>
5:21 pm - Wednesday July 21, 1458

የቅዠት ዓለም ‹ሰንደቅ ዓላማ› እና ‹መዝሙር› (ከይኄይስ እውነቱ)

የቅዠት ዓለም ‹ሰንደቅ ዓላማ› እና ‹መዝሙር›

ከይኄይስ እውነቱ

ወደድንም ጠላንም አንድ ሉዐላዊ አገርና ሕዝብ በዓለም አቀፍም ሆነ በብሔራዊ ደረጃ የሚወከለው በአንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እና ብሔራዊ የሕዝብ መዝሙር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአገሩ መንግሥተ-ቅርፅ አሐዳዊም ሆነ ፌዴራላዊ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ በአንዳንድ እውነተኛ ‹አብሮነትን› (ፌዴራላዊ) ሥርዓት ባቆሙ አገሮች የግዛት ክፍሎች ውስጥ ከብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ ጎን የሚሰቀለው የግዛት መለያ በስሕተት ሰንደቅ ዓላማ እየተባለ ቢጠራም፤ ትክክለኛ ስሙ ዓርማ ነው፡፡ 

ፌዴራላዊ የሚባለው ቅርፀ-መንግሥት የአብሮነት የጋራ ሥርዓት ነው፡፡ ላንድ አገር ልዩ ገጽታ ወይም ልዩ ሁናቴ የሚስማማ እስከሆነ ድረስ አሐዳዊ ቅርፀ-መንግሥትም የአብሮነት ሥርዓት ነው፡፡ በነዚህ ሁለት ቅርፀ-መንግሥታት ረገድ ያለውን የተዛባ አመለካከት በሚመለከት ከዚህ ቀደም ያቀረብሁትን ጽሑፍ መመልከት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ አሁን በምናውቀው ዘመናዊ አስተሳሰብ ረገድ የተሟላ ባይሆንም ኢትዮጵያ በነገሥታቱ ዘመን በንጉሠ ነገሥቱ ሥር የሚተዳደሩ ጠቅላይ ግዛቶች ነበሯት፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ፤ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ትዳሩን ኑሮውን ለመመሥረት የሚንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊ ‹መጤ/ሰፋሪ› ሳይሉ በእኩልነት የሚቀበሉ፤  ለማዕከላዊው መንግሥት ግብር የሚከፍሉ፤ የአገርን ሉዐላዊነትና የግዛት አንድነት ባንድነት የሚያስከብሩ፤ ባንድ አገር ባንድ ሕዝብነት የሚያምኑ ግዛቶች ነበሯት፡፡ ታማኝነታቸውና ታዛዥነታቸው ግን ላንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ነበር፡፡

ባንፃሩም ባለፉት ሠላሳ ሁለት ዓመታት ከስም በዘለለ ፌዴራላዊ ሥርዓት የለም፡፡ በቋንቋ ተቧድነው የሚኖሩበት ግዛት እንጂ ባንዳንዶች ዘንድ የሚነገርለት የማይፈለገውም የጐሣ ፌዴራላዊ ሥርዓት በተግባር አልነበረም፤ የለም፡፡ ከሚቀራመቱትና ከሚዘርፉት በጀት በስተቀር ከማዕከላዊ መንግሥት ተነጥለው፤ የራሳቸውን አጥር አጥረው፤ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ባዕድና ባይተዋር አድርገው፤ እንደ ሉዐላዊ አገር የራሳቸውን ‹ሠራዊት› ይዘው፤ ኢሕአዴግ/ብል(ጽ)ግና ለሚባል አገር አፍራሽ ቡድን ጭፍራና ታማኝ ሆነው፤ በዙሪያቸው ያሉ ጥቂት ቡድኖችን ጥቅም በዝርፊያ የሚያስጠበቅና ሥርዓተ አልበኝነት የነገሠበት የዘራፊ ሽፍታዎች አስተዳደር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የዱርዬዎች አስተዳደር ፌዴራላዊ የሚባል ከሆነ ጽንሰ ሃሳቡን እንደገና መፈተሽ ይገባናል፡፡

ወያኔ ደደቢት በረሃ ያዘጋጀውን ሕገ አራዊት ሲቀርፅ እና ኋላም ‹በጥፊና በእርግጫ› ብሎ ካባረረው ኦነግ ጋር ይህን የጥፋት ሰነድ ይፋ ሲያደርግ ዓላማው 9 ‹ሉዐላዊ› ‹አገሮችን› ፈጥሮ እና ምንነቱ ያልታወቀ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› የሚባልና በጥቅሉ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዐላዊነት ጐሣ ለሚባለው ቡድን አሳልፎ በመስጠት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች› የሚባለው ልዩ ‹ፍጥረት› በተግባር ጐሣ ከሚለው ማኅበረሰብ-ፈጠር ቡድን የተለየ ትርጕም የለውም፡፡ የ ‹ያ ትውልድ› ተማሪ ፖለቲከኞች (በተለይም ‹ኢሕአፓ› የሚባለውና አሁንም በጽላሎተ አምሳል ወይም በሙት መንፈስ የሚንከላወሰው ቡድን) ሳይገባቸው ከባዕድ ተውሰው ካመጧቸው አገር አጥፊ ሃሳቦች መካከል አንዱ ነው፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና፣ የወያኔ ሕወሐት ወራሽ የሆነው ኦሕዴድ/ኦነግ አገዛዝ ኦሮሚያ የሚለውን የቅዠት ዓለም ለማሳካት በዚህ 5 ዓመት ውስጥ ወያኔ በ27 ዓመታት ካደረሰው ጥፈት በእጅጉ የላቀ ጥፋት ፈጽሟል፤ አሁንም በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ ጥፋት የመጨረሻ ዒላማ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት ሲሆን፣ መገለጫዎቹ ግን ፈርጀ-ብዙ ናቸው፡፡ ከነዚህ የጥፋት አጽቆች መካከል በመላው ኢትዮጵያ ግዛቶች በኃይል የኦሮምኛ ቋንቋን በሕዝብ ላይ መጫን፣ የኦነግ ዓርማንና መዝሙር በኢትዮጵያ ላይ እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር በማስፈራራትና በግዴታ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ነው፡፡ ይህ የሽብር ድርጊት በአሳፋሪ መልኩ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ በሆነችው አ.አ. በሚገኙ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሁከትና ሽብር ከመፍጠር አልፎም ደም እስከማፋሰስ ደርሶ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ በዚህም የሽብር ተግባር የወንጀል ሥርዓቱ ከወጣቱና ከነገው ትውልድ ጋር የማይሽር ቅራኔና ጥላቻ እየገባ ነው፡፡ ውጤቱም የቅዠት ዓለሙን የሚያሳካ ሳይሆን ውድቀቱን የሚያፋጥን ሆነ ይታያል፡፡ 

በአምሐራና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ጥላቻ ተመሥርቶ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሲንቀሳቀስ የነበረው ባንዳው ወያኔ የትግራይን ሕዝብ በጭራሽ እንደማይወክለው ሁሉ፤ ይህንኑ የርኵሰት መንፈስ እጥፍ ድርብ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ዘረኛው የኦሮሞ ቡድን ኦሕዴድ/ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ በጭራሽ አይወክልም፡፡ ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ማኅበራዊ መሠረታችን ነው የሚሉትን ሕዝብ ለአገራዊ ጥፋታቸው እንደ መናጆ በመጠቀምና በሥሩ በመወሸቅ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እያጣሉት ይገኛሉ፡፡

በቅርቡ አ.አ. ፈለገ ዮርዳኖስ ትምህርት ቤት የተፈጠረውን እናስታውሳለን፡፡  ጠቅለል አድርጌ ለመግለጽ የሕፃናቱ ተቃውሞ እንዲህ ዓይነት መልእክት ነበረው፡፡ እኛ የተለያየ ቋንቋ ከሚናገሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ የተገኘን በመሆናችን ለምን የአንድ አካባቢና ማኅበረሰብ ቋንቋ እንደ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ካልሰቀላችሁና ካልዘመራችሁ እንባላለን? ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን ሰቅለናል፤ ብሔራዊ መዝሙራችንንም ዘምረናል፤ ተጨማሪው ከየት የመጣ ነው? በማለት ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡

ምናልባት መረጃው ለሌላችሁ አንድ የሚገርም የወንጀል ሥርዓቱን ተሞክሮ ልንገራችሁ፡፡ እንደሚታወቀው በአራቱም ማዕዝናት ከአዲስ አበባ ዳር/ጫፍ ባሉ ቦታዎች (outskirts of Addis) ኦሮምኛ ተናገሪ ወገኖቻችን ይኖራሉ፡፡ አገዛዙ የአዲስ አበባን የቆዳ ስፋት ለማጥበብ የጀመረው ፕሮጀክት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሙሉ በሙሉ እቆጣጠረዋለሁ፣ ነዋሪዎቹም የኔ ናቸው ብሎ በሚያስበው በነዚህ አካባቢዎች በኦሮምኛ ቋንቋ ብቻ ትምህርት የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች ከፍቶ ጥሪ ቢያደርግም ወላጆች ልጆቻቸውን ለመላክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ት/ቤቶቹ ኦና ቀርተዋል፡፡ የዚህ ተሞክሮ አንደምታ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ድንቊርናና ዕብደት የተጣባቸው ጉዶች ነው የገጠሙን፡፡ ከውስጣቸው አንድ ሀይ ባይ እንዴት ይጠፋል? ሀብት መዝረፍ፣ ቅርስን ማጥፋት ይቻል ይሆናል፡፡ የሰውን አእምሮና መንፈስ በኃይል ማንበርከክ ግን የሚሞከር አይደለም፡፡ 

አይደለም! የኦነግን ዓርማ መስቀልና ኢትዮጵያን የሚያወግዝ ኦነጋዊ መዝሙር በኦሮምኛ መዘመር፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የወየኔ ዓርማ ያለበትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዳልተቀበለው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በወያኔ ዘመን የተዘጋጀውን ‹ብሔራዊ መዝሙር›ም ትውልዱ በየትምህርት ቤቱ እንዲዘምር በመደረጉ ቢያውቀውም፣ የወንጀል ሥርዓቶቹ ያስተዋወቁት በመሆኑ ከሕዝቡ ጋር ተዋሕዶና ብሔራዊ ስሜቱን ፈንቅሎት የሚዘምረው አይደለም፡፡ ነፍሳቸውን ይማርና ፕሮፌሰር መሥፍን በመጽሐፋቸው ‹‹እንዘጭ! እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ›› እንደጠቆሙት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ገላጭ በሆኑ የጋራ አኩሪ ታሪኮች፣ እሴቶችና ባህሎች ላይ ተመሥርቶ የተሻለና አገዛዞች በተለዋወጡ ቊጥር የማይለወጥ ብሔራው መዝሙር ማዘጋጀት እንደሚቻል በአብነትም መልክ አሳይተዋል፡፡

ለመሆኑ አገር አፍራሾቹ ወያኔና ወራሹ ኦሕዴድ ለለበጣ ካልሆነ በቀር የሰንደቅ ዓላማ ቀን ብለው የመሰየምና እንዲታሰብ የማድረግስ የሞራል ልዕልናው አላቸው?

Filed in: Amharic