንያታዊ ማብራርያ እና መፍትሄ(rational explanation and legal remedy) ማቅረብ አለመቻላቸው ነው። የትግል ዓላማ ዝናን መቃረምያ፣ ጭብጨባን መፈለግያ፣ እውቅና ማረጋገጫ፣ ኑሮን መደገምያ እስከሆነ ድረስ ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭነው። የድል ባለቤቶች ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የተቆራኙ ታጋዮችና አርበኞች ብቻ ናቸው።

ፖለቲካ ወቅታዊ ነው (politics is conditional)። የሁኔታዎች በፍጥነት መለዋወጥ፣ የጦርነቶች መበርታትና የምጣኔኃብት መላሸቅ ምዕራቡን ዓለም ሊያስጨንቀው ይችላል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በፊት ስደት በአንድ በኩል የሶቭየት ሕብረት ሳተላይት የሆኑ አገሮች (Soviet satellitestates) እውቅ ሰዎችን መቀምያ ሲሆን በሌላ በኩል ደግም ዓዕምሮና ጉልበት መሰብሰብያ ነበር። ነባራዊ ሁኔታው ነው ስደተኛ እምቅ የሃገር ደህንነት ስጋት ነው (potential threat to national security)ወደሚል ውንጀላ ያቀረበው። ነገሩ ቀሰ በቀስ ወዴት እንደሚያመራ ልንገነዘብ ይገባል። የዋጋ ግሽበት ሲያይል፣ የጦር መሳርያ ወጪ ሲበዛ፣ የምግብ ዋጋ ሲንር ወይንም የሃብት ማሽቆልቆል ቢከሰት ስደተኛ የተሰደደበትን አገር ለቆ እንዲወጣ ግፊት ሊደረግ ይችላል። በተጨማሪም ችግሮች በሰፉ ቁጥር በበርካታ ምክንያቶች ሳብያ ስደተኛ የቀኝ አክራሪዎች ዒላማ ሊሆኑም ይችላል። (“Go Back From Where You Came From» የሚለውን የ Sasha Polakow-Suransky መጽሃፍ ማንበብ ግንዛቤን ያስጨብታል)

ሁላችንም ነገሮችን ከወዲሁ ማስተካከል አለብን። ስደት እንዲቆም ግፍና ሰቆቃን መከላከል አለብን። ከህወሓት ወዲህ የተከሰተው ብልሹ ሥርዓት በውጭ ላሉትም ይሁን በአገር ቤት ላሉ ራስ ወዳድ ጮሌዎች የገቢ ምንጭ ሲሆን ከሕዝብ ጎን ለቆሙ ሃቀኛ ፖለቲከኞች ደግሞ እንደ ሓዋርያቶች ስቃይን መቀበያ ሆኗል። ይህ ግፍ እስከመቼ ይቀጥል። እነ ክርስትያን ታደለ፣ መስከረም አበራ፣ ታድዮስ ታንቱ፣ አባተ ቧ ያለው፣ ወዘተ፣ የ21 ክፍለ ዘመን ስቃይ ማሳያ ናቸው።

ወገኖቼ! የፖለቲካው ብኩንነት (political extravagance)ክቡር የነበረው የሃገር ፍቅር እሴትና ኩራት (virtue and pride) ገደል ከቶብናል። እርግማኑ እየቦረቦረን፣ እያሰለለን እነሆ ግማሽ ምዕት ዓመት ደፈነ። የቅኝ ገዥዎችን ምኞት ቅዠት ያደረገችው የታላቂቱ ኢትዮጵያ ልጆች በስደት ታነቅን። ግናስ ምን ማድረግ ነበረብን? በማንም መፍረድ አይቻልም። አፈር መስኮት ኖሮት አጼ ቴዎድሮስና አጼ ሚኒልክ የዛሬዪቱን ኢትዮጵያ ቢመለከቷት ኖር ሃዘናቸው እጅግ በበረታ። ያለፈው አለፈ፣ የወደፊቱ ማሳመር ብልህነት ነው። ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ ታጋዮች በተለይም የአማራ ፋኖ ኃይማኖቱ፣ አኗኗሩና ባህሉ ያስተማረውን ጨዋነት በመንተራስ የቀድሞ ሥነምግባሮችና ግብረገቦች ዳግም እንዲመለሱ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። የአማራ ፋኖ በሰበብ አስባባቡ የተወሰደውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ምጣኔኃብታዊ ብሔራዊ ጥቅሞች እቦታው መመለስ አለበት። የአማራ ፋኖ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎትና መሰርያዊ አካሄድ ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል። ስለሆነም ፋኖ የአስተዳደር ሥራዎችን ከመረከቡ በፊት ሊተገብራቸው የሚገባቸውን አገራዊና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎችን የመመርመር የአርበኝነት ግዴታ አለበት። በእርግጥ ሁሉን ነገር ታጋዮችና አርበኞች ላይ ብቻ መጣል የለብንም። የጥቁር ሕዝብ አቀፉ እንቅስቃሴ (Pan-Africanism) ፋና ወጊዋ ኢትዮጵያ ከራሷ ጥቅም ይልቅ ለአፍሪካ ጥቅም ስትታገል የቆየች አገር ብትሆንም ወሮታዋን ተነፍጋ እታች ወርዳለች። ግድ የለም – ሁሉም ይቅር፣ ልማቱም ዴሞክራሲውም ይቆይልን፣ ብቻ ቢያንስ ቢያንስ ሽንገላው ቆሞ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከህወሓት በፊት ወደ ነበረችበት አገራዊና ሉዓላዊ ቁመና እንትመለስና አንድነቷ እንዲጠገን ሁላችንም የሚቻለንን አስተዋጾ እናበርክት።

ኢትዮጵያ ለዘላልም ትኑር

Filed in: Amharic