ከይኄይስ እውነቱ
አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፡፡ ምሳሌ 22÷28
ሃይማኖትን በሚመለከት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የሚመጡ ጉዳዮችን ተራ ተርታ አድርጎ መመልከት ኋላ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ ራሱን ችሎ ባይሆንም አንዳንድ መጣጥፎችን በማሳሰቢያ መልክ ለማቅረብ ሞክሬአለሁ፡፡ ራሱን ‹‹የጃንደረባው ትውልድ›› ብሎ የሚጠራው ይህ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር ተጠልሎ በይፋ የታየው በቦሌ ደብረ ሳሌምመድኃኔዓለም መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ወአቡነ አረጋዊ ዓቢይ ደብር (ካቴድራል) ነው፡፡ በወቅቱ የቤተክርስቲያኒቱ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት በትርያርክ አቡነ ማትያስ ሕዝባዊ ዜማ ላቀረበው ‹‹የአእላፋት ዝማሬ›› ለተባለው ስብስብ እና ለምእመናን ባደረጉት ንግግር (ቃል በቃል የተወሰደ ባይሆንም) ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት የተንጣለለ ሰፊ ዓፀድ እያላት በዓላትን አደባባይ መውጣት ሳያስፈልጋት በቅፅር ግቢዋ ማክበር ትችላለች የሚል አነጋጋሪ አንደምታ ያለው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ዓላዊው የጐሣ አገዛዝ የኢኦተቤክ የአደባባይ በዓላትን የምታከብርበትን ሕጋዊ ይዞታዎች በጉልበት ከመከልከል እስከ መቀማት ላሳየው ድፍረት የተሰጠ ጥብዐት የጎደለው መልስ ይመስላል፡፡
ጊዜው ተዋሕዶ ሃይማኖታችንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ኢትዮጵያ አገራችንን እያመሱ ባሉት በዓላውያንየጐሣ አገዛዞች ከፍተኛ ፈተና ላይ የሚገኝበት (ፈተናው የጐሣ አገዛ ያነገሠው ቆሻሻ ሥርዓት እስካለ ድረስ ይቀጥላል)፤ አገልጋይ ካህናት፣ ገዳማውያን መነኮሳት፣ የአብነት ተማሪዎች ፣ምእመናን የሚታረዱበት÷ የሚደበደቡበትና የሚዋረዱበት፤ አድባራትና ገዳማት እስከ ቅርሳቸው የሚወድሙበት፤ በዓላትን በአደባባይ ማክበር የማይቻልበት፣ በአደባባይ አምልኮ መፈጸሚያ ቦታዎች በአገዛዙ ኃይሎች የተወሰደበት፣ የበዓላት ውበትና ድምቀት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መያዘም ሆነ በየትኛውም መልኩ መጠቀም እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሚያስደበድብናየሚያሳስር ነበር÷ አሁንም ነው፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ‹‹የሃይማኖት አባቶች›› ተብለው በቤተ ክህነቱ የተጎለቱት ርጉም ዐቢይ ሠራሾቹም ሆኑ ቀደም ሲል በማማለጃ/እጅ መንሻ የተሰየሙት፤ ክህነታቸውን አፍርሰው በነውር የተያዙትም ሆነ በፍርኀት ተሸብበው አስደንጋጭ ዝምታ ውስጥ የወደቁት፤ እንዲሁም እንደ ‹ዴማስ› ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ ብለው ሀብት ከብትን÷ ገንዘብ ንብረትን ‹አምላካቸው› ያደረጉት፤ ምእመኑን ለማይነጥፈው ገንዘብ ብቻ የሚፈልጉት፤ሰማይ ሩቅ አደራ ጥብቅ ተብሎ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ቁርጥም አድርገው በልተው ምእመኑን ተቅበዝባዥ እረኛ አልባያደረጉበት፤ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር እውነትንና ጥብዐትን ገንዘባቸው ያደረጉ መሪዎች አልባ በማድረግ ክህደት የፈጸሙበት፤ መንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሲኖዶስ የሌለበትነበር÷ አሁንም ነው፡፡ አሁንም ያለውና የቀጠለው ይኸው በዝርዝር የቀረበው መራር እውነት ነው፡፡
እንግዲህ የአሁኑን ርእሰ ጉዳይ የምናየው ይህንን የጀርባ ታሪክ በዓውድነት በመያዝ ይሆናል፡፡ ከስሙ እንጀምር፡፡ ‹‹የጃንደረባው ትውልድ›› የሚባል ማኅበር ቤተ ክህነቱ ዕውቅና ሰጥቶት ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕጋዊ ነኝ ሊል ይችላል፡፡ ይህ ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ ቤተ ክህነቱ በዐላውያንና የነሱ ተከታዮች በሆኑ መለካውያን ቊጥጥር ሥር ከዋለ ዓመታት እንደተቆጠሩ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ እንደማለት ይሆንብናል፡፡ ‹ጃን ደረባ› የሚለው ቃል የተለያዩ ትርጕሞች አሉት፡፡ አንዱ በወንጌሉ እንደተመለከተው ራስን ስለ ጽድቅ ብሎ ከሴት ርቆና ንጽሕ ጠብቆ የሚኖር ማለት ነው፡፡ ማቴ. 19÷12፡፡ ‹አእላፋት ዝማሬ› ከሚባለው እንቅስቃሴ በስተጀርባ ያለው ‹ማኅበር› ስያሜውን የወሰደው በግብረ ሐዋርያት ም.8 ቊ. 27 የተጠቀሰውንና ላገሩ ሐዋርያ የሆነውን ‹ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ› ባኮስን አስቦ ከሆነ ትርጕሙ በዥሮንድ የገንዘብ ሹም (በዘመናዊው አጠራር የገንዘብ ሚኒስትር)ማለት ነው (ዐዲስ ዐማርኛ መዝገበ ቃላት፤ አ.ደ.ተ.ወ)፡፡ የሱ ተከታይ ትውልድ ነን ለማለት ከሆነ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆንብናል፡፡ ሌላው በተፈጥሮ ትእምርተ ተባዕት የጐደለው ወይም የተባዕትነት ትእምርቱ በሰው የተሰለበ(ሕፅው) ማለት ነው፡፡ ይኼኛው ትርጕም በምስጢራዊ ፍቺውየሚስማማው ይመስላል፡፡ የመከነ ትውልድ ለማለት፡፡ ለምን የሚለውን ወረድ ብለን ለማየት እንሞክራለን፡፡
ሌላው በ‹ጃንደረባው ትውልድ› የሚመራው እንቅስቃሴ ‹የአእላፋት ዝማሬ› የሚለው ቃል ነው፡፡ አእላፋት የግእዝ አኀዝ ስያሜ ሲሆን ቀጥታ ሚልዮን ማለት ነው፡፡ በምስጢር ደግሞየብዙ ብዙ ወይም የማይቆጠር ማለት ነው፡፡ የማይቆጠሩ መላእክት ናቸው፡፡ ስለሆነም የመላእክት ዝማሬ ለማለት ይመስላል፡፡ ማኅሌታዊው ቅ. ያሬድ ‹‹ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑመላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ ንጉሥ››፡፡ (ሰውናመላእክት ንጉሥ ክርስቶስን ያመሰግኑት ዘንድ አንድ ሆኑተባበሩ፡፡) በማለት ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ›› (በሰማያት ምስጋና ተደረገ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ/ሰላም ሆነ፡፡ ሉቃ. 2÷12) ብለውበልደቱ ማመስገናቸውን የተናገረው በዓለማዊው ቅኝት በዝላይ በጭፈራ የሚቀርበውን ‹ግርግርታ› አይደለም፡፡ ስያሜው ይህን ታሳቢ አድርጎ ከሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመላእክት ያገኘችው ሰማያዊ ዜማ ያሬዳዊውን ዜማ ነው፡፡ ስብስቡ የሚዘምረው ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ‹ሕዝባዊ ዜማ› የሚባለውን ነው፡፡ ለዛውም ወደ ጭፈራና ዝላይ ያደላ፡፡ስለሆነም የስም ተፋልሶ ይታያል፡፡ በነገራችን ላይ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ/ቁም ነገሩ ይህ ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ከሥሩ ውኃ ከጥሩ እንደሚባለው ለአንባቢ መሠረት ለማስያዝ እንዲረዳ ነው የቃላቱን ፍቺ ያስቀደምነው፡፡
ቁልፉ ጥያቄ ይህ በተጠቀሰው ማኅበር የሚመራው ‹የአእላፋት ዝማሬ› የሚባለው እንቅስቃሴ እንዴት ተጀመረ? ለምን አስፈለገ? ከሁሉም በላይ የተዋሕዶ ሃይማኖት በዓላት አከባበር ሥርዓት ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ባጭሩ ዓለማዊ ዕውቅና ፈላጊ በሆኑ ‹ሰባክያን› (ባንድ ጽሑፌ ‹ሴሌብሪቲ ሰባክያን› ባልኳቸው) ተልእኮ ተሰጥቷቸው የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ግንባር ቀደሙ ‹ሴሌብሪቲ› ‹ዲ/ን ሄኖክ› የሚባል ግለሰብ ነው፡፡ ዛሬ ይህ ግለሰብ በእውር ድንብር የሚከተሉት በርካታ ተከታዮች አፍርቶ ለምን ይተችብናል ለምን ስሙን በክፉ ታነሱብናላችሁ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉና አልፎም ለዱላ የሚጋበዙ ‹የቤተ ክርስቲያን ልጆች› አሉ፡፡ ጊዜው በዓለማዊውም መስክ ሆነ በመንፈሳዊው ሕይወት ሽፋን በንዋይ የሰከሩ፣ የአገዛዙን ፖለቲካ እና የባዕዳንን የምንፍቅና እምነት ለማስፈጸም ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና ግለሰቦች እንደ አሸን የፈሉበት ነው፡፡ አንባብያን ባጠቃላይ፣የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በተለይ የምታስታውሱ ከሆነ አንድ ወቅት ራሱን ‹መ/ር ምሕረተ አብ› ነኝ የሚል ‹ሴሌብሪቲ ሰባኪ› ‹‹የማንቂያ ደወል›› በሚል ስያሜ በየመድረኩ ገኖ ለአገር አጥፊው አገዛዝ ተልእኮ ተሰጥቶት ሲሠራ የነበረ፣ የምእመናን ገንዘብ ዘርፎ ሲያበቃ አሁን ስም አጠራሩም የጠፋ ሰው ነበር፡፡ቀደም ብሎም ገብረ መስቀል የሚባል ዲቁናውን ያፈረሰ ግለሰብ ‹ባሕታዊ› ነኝ እያለ ለአገዛዞች የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ የከተተና አሁንም ከዚህ አጭበርባሪነቱ ያልታቀበ ሰው እንዳለ እናውቃለን፡፡ በቅርቡ ደግሞ ‹እኅተ ማርያም› የተባለችው ከአእምሮዋ የተለየች ሴት ‹ነቢዪት› ነኝ በማለት አገር ስታመስ መክረሟ እና ብዙዎችን ገደል መክተቷ የሚታወስ ነው፡፡ ክህነት ሳይኖረውና ምንኵስና ሳይቀበል (ነውሩን በቅዱስ እስጢፋኖስ ደብር የጀመረ) ራሱን ‹አባ› ብሎ በ‹አጥማቂነት› ከአገር ቤት እስከ ውጩ ዓለም አሁንም እያጭበረበረና የሞኞችን ገንዘብ እየዘረፈ የሚገኘው ግርማ የተባለ ግለሰብ የአገር መነጋገሪያ መሆኑን የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ‹ምድራዊ ባለቤት› አጥታ የበርካታ ‹ቊጭ በሉዎች› መናኸሪያ ከሆነች ውላ አድራለች፡፡ የሚገርመኝና የሚያሳዝነኝ ግልብ የሆነውና ቊጥሩ በርካታ የሆነ ወጣት ትውልድ (‹ጃንደረባው›/የመከነው ትውልድ – ቊጥራቸው በርካታ የሆኑ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ጭምር) አእምሮው ተሰልቦ እነዚህን በየጊዜው አፍራሽ ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አጭበርባሪ ግለሰቦች ሰለባ መሆኑ ነው፡፡በመግቢያችን እንደጠቀስነው ቊጥራቸው ቀላል የማይባል የቤተ ክህነቱ ‹ባለሥልጣናት›ና አንዳንድ ‹ከሊቃውንቱም ወገን› የሆኑ ግለሰቦች ከእንደዚህ ዓይነቱ የውንብድና ተግባር ተጠቃሚዎችና በነውሩም ተባባሪ በመሆናቸው ተራውን ምእመን ከአፍራሽ እንቅስቃሴዎቹ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ አክብዶታል፡፡
‹የአእላፋት ዝማሬ› የተባለውን እንቅስቃሴ የሚመራው ‹ጃንደረባው/የመከነው ትውልድ› ማኅበር በዝማሬ ስም የሚያካሂደውን ‹ግርግር› በቅድሚያ መስቀል አደባባይ ቀጥሎም ጃን ሜዳ እንዲፈቀድለት አገዛዙን ጠይቆ የነበረ ቢሆንም አልተፈቀደለትም፡፡ በዚህም ምክንያት የመጀመሪያውን ‹ትርኢት› በቦሌ መድኃኔ ዓለም አካሂዶ የበትርያኩን ‹ቡራኬ› አግኝቷል፡፡ ከዚያም በኋላ በዓለ ንግሥ ባለባቸው የዐዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት እየዞረ ግርግር መፍጠሩን ቀጥሏል፡፡ በመሪነት የጠቀስነው ግለሰብ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ባይኖረውም የካቶሊክ እምነት ዓለም አቀፍ መቀመጫ ወደሆነው ቫቲካን ተልኮ በተቀበለው መመሪያና ይህም ተልእኮ ፋሺስታዊው የጐሣ አገዛዝ በነጮቹ ከተሰጠው ተዋሕዶ ሃይማኖታችንንባጠቃላይ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን በተለይ ለማጥፋት ከሚያደርገው አፍራሽ እንቅስቃሴ ጋር የሰመረ በመሆኑ ባንድ ወገን፤ በሌላ በኩል አገዛዙ ከፍ ብለን የጠቀስነውን የተዋሕዶ ሃይማኖት አገልጋዮችንና ተከታዮችን በየክፍላተ ሀገሩ የመግደልና የማሳደድ ተግባሩን አጠናክሮ የመቀጠሉ ሰይጣናዊ ተግባር በተቆርቋሪ ምእምናንና ጥቂት እውነተኛ አገልጋይ አባቶች በውጩ ዓለም መጋለጡ ለሥልጣኑ አሳሳቢ ስለሆነበት ‹የገጽታ ግንባታ ሥራ› መሥራት ግዴታ ሲሆንበት ‹የአእላፋት ዝማሬ› በአደባባይ እንዲካሄድ ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ፈቅዷል፡፡ እንቅስቃሴው ቤተ ክህነቱንም ሆነ ቤተ መንግሥቱን በጋራም ሆነ በተለያየ ምክንያት የሚጠቅም ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ክዶ ለዐላውያኑ ያደረውናየመለካውያን ስብስብ የሆነው ቤተ ክህነት፣ ጀርባውን የሰጠውን ምእመን በተለይም የወጣቱን ልብ ለማግኘት ለ‹አእላፋት ዝማሬ› እንቅስቃሴ ዕውቅና በመስጠት የገቢ ምንጩ እንዳይነጥፍ መያዣ መንገድ አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ አገዛዙ ደግሞ ‹ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ› ተብሎ ለሚታወቀው ለምዕራቡ ኃይል የእምነት ነፃነት አክባሪ መሆኑን ለማሳየት እንቅስቃሴውን ለጊዜው ‹በእሳት አደጋ አጥፊነት› ከተሳካለት ደግሞ ለኢኦተቤክ ተቈርቋሪ ኃይሎች በተገዳዳሪነት የሚቆም(ዶግማውን፣ ቀኖናውን/ሥርዓቱን ለመሸርሸር ብሎም ለማጥፋት መሣሪያ የሚሆን) ማኅበር አድርጎ ለመጠቀም እየሠራ ይገኛል፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የአፍራሹን እንቅስቃሴ ዓላማና ተልእኮ ባለማወቅ ግርግሩን የተቀላቀሉና ሰለባ የሆኑ በርካታ ንጹሐን የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እንዳሉ ሁሉ፣ ከመነሻው ዓላማውንና ተልእኮውን ተረድተው (የዋኀኑንና ንጹሐኑን መሣሪያ አድርገው)፣ በተጠናና በተደራጀ መልኩ የሚሠሩም አሉ፡፡ ራሱን በመሪነት የሰየመው ‹ሴሌብሪቲ ሰባኪ› ከአገዛዙ መመሪያ ተቀብሎ በዚህ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ ‹ምእመናንን› አለባበስ ሥርዓት (‘dressing code’) ሁሉ ወስኗል፡፡ በዚህም መሠረት ወንድም ሆነ ሴት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማምልክት የሌለበት ነጭ ልብስ ብቻ እንዲለብሱ ያዘዘ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩ የሚመራው በጣዖት አምላኪዋ አዳነች አበቤ የጉልበት አስተዳደር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህች የዮዲት ጉዲት አምሳል የቤተክርስቲያኒቱን የአደባባይ በዓላት ከተቆጣጠረች ውሎ አድሯል፡፡ እያንዳንዱ መርሐ ግብር ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ ምእመኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን የበዓል አከባበር ሥርዓት ተከትሎ በፈቃዱ የሚያደርገው ሳይሆን አስቀድሞ የተቀነባበረ (Orchestrated የሆነ)ነው፡፡ በቅርቡ በዓለ ልደትን ታኮ በተካሄደው የቡድኑ መርሐ ግብር ጊዜው የሐዘን ነው ብለው ጥቁር ለብሰው የሄዱ ‹ምእመናን› በፖሊስ እየተገፈተሩ ተባርረዋል፡፡ ነጭ ልብስ የሌለው ሁሉ ‹የጭፈራው/የዝላዩ› አካል እንዲሆን አልተፈቀደለትም፡፡ እዚህ ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ያለ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የወጣ ድርጊት ‹‹የጥበብ ሰዎች›› በተለምዶ አርቲስት በተባለት በተደጋጋሚ ሲፈጸም እያስተዋልን ነው፡፡ አሁን ርእስ ባደረግነው ‹የአእላፈት ዝማሬ› እንቅስቃሴም ሆነ ቤተ ክርስቲያናችን በምታከብራቸው ክብረ በዓላት በተለይም ‹የውስጥ ካድሬዎች› በሚያካሂዱት ‹የቴሌቶን መርሐ ግብር› ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ሆነው እናያለን፡፡ በየንግሡ በሚካሄደው ‹የገንዘብ ዝርፊያ መርሐ ግብር› ታዋቂው አርቲስት እገሌ ይገኛል አጨብጭቡለት እልል በሉለት ተብሎ ዓውደ ምሕረት ይለቀቅለታል፡፡ ወገን! ወደ እናታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መምጣታችሁ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ብዙዎቻችሁም የትምህርት መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላችሁ ትምህርተ ክርስትናን መከታተላችሁ አበጃችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ያጽናችሁ የሚያሰኝ ነው፡፡ በሊቃውንት ታግዛችሁ መንፈሳዊ ትእይንተ ጥበብ (ቴአትርም ሆነ ፊልም) ካዘጋጃችሁም ይደልዎ በርቱ የሚያሰኝ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በበዓላትም ሆነ በተለያዩ የቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊ መርሐግብር ላይ በመገኘት ታዋቂነትን ማትረፊያ ማድረግ ዋጋችሁን ምድራዊ እንደሚያደርገው መዘንጋት የለባችሁም፡፡ ‹ቆራቢ አርቲስት› የሚል ቋንቋ ከየት የመጣ ነው? ይህ ንግግር ‹የአእላፋት ዝማሬ› በተባለው የ‹ጃንደረባው ትውልድ ማኅበር› የዘንድሮው የጌታ ልደት መርሐ ግብር ላይ (ልዩ የክብር ቦታ ለቈራቢ አርቲስቶች ስለሚሰጥ ተመዝገቡ የሚል ማስታወቂያተሰምቷል፡፡ ጉድ በል ሺዋ! ይህ ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የወጣ ውዳሴ ከንቱ ነው፡፡ ቅ.ጴጥሮስ ከሰቃልያነ እግዚእ ራሱን ለመደበቅ ‹አምላኩን አላውቀውም› ብሎ በካደ ጊዜ አንተ ከሱ ወገን ነህ በንግግርህ ትታወቃለህ፡፡ የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ‹ወፍ ዘራሾች› ከንግግራቸው የተዋሕዶ ልጆች አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡ ወንጌሉ ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድ ይጠንቀቅ ነው የሚለው፡፡ (1ቆር.10÷12)ዋናው ቁም ነገር እንደ ‹አእላፍ ዝማሬ› ባሉ አፍራሽ መርሐ ግብሮች ላይ በመገኘትና በማዳመቅ የቀረውን ምእምን የማሰናከል አካል እንዳትሆኑ ትመከራላችሁ፡፡ አደራችሁን! ሕጋዊ ነው ቤተ ክህነቱም ሆነ ቤተ መንግሥቱ ፈቃድና ዕውቅና ሰጥተውታል ወደሚል ክርክር እንዳትገቡ፡፡ ፈቃጆቹ/ዕውቅና ሰጪዎቹ አገርና ቤተ ክርስቲያን አፍራሾች ናቸው፡፡ ዓላውያን (ከሃድያን አገዛዞች) እና መለካውያን (በቤተ ክህነቱ ከላይ እስከ ታች የአመራር ቦታ የያዙ የጐሣ ፋሺስቶች ፈቃድ ፈጻሚዎች) ናቸው፡፡
በቀጣይነት የምናነሳው ‹የአእላፋት ዝማሬ› የተባለው እንቅስቃሴ የኢኦተቤክ የበዓል አከባበር ሥርዓት አካል ነው ወይ? ቤተ ክርስቲያናችን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ የታነፀች በመሆኗ መሠረተ እምነቷ (dogma)፣ አስተምህሮዋ (doctrine)፣ ቀኖናዋ/ሕጓ (canon) እና ሥርዓቷ (order) በሙሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን እና ቅዱስ ትውፊትን (sacred tradition) መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ‹ስንዱ እመቤት› በመሆኗ ዘመነ የወለደውን ጊዜ የወደደውን በዘፈቀደ የምትከተል አይደለችም፡፡ ዐሥራ አራት መልእክታትን የጻፈልን ታላቁ ሐዋርያ ቅ. ጳውሎስ ‹ሁሉ ባግባቡና በሥርዓቱ ይሁን›1ቆሮ.14÷40 ብሎ እንዳስተማረን ከሥርዓት ያፈነገጡትን በእግዚአብሔር ቃል መገሠፅ ተገቢ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለ ምክንያት የምትፈጽመው አንዳች ነገር የለም፡፡ ‹ምናለበት› ተብሎ የሚደረግ ነገር ከቤተ ክርስቲያን አይደለም፡፡መምህራን እንደሚያስተምሩን ‹ምናለበት› የምዕራቡ ዓለም የልቅነት/የእግዚአብሔር አልቦነት መገለጫ የሆነው የሊበራሊዝም ርእዮት አስተምህሮ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ዘመንን መዋጀት ማለት ሰዎች ጭፈራና መሸታ ቤት እንዳይሄዱ በማለት እንግዳ የአደባባይ ‹ግርግር› በስርዋጽ ማስገባት አይደለም፡፡ ከመሠረተ እምነት፣ ከአስተምህሮ፣ ከቀኖና/ሥርዓት ወዘተ. አኳያ በሚገባ ተመርምሮ ሲያበቃ ከታመነበት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖ የሚፈጸም እንጂ በዘዋሪ ደብዳቤ (circular) የሚፈጸም ተራ ተርታ ጉዳይ አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማስጮኽና ‹ዓለም ጉድ አለ› በማለት እውነት አይቀየርም፡፡ በመንፈሳዊው ሕይወት ረገድ የምናከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ስማችን ‹በሕይወት መጽሐፍ› እንዲጻፍ እንጂ ዩኔስኮ ለማስመዝገብ ወይም ዓለም ጉድ እንዲለን መሆን የለበትም፡፡ በቊጥር ብዛት አንደነቅ፡፡ የኢኦተቤክ የምእመናን ደሀ አይደለችም፡፡ ምእመናን!እግዚአብሔር አምላክ በጠቢቡ ሰሎሞን አደሮ የተናገረውን ይህን ቃል አስተውሉ፡፡ አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ፡፡ (ቅዱሳኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ያመኑበትን እምነት ያቆዩልንን መንፈሳዊ ትውፊትጠብቅ፤ የሠሩልንን ቀኖና/ሥርዓት አክብር/ተከተል ማለት ነው፡፡) ምሳሌ 22÷28
አንድ ወቅት ላይ የፕሮቴስታንቱ ቡድን ‹ተሐድሶ ኦርቶዶክስ› በሚል ሽፋን በቤተ ክርስቲያናችን ሠርጐ ገብቶ (አሁንም አሉ፤ ‹አእላፋት የተባለው እንቅስቃሴም ከጀርባ በመናፍቃኑ የሚነዳ ነው) ያልጸኑና በቂ ትምህርት የሌላቸው ምእመናንን ሲያስኮበልል የተመለከቱ የቤተ ክርስቲያኒቷ ነን የሚሉ አንዳንድ ‹ሰባክያን እና ምእመናን› ብዙዎች በፕሮቴስታንቱ ‹መዝሙር› ነውና ተስበው የሚሄዱት ‹ምናለበት› ወጣቱን ለመያዝ የሙዚቃ መሣሪያውንም ሆነ ዜማውን አሻሽለን ብናቀርብ በሚል ሰማያዊውን የቅዱስ ያሬድ ዜማ በ‹ዘፈን› ሊቀይሩ የዳዳቸው እንደነበሩ የምናስታውሰው ነው፡፡ ተዋሕዶ ለመዝሙር/ለማኅሌት፣ ለጾም/ለሱባኤ፣ ለጸሎት፣ ለስብከት/ለትምህርተ ወንጌል፣ ለሁሉም ሥርዓት አላት፡፡ ልዑል እግዚአብሔር የሥርዓት አምላክ ነውና፡፡ እንደሚታወቀው የጌታችንን ልደት፣ ጥምቀትና ትንሣኤ በዓላት የምናከብረው የተጋብኦ ደወል ከተደወለበት ምሽት አንስቶ ሌሊቱን በቤተ ክርስቲያን ዓፀድ ተሰባስበን የቅዳሴውና የማኅሌቱ ሥርዓትተከፋይ በመሆን ነው፡፡ ይህ ከሐዋርያት፣ ከዚያም ከሐዋርያን አበው፣ ከዚያም በየዘመኑ ከተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ትውፊት ሲተላለፍልን እኛ ዘመን የደረሰ የበዓል አከባበር ሥርዓት ከሺሕ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ እነዚህ በዓላት እንደ መስቀልና ጥምቀት የአደባባይ አይደሉም፡፡ የቤተ ልሔም (ኤፍራታ) ምሳሌ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን አራቁቶ በታቀደ ሁናቴ ተደራጅቶ አደባባይ ወጥቶ መጨፈርና መዝለልን ምን አመጣው? የማን ተልእኮ ነው? ጎበዝ እናስተውል! ቤተ ክርስቲያን በውስጥ (አገርና ምእመናንን በካዱ አብዛኛው የቤተ ክህነቱ ሰዎች) በአፍኣ (በርጉም ዐቢይ በሚመራው ፋሺስታዊ የጐሣ አገዛዝ) ፈተና ላይ እያለች ባለማወቅ ይህ ‹የአእላፋት ዝማሬ› በተባለ አፍራሽ እንቅስቃሴ ሰለባ ሆናችሁ ተጨማሪ ፈተና እንዳትሆኗት ሳትዘገዩ ንቁ! ንቁ! ንቁ! የሚል ጥሪአችንን እናስተላልፋለን፡፡ በተለይም ወጣቶች የሰንበት ተማሪዎች ጭፈራ አያታላችሁ፡፡ የምትጎዱት እናንተ ናችሁ፡፡ ስሜታዊነት የትም አያደርስም፡፡ ኋላ ላይ ጩኸታችሁ የማይጠቅም ከመሆኑ በፊት ረጋ ብላችሁና ምክንያታዊ ሆናችሁ አስቡ፡፡ እውነተኛ አገልጋዮችና ምእመናን ሰማዕትነት ሊቀበሉ ይችላሉ፤ አድባራትና ገዳማት ከቅርሶቻቸው ጋር ሊወድሙ ይችላሉ፤ ዓለም ከከሃድያኑና መናፍቃኑ ጋር ሊቆም ይችላል፤ እውነት ልትሳሳ ትችላለች፡፡ የኢኦተቤ ግን ራሷና ጉልላቷ መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ፈተናውን ማለፏ አይቀርም፡፡ ለሺህ ዓመታት የጠላት ዲያቢሎስ ገንዘቦች ከሆኑ ኃይሎች የተቃጣባትን ነጐድጓዱን፣ መባርቅቱን፣ ወጀቡን፣ ማዕበሉን፣ ቀስቱን፣ ጦሩን ወዘተ አሳልፋ እንደኖረች ሁሉ አሁንም ትቀጥላለች፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን÷ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናችንን ከፈተና ሁሉ ይጠብቅልን፡፡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን ያስታግሥልን፡፡ አሜን፡፡

























