>

እንቁጣጣሽ! ኑ አብረን እንጸጸት...!!!  (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

እንቁጣጣሽ! ኑ አብረን እንጸጸት…!!!

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

.


እነሆ ሜዳው አደይ ለበሰ፡፡ አደይ የተስፋ ጉዝጓዝ ነው፡፡ ልቦናዬን ፈተሸኩት፤ ቄጠማ አልተጎዘጎዘበትም፤ በአደይ አልተንቆጠቆጠም፡፡ የጸጸት ደለል ተኝቶበታል፡፡
.
በብሄርና በፖለቲካ ተቧድነን አደይ ሳይቀጥፉ ስለቀጠፍናቸው ህጻናት እጸጸታለሁ፤ የፖለቲካ ሴራ ሰለባ ስለሆነው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ እጸጸታለሁ፤ በወጡበት ስለቀሩት የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እጸጸታለሁ፤ በመላው ሀገሪቱ ስለሞቱ ንጹሀን እጸጸታለሁ፤ በሻሸመኔና በመላው ሀገሪቱ ቄጠማ ጎዝጉዘው ሳይሆን፣ የአመድ ክምር ሆነው አዲስ አመት ለጠባባቸው ቤቶች እጸጸታለሁ፤ ለድንኳንና ለመጠለያ ስለዳረግናቸው ወገኖቼ እጸጸታለሁ፤ . . . . . .
.
ወገኖቼ በገዛ ወገናቸው ስለደረሰባቸው የማይገባ ድርጊት ሁሉ እጸጸታለሁ፡፡ የጸጸት ደለል በልቤ ተኝቷል፡፡ እንቁጣጣሽ! ኑ እንደሀገር አብረን እንጸጸት፡፡ ከጸጸት ደለል ላይ አደይ ያቆጠቁጣል፡፡ በጨለማው የተጸጸተ ወደብርሀን ይመለከታል፡፡
Filed in: Amharic