>
5:21 pm - Thursday July 20, 2693

እውነተኛ ጸሎት እንደ ስንቅና ትጥቅ ለወንድሜ ጎዳና ያዕቆብ (ከይኄይስ እውነቱ)

 

እውነተኛ ጸሎት እንደ ስንቅና ትጥቅ

ከይኄይስ እውነቱ

⇐ ለወንድሜ ጎዳና ያዕቆብ 


‹‹ ሰላም ከአድሎ በፀዳ ፍትህ እንጂ በፀሎት አይመጣም::››በቅርቡ ‹‹

ችግራችን መዋቅራዊ ነው ስንል በምክንያት ነው…!!! (ጎዳና ያእቆብ)

…›› በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ አቅርበህ አንብቤአለሁ፡፡ ላገርና ለሕዝብ በመቆረቆር ስሜት የምታቀርባቸውን ጽሑፎች በአብዛኛው ለማንበብ ጥረት አደርጋለሁ፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊም ከቅርቡ ትውልድም ሰዎች መኖራቸው በአገሬ ተስፋ እንዳልቆርጥ ልቤም በተስፋ እንዲሞላ አድርጎኛል፡፡ የጽሑፉን መልእክት በአመዛኙ የምጋራው ነው፡፡ የተናገርህበትን ዓውድና ስሜትህን ብረዳም በመግቢያዬ ላይ በቀይ ያቀለምሁት አገላለጽህ ላይ ግን ተዐቅቦ (reservation) አለኝ፡፡ የአስተያየቴም ዓላማ ከቅን ልቦና የመነጨና ጸጕር ስንጠቃ እንዳልሆነም ትረዳኛለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ፈረንሳዮች ልዩነት (የሃሳብ) ለዘላለም ይኑር እንደሚሉት በዚህ ጽሑፍ ያሰፈርሁት አስተያየት የሚያንፀባርቀው የሃሳብ መለያየትንም ከሆነ በሚገባ አከብራለሁ፡፡

ደጋግሜ እንደምናገረው ላለፉት ሠላሳ አንድ ዓመታት ኢትዮጵያ አገራችን ላይ ከሠለጠነውና ማኅደረ ከይሲ ከሆነው ኢሕአዴግ ከሚባል የአጋንንት ስብስብ የምጠብቀውም የምጠይቀውም ነገር የለኝም፡፡ ይሄ የአጋንንት ማኅበር በሠለጠነ መንገድ በንግግር/ውይይት/ድርድር እንደማያምን እስኪታክተን አይተነዋል፡፡ ጊዜያዊ ፋታ ለማግኘት ወይም በደም የተጨማለቀ ሥልጣኑ አደጋ ላይ ወድቆብኛል ብሎ ሲያምን ለስልትነት ከሚጠቀምበት በስተቀር ይህ የጥፋት ቡድን በሃሳብ ፍትጊያና የበላይነት የሚያምን አይደለም፡፡ አገራችንና ሕዝባችን በአውዳሚ ጦርነት እንድትታመሰ እያደረገ፣ በደናቁርት ካድሬዎቹ አማካይነነት ዲፕሎማሲያዊ/ዓለም አቀፍ ግንኙነታችን አበላሽቶ፤ ጎን ለጎን ደግሞ ሰላማዊ ሕዝብን በኦነጋዊ ኃይሉ እየገደለና እያፈናቀለ፤ በመንግሥታዊ ንቅዘትና ዝርፊያ ተጠምዶና አገዛዝ ሠራሽ የኢኮኖሚ ቀውስ ፈጥሮ ሕዝባችንን በረሃብ አለንጋ እየገረፈ ይገኛል፡፡ 

ያለፉት ሦስት የግፍና ሰቈቃ ዓመታት ሊመጣ ያለውን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው፡፡ አገዛዙ በዚህ አያያዙ መጨረሻው ውድቀት ቢሆንም የግብር አባቱ ወያኔን ጨምሮ በየስርቻው በፈለፈላቸው፣ ሀገር-አከል ግዛት ሸንሽኖ በሰጣቸውና ብረት እንዲያነግቱ ባደረጋቸው ሀገር-ጠል ጐሠኞች ምክንያት ሀገር አልባ እንዳያደርገን ከፍተኛ ሥጋት አለ፡፡ እንደሚታወቀው ኦነጋዊው ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ከሆነው ወያኔ ጋር የዓላማ፣ የርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ ልዩነት የለውም፡፡ የተንኮታኮተውን ወያኔ ‹‹በተናጠል ተኩስ ማቆም›› ሽፋን እንዲያንሠራራና ሰሜነኞችን በሳቦታዥ በተተበተበ ጦርነት እንዲፋጁ የሚያደርገው እንደለመደው ከቀውስ አተርፋለሁ በሚል ስሌት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የሥልጣን ፍትወት ዐቅሉን ያሳጣው ዐቢይ፣ ኦነጋዊና አድርባይ መንጋው ወያኔን የመርገም የሞራል ብቃት የላቸውም፡፡ ከወያኔ ጋር ያላቸው ብቸኛ ጠብ ሥልጣን ነውና፡፡ አገር አጥፊውን የደደቢት ‹ሰነድ›፣ ይህም ሰነድ የፈጠረው አገር አፍራሽ የጐሣ ፖለቲካ፣ ‹ክልል› የተባለ ባንቱስታናዊ የአፓርታይድ መዋቅር፣ ሕገ አራዊት የሠለጠነበት ፍትሕ አልባ ሥርዓት፣ ሥር የሰደደ ‹መንግሥታዊ› ንቅዘት፣ አገርን ያዋረደ በደናቁርት ካድሬዎች የሚመራ ዲፕሎማሲ፣ ከችሎታና ብቃት የፀዳ ቢሮክራሲ፣ ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ለዝርፊያ÷ሕዝቧን ለባርነት ያመቻቸ የዘረኝነት ሥርዓት ወዘተ. በማስፈኑ ረገድ የከይሲው ኢሕአዴግ አዋልድ የሆኑት አጋንንታዊ ኃይሎች መካከል የተረኝነት ጉዳይ ካልሆነ በቀር ልዩነት የለም፡፡  

በእኔ ትሁት እምነት ኢሕአዴግ የሚባል የኢትዮጵያ ደዌ ከሥሩ ተነቅሎ እንዲጠፋ ሰላማዊ የሕዝባዊ ትግል የግድ ይመስለኛል፡፡ ያልተደራጀ ሕዝብ የአገዛዞች መጫወቻ ከመሆን አያልፍም፡፡ ከ3 ዓመታት በፊት የተደረገው ያልተደራጀ ሕዝባዊ ዓመፃ በከይሲው ድርጅት አባላት የተጠለፈበትም ምክንያት ሌላ አይደለም፡፡ ያልተደራጀ ሕዝብ የመንጋነት ባሕርይ ያጠቃዋል፡፡ ለተረኛ አገዛዞች የመጋለጥ ዕድሉም ከፍተኛ ነው፡፡ 

ንግባእኬ ኀበ ቀዳሚት ነገር (ወደ ቀዳሚ ነገሬ ልመለስና) እንዲሉ አበው ወደተነሣሁበት ርእሰ ጉዳይ ስመለስ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የጸናችው በደጎቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን ጸሎት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖተኛ ነዪ ባዩ በዝቶ መንፈሳዊነቱ ቢነጥፍም ሥጋዊ ደማዊ ፍጡር ‹ሰው› ጠፋ ብሎ ተስፋ በቈረጠበት ሰዓት እግዚአብሔር ደጋግና ከደመና በታች የማይቀር እውነተኛ ጸሎት የሚያደርጉ ሰዎች አሉት፡፡ ጠላት በመጣበት ጊዜ እንኳን እግዚአብሔርን ስንቅና ትጥቅ/ኃይል አድርጎ የሚዘምት ሕዝብ የነበረበት አገር መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡ እግዚአብሔርን ስንቅና ትጥቅ የማድረግ አንዱ መገለጫው ደግሞ ጸሎት ነው፡፡ ለዚህ ዋቢ እንዲሆነኝ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅስና በአገርና በግል ሕይወት የተፈጸሙ እውነተኛ ታሪኮችን እንድተርክልህ የምትፈልግም አይደለህም፡፡ ቦታውም አይደለም፡፡ በርግጥ እውነተኛ ፍትሕ ሰላምን ለማግኘት ዐቢይ አላባ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ የሰላም እና እውነተኛ ፍትሕ እና ሰላም ባለቤት ደግሞ ፈጣሪ እንደሆነ ሁሉም እንደየ ቤተ-እምነቱ ያምናል፡፡ ርእሰ መጻሕፍቱ እግዚአብሔርን ፈታሔ በጽድቅ ኰናኔ በርትዕ  (ቅንና እውነተኛ ፈራጅ፤ ፍርድአደላዳይ/አስተካካይ ) ይለዋል፡፡ እንደ ሰው ሕግና ፍርድ ሕፀፅ የለበትም፡፡

ኢሕአዴግ የሚባል ከይሲ ቡድን እንዳቀደው ቢሆን ዛሬ የምናያት አንድ ሐሙስ የቀራት የምትመስለው ሀገራችን ወሬ ሆና በቀረች ነበር፡፡ ወንድሜ ጎዳና እውነተኛ ጸሎት በቊዔት (ረብ፣ጥቅም) እንዳለው ጠፍቶህ እንደልሆነ እረዳለሁ፡፡ ግን አገራችን ኢትዮጵያዊ መንግሥት ካጣች መክረሟ፣ ቊጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝባችንም ማስተዋሉ ተነሥቶትና በአገዛዞች ለመታለል ዝግጁ እስከሚመስል ድረስ በሃይማኖት ሽፋን የሠለጠነበት ስንፍና በጭቆና አዙሪት ውስጥ እንደዶለው ከማየት በመጣ ብስጭትና ቊጭት የተሠነዘረ ንግግር አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ዛሬ ሕዝባችን የቀረው ይኸው የሳሳው የሃይማኖት ክር ነው፡፡ ይህች የእምነት ክር ከተጠበሰች ተስፋ ያጣል፡፡ ተስፋ የእምነት ውጤት ነውና፡፡ ተስፋ ካጣ ደግሞ ስለ ሕይወት ማሰብ ሊቆም ነው፡፡ ሕይወትን የሚያስቀጥል ተስፋ ነውና፡፡ ስለሆነም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከምግባር ጋር የታገዘ እውነተኛ ጸሎት የሚያስፈልግበት ሰዓት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ እንዳልኸው ኢትዮጵያን በአፍ እወዳታለሁ የሚለው ብዙ ነው፡፡ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲዖል ያደረጋት ዕቡዩ ዐቢይም ከአንገት በላይ ሲናገረው እስኪታክተን ሰምተናል፡፡ እምነትን ለቆሻሻ ፖለቲካውና ለሥልጣን ጥማቱ ሲጠቀምበትም አስተውለናል፡፡ ግን ወንድሜ መሠረቱ መንፈሳዊነት የሆነ እውነተኛ ጸሎት አገርንም ሆነ ሕዝብን ያለጥርጥር ከጥፋት ይታደጋል፡፡ የዛሬን አያድርገውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ‹የጦር ዕቃ› ጸሎት ነበር፡፡ ዛሬም በእምነት ለጸኑት የጦር ዕቃቸው ይኸው ጸሎት ነው፡፡ ከሀዲውና መሠሪው ዐቢይ ከግብር አባቱ ወያኔ ጋር አብሮ ሕዝብን ስንቅና ትጥቅ አልባ አድርጎ ለእልቂት እንዳጋለጠው ሁሉ ከየትኛውም ቤተ-እምነት የሃይማኖት መሪዎች የተባሉ በደከሙበት ሰዓት ሕዝብ የቀረውን ዋና ‹ስንቅና ትጥቅ› (ጸሎት) ሰላም አያመጣም አይታደግም ካልነው ምርኵዙን ተነጥቆ ምን ተይዞ ጎዞ አይሆንም? የጸሐፊው ፍላጎትና ሃሳብ ባይሆን እንኳን በጥቁርና በነጭ ተጽፎ የምናነበው ይኸው ነው፡፡ በርግጥ ከዚህ አስተያየት ቀደም ብዬ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ በጫርኩት መጣጥፍ ውስጥ እንደገለጽኹት በእግዚአብሔር የማዳን/ቸርነት ሥራ ውስጥ የሰው ልጆች ድርሻ አላቸው፡፡ ጸሎት ከሥራ/ተግባር ጋር ሲተባበር ነው ውጤት የሚያስገኘው፡፡ ከልብ ጸሎት ከማድረጉ ጋር አእምሮና ኅሊናን ተጠቅሞ ከክፉዎች (ከአገር አጥፊዎቹ ወያኔ፣ ኦነጋዊው ኦሕዴድ እና መሠረታቸው ዘረኝነት ከሆኑ አጋንንታዊ ቡድኖች ሁሉ) ጋር አለመተባበርን፤ ጨቋኝን ብቻ ሳይሆን ጭቆናን እምቢኝ ብሎ በሰላም መታገልን ገንዘብ ማድረግ፤ እንዲያው በደመ ነፍስ በነፈሰው ነፋስ አለመወሰድን፣ በተቀደደ ቦይ ሁሉ አለመፍሰስን፤ የአገርን ጉዳይ የአንድ ወቅት ተራ ቲፎዞነት ጉዳይ አለማድረግን፤  በተሠማራበት መስክ ጐሣ ሳይቆጥር ለወገኑ ቅን ማድረግን ባጠቃላይ ላገርና ለወገን የሚበጁ በጎ ሥራዎችን ከማከናወን ጋር መቀናጀት ይኖርበታል፡፡ ያኔ እውነተኛ ጸሎት በቊዔት ይኖረዋል፡፡ ወንድሜ ጎዳና ይህቺን ሃሳቤን ለወገኖቼ እንዳካፍል በጎ ምክንያት ስለሆንከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔንም ሆኑ ሌሎች ባገር ጉዳይ የሚጽፉ ወገኖችን (የአገዛዝ ቅጥረኞችን አይመለከትም – ዓላማቸው ማሳሳትና ማደናግር ስለሚሆን) እንዲህ ዓይነት ስህተት ሊያጋጥም ስለሚችል አንዳንድ ጊዜ ጽሑፋችንን አውለን ወይም አሳድረን ብንመለስበት ያላሰብነውን የተሳሳት መልእክት ወይም ሕዝብን ሊያደናግር የሚችል ሃሳብ ከማስተላለፍ እንድንቆጠብ ይረዳናል፡፡ ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም እንዲሉ የምንጽፈው ሁሉ የታሪካችን አካል መሆኑን ማሰብ አይከፋም፡፡

Filed in: Amharic