>

ሙስጠፌ እና አብዲልሃፊዝ Hard-talk ክፍል ሁለት (ሙክታሮቪች)

ሙስጠፌ እና አብዲልሃፊዝ Hard-talk

ክፍል ሁለት
(ሙክታሮቪች) 
ትናንትና ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ እና የዩኒቨርሳል ቲቪው ጋዜጠኛ አብዱልሃፊዝ ያደረጉትን ቃለመጠይቅ  ( Hard-talk !!! (ሙክታሮቪች)  አቅርቤ ነበረ። ክፍል ሁለት የሚከተለው ነው።
ጋዜጠኛ:
ክቡር ፕሬዝዳንት የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ህዝብ እራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን መብት ይገፋል። የሶማሌ ህዝብ ማንነቱ እና ባህሉን በነፃነት እንዳያራምድ እንቅፋት ይሆናል ብለው ቅሬታቸውን የሚያሰሙ አካላት አሉ። ብልፅግና ፓርቲ የተባለው እውነትም እንደተባለው ብልፅግና ለሶማሌ ህዝብ እንደሚያመጣ በምን አረጋግጣችሁ ነው የተቀላቀላችሁት?
ሙስጠፋ:
ብልፅግና ፓርቲ በምን መልኩ፣ እንዴት የሶማሌን ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደሚገፋ፣ እንዴት የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት እንደሚነጥቅ ዘርዘር አድርገው ማስረዳት ያለባቸው ብልፅግናን የሚቃወሙት ሰዎች ናቸው። ይህን ማስረዳት ያለባቸው እነሱ ናቸው።
እንግዲህ ተነጠቀ የሚባለው አንድ ነገር ቀድሞ በእጅህ ያለ ነገር ሲሆን ነው። አነሰ ተቀነሰ የሚባለው ቀድሞ ሙሉ የነበረ ነገር ነው። ሊሄድብን ነው የሚባለው ቀድሞ የነበረ ነገር ነው።
የሶማሌ ህዝብ በ28 አመት ውስጥ በሀቀኛ ዴሞክራሲ እና ነፃነት እራሱን አስተዳድሮ አያውቅም። ዴሞክራሲያዊ መንግስት አልነበረውም። እውነተኛ ፌዴራሊዝም ኖሮን አያውቅም። በህወሃት ባለስልጣናት የበላይ አዛዥነት የነበረ የሞግዚት አስተዳደር ነው የነበረው። አጋር ተብሎ የተገፋ፣ ከመሀል ሀገር የፖለቲካ ውሳኔ ውጪ ሆኖ የበይ ተመልካች እንዲሆን የተደረገ ክልል ነው። ጄኔራሎች የሚያስተዳድሩት፣ ሁሉ እየመጣ የሚዘርፈው፣ የሚገድለው እና የሚያስረው ህዝብ ነበረ በክልሉ።
በርዕዮተአለም ሳይቀር በይፋ የአርብቶአደርነት የኑሮ ዘይቤ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የማይመጥን ኋላ ቀር ስለሆነ የሶማሌ ህዝብን የሚወክል የፖለቲካ ድርጅት ወደ ኢህአዴግ ፓርቲዎች መቀላቀል አይችልም ነው በመለስ ዜናዊ የተባልነው። ይህን ውርደት ነው እራስን በራስ ማስተዳደር ነበረ የሚባለው? ይህ ነው ፌዴራሊዝም? ይህ ነው እኩልነት? ይህ ነው ዴሞክራሲ?
እኛ እንደምናምነው የሶማሌ ህዝብ የነበረው እና የሚወሰድበት መብት የለም። ያልነበረ ነገር አይቀማም። ሀቀኛ ሆኖ በፌዴራሊዝም መርህ ላይ የተመሰረተ አስተዳደር የሶማሌ ህዝብ አይቶ አያውቅም። ያላየው ስርዓት ደግሞ አይናፍቅም፣ ተቀማሁ ብሎም አያዝንም። አሁን በብልፅግና ፓርቲ መንገድ ትክክለኛውን የራስን በራስ ማስተዳደር ሀቀኛ ፌዴራሊዝም እየጀመርን ነው።
ጋዜጠኛው:
እንደ እርስዎ እምነት የሶማሌ ህዝብን መብት ብልፅግና ፓርቲ ያስከብራል ነው እያሉን ያለው?
ሙስጠፋ:
በእርግጠኝነት! አሁን በያዝነው መንገድ የሶማሌን ህዝብ ወደ መካከለኛ የሀገሪቱ ፖለቲካ አምጥተን መብቱን እናስከብራለን። በፍትሃዊነት የድርሻችንን እንጠይቃለን። ብልፅግናን የተቀላቀልነው ሶማሌ ሆነን ነው። ባህላችን፣ እምነታችንን፣ እሴታችንን ይዘን ነው ወደ ብልፅግና የገባነው።
ከዚህ ቀደም ወደ መሀል ፖለቲካ መግባት አለብን፣ ተገልለናል፣ ወደ ዳር ተገፍተናል እያልን ስናኮርፍ ነበረ። አሁን እድሉን ስናገኝ ወደ ኋላ ማለት የለብንም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ መንገድ ተዋውቋል። ይህን መንገድ እንሞክረዋለን።
ተቃዋሚዎቻችን ግን ለምን ብልፅግና የህዝቡን መብት ይገፋል እንደሚሉ እነሱን መጠየቅ ነው። ስትጠይቃቸውም፣ ለህዝቡ የሚያስቀምጡለትን አማራጭንም አብረህ ጠይቃቸው። አማራጫቸው ትናንት ሲገላቸው፣ ሲያሳድዳቸው እና በፌክ ፌዴራሊዝም ሲያታልላቸው የነበረውን የህወሓት መንገድ አይነት እንደማይሆን እምነት አለኝ። ብልፅግና መብትን ይገፋል የሚሉት አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም መብትን በመግፈፍ የሚታወቁ እንደተነቃባቸው እንኳን አውቀው ትንሽም የማያፍሩት ናቸው።
ጋዜጠኛ:
እንግዲህ ይህን ጉዳይ ህዝቡ፣ እንዲሁም ብልፅግናን የሚቃወሙት ሰዎች ቅሬታቸው ከምን እንደሆነ ለእነሱ የምተወው ይሆናል።
ወደ ሌላ ጥያቄ ልለፍ።
በክልሉ ቅድም እርስዎም እንደጠቀሱት ከፍተኛ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። ህዝቡ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በዚህ በኩል የርስዎ አስተዳደር ዳግሞ የህዝቡ ጉዳት እና ጉዳት ባደረሱት አካላት መካከል እርቅና መግባባት እንዲኖር አስፈላጊ ነው። ለተፈፀሙት ወንጀሎች ፍትህ የሚፈልግ ህብረተሰብም አለ። እንዲሁም ይህ ግፍ ለደረሰባቸው ግለሰቦች ከጉዳታቸው እንዲያገግሙም ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የተሳካላችሁ ጉዳይ ካለ እና እክል የገጠማችሁ ነገር ካለም እባክዎ ይንገሩን።
ሙስጠፋ:
አንተም እንደምታውቀው የደረሰው ግፍና መከራ በጣም ከሚታሰበው በላይ ሰፊ እና በተወሳሰበ ደረጃ የተተገበረ፣ በመንግስት ደረጃ በጣም በጥንቃቄ ታቅዶበት የተፈፀመ ወንጀል ነው።
ለረጅም ጊዜ የተካሄደም እንደሆነ መረሳት የለበትም። ሁሉንም ጉዳይ ከስርመሰረቱ አጥርቶ ለማወቅ እና መረጃ ለመሰብሰብ በዚህ በአጭር ጊዜ ሊያልቅ የሚችል አይደለም። ፍትህ የማስገኘቱ ስራ አሁንም እየተሰራ ያለ ነው። ማስረጃዎችን በዶክሜንት ደረጃ የማጥራት ስራ ጊዜ የሚፈልግ ነው። ምክንያቱም ፍትህን ከበቀል መለየት አለብን። በጥድፊያ የሚሰራ ነገር ስህተት ሊኖረው ይችላል።
በሌላ በኩል ግን የዚህ ግፍና ወንጀል ሰለባ የሆኑትን ለመደገፍ ጥረት አድርገናል። ማህበር መስርተው እንዲንቀሳቀሱ፣ በኢኮኖሚ በምንችለው ደረጃ ደግፈናል። የጤና መቃወስ የገጠማቸውን አሳክመናል። ሆኖም የደረሰው ጉዳት በጣም አሰቃቂ ስለነበረ እውነት ለመናገር ሁሉን ነገር ብናደርግ እንኳ ጠባሳውን ማሻር አንችልም። ከባድ ስቃይ ነው የተፈፀመባቸው።
በርካታ ነገሮችን ሞክረናል። ሆኖም አጥጋቢ እንዳልሆነ ግን አምናለሁ።
ጋዜጠኛ
መልካም። ይህን ግፍ ሲቃወም ለዚህም ሲታገሉ የነበሩ ድርጅቶች ነበሩ። ስርዓቱ በርካታ በደል አድርሶባቸው የነበረ ለህዝባቸው የታገሉ አሉ። ከነዚህም ውስጥ ነፃ አውጪ ግንባር የነበረውና የምዕራብ ሶማሌ ነፃ አውጪ ግንባር በመባል የሚታወቀው ድርጅት እና በእርስዎ አስተዳደር መካከል አለመግባባት እንዳለ ይነገራል። የፀባችሁ መንስዔ ምንድነው?
ሙስጠፋ
በእኛ እና በምዕራብ ሶማሊ ነፃ አውጪ ግንባር በሚባል ድርጅት መካከል የተፈጠረ ችግር የለም። ምክንያቱም በዚህ ስም እኛ የምናውቀው ድርጅት የለም። ከሌለ ድርጅት ጋር ደግሞ ልንጋጭ አንችልም።
ጋዜጠኛ:
በሌላ መንገድ ላስቀምጠው ጥያቄዬን። ከአማፂ ግንባርነት ወደ ፖለቲካዊ ፓርቲነት የተሸጋገረ አካል ጋር ስምምነት አድርጋችሁ ወደ ሀገር ገብቷል። ስምምነታችሁ ምን ነበረ?
ሙስጠፋ:
ከማን ጋር ነው ስምምነት የፈጠርነው? አንተ ስሙን የጠቀስከው ድርጅት ጋር ስምምነት አልፈጠርንም። በዚህ ስም የተደራደርነው አካል የለም እያልኩህ ነው።
ጋዜጠኛው
ኤርትራ ላይ ተደራድራችሁ ስምምነት ፈፅማችሁ ወደ ሀገር የገባ ድርጅት እኮ አለ ክብር ፕሬዝዳንት
ሙስጠፋ:
አንተ በገልፅከው ስም የሚጠራ አካል አይደለማ! ከማን ጋር እንደተደራደርን በትክክለኛ ስሙ ጠርተህ ጠይቀኝ እመልሳለሁ።
ጋዜጠኛ
ከግንባሩ ጋር አልተደራደርንም; እያሉኝ ነው?
ሙስጠፋ:
የትኛው ግንባር?
ጋዜጠኛው
ONLF የሚባለው ግንባር
ሙስጠፋ:
ፊደሎቹ የሚወክሉትን ቃላት ዘርዝርልኝ እስቲ
ጋዜጠኛ:
ምኑን ነው የምዘረዝረው ገለፅኩት እኮ
ሙስጠፋ:
እኔ እኮ ለመጠየቅ የፈለኩት አንተን ይህ በምህፃረ ቃል ያቀረብክልኝ ድርጅት ስሙ ማን ይባላል? ሙሉ ስሙን ጥቀስልኝ እና መልሱን ልስጥህ።
ጋዜጠኛ
ክቡር ፕሬዝዳንት እያወራሁ ያለሁት በስፋት ስለሚታወቅ ግንባር ነው። በዚህ ጊዜዎን ማባከን አልፈልግም። ግንባሩ ስሙ ምንም ይባል ምን ከመንግስት ጋር ስምምነት ፈፅሞ ወደ ፖለቲካ የገባ ድርጅት አለ። እኔም እርሰዎም እናውቀዋለን። የተስማማችሁት በምን ላይ ነው። አሁንስ ምን ችግር ተከሰተ? እንደሚሰማው ስልጣኖን ሊወስድ እንደሚችል ሰግተው ያልፈፀሙትን ወንጀል ፈፅመዋል እያሉ በሀሰት እንደሚከሷቸው ይነገራል። ስለዚህ ጉዳይ ሊመልሱልኝ ይችላሉ?
ሙስጠፋ
አንተ በምህፃረ ቃል ብቻ የጠቀስከው ድርጅት ሙሉ ስሙን መጥቀስ ካልፈለክ እኔ ልንገርህ።
Ogaden National Libration Front በመባል የሚጠራ ድርጅት ነው። ጥያቄህን የድርጅቱን ስም ጠቅሰህ ነው መጠየቅ ያለብህ።
ጥያቄህን የጀመርከው የምዕራብ ሶማሊያ ነፃ አውጪ ግንባር ብለህ ነው። በዚህ ስም የሚታወቅ የፖለቲካ ድርጅት ደግሞ የለም። በሌለ ድርጅት ላይ ደግሞ አስተያየት መሰጥት የለብኝ።
ለማለት የፈለከው እንደመሰለኝ።
WSLF በመባል ይታወቅ የነበረ ድርጅት ነው። West Somalia Liberation Front ይባል የነበረው ድርጅት ህልውናው 1980s ያከተመ ድርጅት ነው። ስለዚህ ስለዚህ ድርጅት የታሪክ ሰዎችን መጠየቅ እንጂ እኔን ስምምነት ፈፅመሀል ብለህ መጠየቅ የለብህም። ይህን ዝግጅት በርካታ ሰው ያየዋል። እኔ እና አንተ ብናውቀውም ሌላውን ሊያደናግር ስለሚችል መጠንቀቅ አለብን።
ጋዜጠኛ
ተቀብዬኣለሁ
ሙስጠፋ:
የሶማሌ ህዝብ እያዳመጠን ያለ በመሆኑ እውነቱን አፍረጥርጠን መነጋገር አለብን። ምዕራብ ሶማሌ በሚል የሚታወቅ ድርጅት ሳይሆን ከኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ ድርጅት ተብሎ ከሚታወቅ ድርጅት ጋር ተደራድረን በብዙ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል።
ይህ የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጪ የሚለውን ስያሜያቸውን ወደ አጠቃላይ የክልሉ የሶማሌ ህዝብ ሊወክል በሚችል ስም በመተካት ለክልሉ ህዝብ ሁሉ ወካይ ስም በራሳቸው ምርጫ እንዲሰይሙ አጠቃላይ መግባባት ነበረን።
ዘርዘር ለማድረግ
በመጀመሪያ ደረጃ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ፓርቲ ሆነው እንዲታገሉ እና አሁን የተገኘውን እድል በሰላማዊ መንገድ እንዲጠቀሙበት
የታጣቂ ወታደሮቻቸው ጉዳይን የምንፈታበት እና በትጥቅ ትግል ላይ ከመኖራቸው አንፃር የእነሱን ጉዳይ ማኔጅ የሚደረግበት መንገድን
በእኛ እና በእነሱ መካከል የፖለቲካ ውድድር የሚካሄድ በመሆኑ ስለዚህ ጉዳይ የተግባባንበትን ነጥቦችም አሉ
እኛ ቃል የገባነውን አደርገናል። በሞቀ እና በደመቀ ሁኔታ ተቀበ ለናቸዋል። ለአቀባበሉ እና ለወታደሮቹ መቋቋሚያ ከ5 ሚሊየን ብር ያህል አውጥተን መልካም አቀባበል አሳይተናል። ይህ ሁሉም ህዝብ የሚያስታውሰው ነው።
እንግዲህ ወደ ፖለቲካው ውድድር ሀሰብን ወደ መሸጥ ነው የተገባው። በዚህም አንዱ የሌላውን ሀሳብ ፍሬ ያለው ነው ወይስ የለውም፣ ያስኬዳል ወይስ አያስኬድም ወደ የሚል ትችት መግባት ያው የፖለቲካው አንድ አካል ነው የሚሆነው። ይህ የሀሳብ ትግል ነው። ከተከፉም በዚህ ነው እንጂ በምንም ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም።
ጋዜጠኛ:
እርስዎ ድርጅቱ ወንጀለኛ እንደሆነ፣ ደም ሲያፈስ እንደነበረ አንስተው የተናገሩበት አጋጣሚ የለም?
ሙስጠፋ:
እንደዚያ ብዬ አላውቅም።
ጋዜጠኛ
ይህ ድርጅት የፖለቲካ ስልጣን ሊይዝ ነው ከእርስዎ ጋር የሚወዳደረው። ያለእስርና ወከባ እንዲወዳደር ፍቃደኛ ነዎት
ሙስጠፋ:
መፍቀድ ብቻ አይደለም extra mile ሄደን በፖለቲካ ነፃ ውድድር እስከፈቀደልን ድረስ ፍቃደኝነታችንን አሳይተናል። ለዚህም ሽማግሌዎች ምስክር ናቸው። ውድድሩንም የሀገር ሽማግሌዎች እንዲታዘቡት የሚያስችል አሰራር ሁሉ ለመዘርጋት ተስማምተናል። በውድድር ለማሸነፍ ነው እቅዳችን።
ጋዜጠኛ:
ቅድም ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ የህግ የበላይነት እና ስለሰብዓዊ መብት ብዙ ነግረውኛል። ሆኖም በክልሉ አሁንም በፖለቲካ ሳቢያ የሚታሰሩ ሰዎች አሉ። እስቲ በቅርቡ የታሰሩ አካላት ለምን እንደታሰሩ ሊነግሩኝ ይችላሉ?
ሙስጠፋ:
በጥቅሉ አትጠይቀኝ። የታሰረ ሰው አለ የምትለው ማን ነው? በስም ጠቅሰህ የታሰረን ሰው ጥቀስልኝ
ጋዜጠኛ
በርካታ ልጠቅስ እችላለሁ። በቅርቡ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የታሰረ የርስዎ የፕሮቶኮል ሀላፊ አለ። አብዱል ቃድር ይባላል።
እንዲሁ ሌሎችም አሉ። ክቡር ፕሬዝዳንት በቅርብ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ምንድነው መነሻው? ብዙ ስኬት ነግረውኝ አሁን ግን ክልሉ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለህዝብ ሊገልፁ ይችላሉ?
ሙስጠፋ
እየውልህ የሆነው ነገር እንዲህ ነው ……
እይሳ!? አብረን ነን!
Filed in: Amharic