>
5:13 pm - Monday April 19, 5971

ያብይ አሕመድ ኦነግ ሸኔ እና የሂትለር ኤስ ኤስ (መስፍን አረጋ)

ያብይ አሕመድ ኦነግ ሸኔ እና የሂትለር ኤስ ኤስ

መስፍን አረጋ


ዐብይ አህመድ ስልጣኔን ለመንካት ብታስቡ መቶ ሺወች ባንድ ጀንበር ይታረዳሉ በማለት በግለጽ ዝቷል፡፡  ልብ በሉ፡፡  ዐብይ አህመድ ያለው ተቃውሞ ይነሳል ወይም ሁከት ይፈጠራል ሳይሆን፣ መቶ ሺወች ይታረዳሉ ነው፡፡  ይህን ያለው ደግሞ ይታረዳሉ የሚለውን ዘግናኝ ቃል ካንደበቱ ሲያወጣ ምንም ሳይሰቀጥጠውና፣ ዛቻው እንደሚፈጸም ሙሉ ርግጠኝነቱን በሚያመላክት ሁኔታ ፍጹም በተረጋጋ መንፈስ ነበር፡፡  

ዐብይ አህመድ በርግጠኝነት መንፈስ ይህን ዓይነት ሰቅጣጭ ዛቻ ሊዝት የሚችለው ደግሞ፣ በቀጥታ የሚያዘውና ትዛዙን ለመቀበል በተጠንቀቅ የሚጠባበቅ፣ እረድ ያለውን ሁሉ ለማረድ ቅንጣት የማያቅማማ ተወርዋሪ አራጅ ሠራዊት አዘጋጅቶ ካስቀመጠ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ነገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይበልጥና ይበልጥ ግልጽ እየሆኑ እንደመጡት ደግሞ፣ ይህ የአብይ አሕመድ ተወርዋሪ አራጅ ሠራዊት ሌላ ማንም ሳይሆን፣ ራሱ ዐብይ አሕመድ ኦነግ ሸኔ የሚለው፣ የዐብይ አሕመድ ክብርዘብ (republican guards) የታጠቀውን ዘመናዊ መሣርያ እንዲታጠቅ የተደረገው ጨፍጫፊ ሠራዊት ነው፡፡

የዐብይ አሕመድ ኦነግ ሸኔ ሚና ከኤዶልፍ ሂትለር (Adolf Hitler) ኤስ ኤስ (Shutzstaffel, SS) ሚና ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ ኦነግ ሸኔን ፈጥሮ የሚጠቀመበት መንገድ፣ ኤዶልፍ ሂትለር ኤስ ኤስን ፈጥሮ በሚጠቀምበት መንገድ ነው፡፡  

ኤዶልፍ ሂትለር ታላላቅ የጀርመን ጦር መሪወችን በተለያዩ ምክኒያቶች ገድሎ፣ አባሮና በጡረታ አሰናብቶ፣ በምትካቸው ዊሊያም ካይትልን (Wilhelm Keitel) የመሳሰሉ፣ በናዚ አስተሳሰብ የሰከሩ፣ ሲጠራቸው አቤት፣ ሲልካቸው ወዴት የሚሉ አሸርጋጆችን (yes men) በመሾም፣ የጀርመንን መከላከያ ሠራዊት (Wehrmacht) የናዚ የመስፋፋት አጀንዳ  አስፈጻሚ የናዚ ሠራዊት አደረገው፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ የጀርመን ሕዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛለት ሽበር ለመልቀቅ፣ ጀርመናዊ ተቃዋሚወቹን ለመረሸንና፣ በይሁዳወች ላይ የዘር ጭፍጨፋ ለማካሄድ ባረመኔነቱ ወደር የሌለውን የኤስ ኤስ ኢመደበኛ ሠራዊት (paramilitary force) መሠረተ፡፡  

ኦነጋዊው ኦቦ ዐብይ አሕመድ ደግሞ ጀነራል ሰዓረን በማስገደል እሱ ራሱ ጠቅላይ አዛዥ በሆነበት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ብርሃኑ ጁላን ኢታማዦር ሹም፣ ቀንዓ ያደታን መከላከያ ሚኒስትር፣ ይልማ መርዳሳን አየር ኃይል አዛዥ በማድረግ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በኦነጋውያን ቁጥጥር ሥር አውሎ፣ የኦሮሙማን የመስፋፋት አጀንዳ የሚያስፈጽም የኦሮሙማ መደበኛ ሠራዊት አድርጎታል፡፡  ይህ የኦሮሙማ መደበኛ ሠራዊት የኦሮሙማን የመስፋፋት አጀንዳ የሚያስፈጽመው ደግሞ ኦነግ ሸኔ ከሚባለው የኦሮሙማ ኢመደበኛ ሠራዊት ጋር እየተቀናበረ የተለያዩ ዘዴወችን በመጠቀም ነው፡፡  ከነዚህ ዘዴወች ውስጥ ዋና ዋናወቹ የሚከተሉት ሦስቱ ናቸው፡፡

አንደኛው ዘዴ የሚያገለግለው የኦሮሙማን አገር አጥፊ አጀንዳ በጽኑ የሚቃወሙትን፣ ባንኮችን አላስዘርፍ፣ ጌድኦወችን አላፈናቅል፣ አማሮችን አላሳርድ የሚተሉትን አገር ወዳድ ኦሮሞወችን ለማስወገድ ነው፡፡  በዚህ ዘዴ መሠረት አገር ወዳድ ኦሮሞወች ባውራ ጎዳና ላይ በጠራራ ፀሐይ እየተረሸኑ፣ ለሌሎች አገር ወዳድ ኦሮሞወች መቀጣጫ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡  አያሌ ኦሮሞወች በተለያዩ የወለጋ ከተሞች ውስጥ ባደባባይ የተረሸኑት በዚህ ዘዴ መሠረት ነው፡፡      

ሁለተኛው ዘዴ የሚያገለግለው ኦሮምያ የሚባለውን ክልል ካማሮች ለማጽዳት ነው፡፡  በዚህ ዘዴ መሠረት የኦሮሙማ መደበኛ ሠራዊት አማሮች በብዛት በሚገኙባቸው ቀበሌወች ገብቶ በመስፈር አማሮች መከላከያ አለልን ብለው እንዲዘናጉ ካደረጋቸው በኋላ፣ በድንገት ለቆ ይወጣል፡፡  እሱ በድንገት ለቆ ሲወጣ ደግሞ የኦሮሙማ ኢመደበኛ ሠራዊት (ማለትም ኦነግ ሸኔ) እግር በግር ተከትሎ ይገባና የተዘናጉትን አማሮች ሴት፣ ወንድ፣ ሕፃን፣ አረጋዊ ሳይል በገጀራ ይቆራርጣቸዋል፡፡  የተጨፈጨፉት ይጨፈጨፉና ሸሽተው ጫካ የገቡት ደግሞ በረሐብ ያልቃሉ፡፡  ባቅራቢያ የሚገኙ አማሮች ደግሞ በጭፍጨፋው ዘግናኝነት በመሸበር ማቄን፣ ጨርቄን ሳይሉ ጣጥለው ይጠፋሉ፡፡ ቀበሌውና አቅራቢያወቹም ካማራ ይጸዳሉ፡፡  

ሦስተኛው ዘዴ የሚያገለግለው በሌሎቹ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ መሬቶችን ወደ ኦሮምያ ለማጠቃለል ነው፡፡  በዚህ ዘዴ መሠረት አነግ ሸኔ (መከላከያ ከጀርባው ሁኖ በከባድ መሣርያ ከፍተኛ እገዛ እያደረገለት) ወደተወሰነ ቀጠና በተደጋጋሚ እየገባ ጅምላ ጭፍጨፋ እያካሄደ ከፍተኛ መፈናቀልን ያስከትላል፡፡  ዐብይ አህመድ ደግሞ ጭፍጨፋውና መፈናቀሉን ሰበብ አድርጎ በኦነጋዊ ጀነራል የሚመራ ኦነጋዊ ኮማንድ ፖስት ያቋቁምና፣ የቀጠናውን አስተዳደር ሙሉ በሙሉ በኦነጋውያን ቁጥጥር ሥር ያደርገዋል፡፡  በቀጠናው ውስጥ የተቋቋመው ኦነጋዊ ኮማንድ ፖስትና ኦነጋዊ አስተዳደር ደግሞ ከጭፍጨፋውና ከመፈናቀሉ የተረፉትን አማሮች በሽብርተኝነትና በሌሎች ምክኒያቶች እየነቀለ በምትካቸው ኦሮሞወችን በመትከል የሕዝብ አሰፋፈርን ቀይሮ ቀጠናውን የኦሮምያ አካል ያደርገዋል፡፡  በመተከል የተከናወነው ይሄው ነው፡፡  በሰሜን ሸዋ የተቋቋመው በቀንደኛ ኦነጋውያን የሚመራው ኦነጋዊ ኮፓንድ ፖስት ደግሞ ብቸኛ ዓላማው ሰሜን ሸዋን ሰሜን ኦሮምያ ማድረግ ነው፡፡ 

ሂትለር ኤሰ ኤስን የመሠረተው፣ ውድቀታቸውን ሁሉ በይሁዳወች እያሳበቡ በይሁዳ ጥላቻ የተመረዙ እርነስት ሮምን (Ernst Rohm) የመሳሰሉ ውድቀታም (loser) ወታደሮችን በማሰባሰብ ነበር፡፡  ዐብይ አህመድ ደግሞ የኦነግ ሸኔን አስኳል ሊፈጥር የሚችለው፣ በኤርትራ በርሓ የሚሰቃዩትን ስቃይ በፀራማራ ትርክት እንዲያስታግሱ ይደረጉ ከነበሩት፣ ትጥቃቸውን ሳይፈቱ እንዲገቡ ካደረጋቸው የኦነግ ወታደሮች ውስጥ፣ ይበልጥ ጽንፈኛ የሆኑትን በመምረጥ ነው፡፡   

የይሁዳ ዋና ጠላት ናዚው ሂትለር እንደነበር ሁሉ፣ ያማራ ዋና ጠላት ኦነጉ ዐብይ አሕመድ ነው፡፡  ኦቦ ዐብይ አሕመድ የጭቆናን ምንነት በቅጡ ሊረዳ በማይችልበት ለጋ እድሜው “ያማራ ጨቋኞችን” ለመታገል ጫካ ገብቶ የወያኔን ጡት እየጠባ ባማራ ጥላቻ ተመርዞና ተሰቅዞ ያደገ፣ ለስልጣን ያበቃውን ብአዴንን እንደ መጋዣ እየጋለበ አማራን በመረጋገጥ የሚጨፈላልቅ የኦሮሙማ መለስ ዜናዊ ነው፡፡  የፀረኦሮሙማ ትግል ዋና ዒላማ መሆን ያለበትም ይሄው ዐብይ አሕመድ ነው፣ የወያኔ ሞተር መለስ ዜናዊ እንደነበር፣ የኦሮሙማ ሞተር ዐብይ አሕመድ ነውና፡፡  መለስ ዜናዊ ያደርገው እንደነበረው፣ ብአዴንን በድን አድርጎ አማራን ማድበን የሚችል ኦነጋዊ አንድ ብቻ ሲሆን፣ እሱም በማኪያቬሊ (Machiavelli) ሤራ የተካነው፣ ሲዞሩበት እየትጥመለመለ ሲዞሩለት የሚናደፈው እፉኝቱ ዐብይ አሕመድ ነው፡፡    

 

መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com                  

Filed in: Amharic