“ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል”
አፈንዲ ሙተቂ
የአሁኑ የኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብ ከወረቀት የተሰራ ነው። በዚህ ገንዘብ ላይ “ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል” የሚል ጽሑፍ አለ። ይህ ጽሑፍ በኖቱ ላይ እንዲጻፍበት ምክንያት የሆነውን መነሻ ታውቃላችሁ? ካላወቃችሁ በአጭሩ ላውጋችሁ።
አጼ ኃይለ ስላሴ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በኢትዮጵያ ለግብይት ይውሉ የነበሩትን የማር ትሬዛ የብር (silver) ገንዘብ እና የምኒልክ ገንዘብ (ከብር፣ ከመዳብ እና ከነሐስ የተሰራ) በወረቀት ገንዘብ ለመተካት ከውሳኔ ላይ ደረሱ። በ1924 ገደማ አዲሱ የወረቀት ገንዘብ በስራ ላይ ዋለ። ይሁንና ገንዘቡ በሕዝቡ ተቀባይነት አላገኝ አለ። ሕዝቡ “የውሸት ገንዘብ ነው። እንድ ድሮው በማር ቴሬዛ እና በምኒልክ ገንዘብ ካልሆነ በወረቀት ገንዘብ አልገበያይም” በሚል ለገመ። በተለይም ገንዘቡ ከወረቀት ተሰርቶ ሳለ “ብር” (silver) ተብሎ መጠራቱ የተንኮለኞች ሴራ መሰለው። የኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጥብቅ አዋጅ ቢያወጣም ለውጡ እምብዛም ነበር።
በ1928 ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረችና የራሷን ገንዘብ በስራ ላይ አዋለች። ኢጣሊያኖች ተባረው እንግሊዞች ሲመጡ ደግሞ በቅኝ በሚገዟቸው ሀገሮች የሚሰሩትን የብረት ገንዘቦች (coins) ወደ ኢትዮጵያ አመጡ። በማር ቴሬዛ እና በኢጣሊያ ገንዘቦችም ግብይት መፈጸም ተፈቀደ።
እነዚህ ገንዘቦች በሀገሪቱ በመሥራት ላይ ሳሉ የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በ1938 ሁለተኛውን የወረቀት ገንዘብ አሳትሞ በስራ ላይ አዋለው። ነገር ግን በዚህ ጊዜም ሕዝቡ በአዲሱ የወረቀት ገንዘብ ለመገበያየት ለገመ። “አዲሱ የወረቀት ገንዘብ የውሸት ነው፣ አትቀበሉት” እየተባለ ገበያ ላይ መንቀሳቀስ አቃተው። የወረቀት ገንዘቡን ይዞ ገበያ የሚወጣ ሰው የሚቀበለው አጥቶ ከገንዘቡ ጋር ወደ ቤት ይመለስ ጀመር። በተለይ ግን የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና የውጪ ዜጎች በገንዘቡ ለኢትዮጵያ ዜጎች ክፍያ ለመፈጸም ተቸገሩ።
የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት አዋጅ አወጣ። “በእርሱ አልገበያይም፣ ገንዘቡን አልቀበልም፣ የውሸት ነው” የሚሉት ሐሰተኞች መሆናቸውን አስታወቀ። በትልልቅ ከተሞች የጎዳና ላይ ማስታወቂያዎችን ሰራ። በዚህ መንገድ የተወሰነው ሕዝብ በገንዘቡ መገበያየት ቢጀምርም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም።
የኃይለ ሥላሴ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አማካሪዎችን አፈላልጎ ቀጠረ። አማካሪዎቹ ከአጼውና ከሌሎች ባለስልጣኖች ጋር መከሩ። በአንድ ላይ ተሰብስበው በጉዳዩ ላይ ተወያዩ። በመጨረሻም ይበጃል የተባለው መፍትሔ ፈለቀ።
አዲሱ የመፍትሔ ሐሳብ በወረቀት ገንዘቡ ላይ “ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል” የሚል ዐረፍተ ነገር መጻፍ ነው። ከዚያም ዐረፍተ ነገሩ የተጻፈበት ገንዘብ የኢትዮጵያ ህጋዊ ገንዘብ ሆኖ በአዋጅ ይወጣል።
በአማካሪዎቹ ሐሳብ እና በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ይህ ዐረፍተ ነገር ሁለት ዒላማዎችን ይመታል። በመጀመሪያ የወረቀት ገንዘቡ የኢትዮጵያ ህጋዊ ገንዘብ መሆኑን ያረጋግጣል። ከእርሱ ውጪ ሌሎች ገንዘቦች የህግ ድጋፍ የላቸውም ማለት። ሁለተኛውና ትልቁ የስኬት ዒላማው ደግሞ በሀገሪቱ ግብይት የሚፈጽም ማንኛውም ሰው ገንዘቡን እንዲቀበል ያስገድዳል። “በእርሱ ግብይት አልፈጽምም፣ አልቀበልም፣ በእርሱም ክፍያ አልፈጽምም” ያለ ሰው ደግሞ በህግ መሠረት እርምጃ ይወስድበታል ማለት ነው። በዚህ ላይ ለፖሊስና ለሌሎች አስፈጻሚዎች ሙሉ ስልጣን ተሰጥቶአቸዋል።
በመጀመሪያው አካባቢ በግብይት ወቅት በዚህ “ገንዘብ አልገበያይም፣ አልቀበለውም” እና “እኔ የምከፍልህ በማር ቴሬዛ እንጂ በወረቀት አይደለም” ያሉ ብዙ ሰዎች ዘብጢያ ወርደዋል። ከዚያ በኋላ ነው የወረቀት ኖቱ ብቸኛው የኢትዮጵያ ህጋዊ ገንዘብ መሆኑ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው።
እንግዲህ ከዐረፍተ ነገሩ አመጣጥ ጀርባ ያለው ታሪክ ይህ ነው። በነገራችን ላይ ዐረፍተ ነገሩ በደርግ ዘመን “የኢትዮጵያ ህጋዊ ገንዘብ” (Legal Tender in Ethiopia) በሚል ተቀይሮ ነበር። በኢህአዴግ እና በብልጽግና ዘመን ግን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ወደሚጻፈው ዐረፍተ ነገር ተቀይሯል።